በ300 ዓመታት ትልቁ የተባለ አልማዝ አንጎላ ውስጥ ተገኘ

በሰሜን ምሥራቅ አንጎላ በመጠኑ ትልቅ የተባለ ሮዝ ቀለም ያለው አልማዝ መገኘቱ ተገለጸ።

ሉካፓ የተሰኘው ማዕድን አውጪ ኩባንያ ከ300 ዓመታት ወዲህ በመጠን ተስተካካይ የሌለው አልማዝ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው ብሏል።

የአውስትራሊያው ኩባንያ ባለ 170 ካራት የከበረ ድንጋዩን ‘ዘ ሉሎ ሮዝ’ የሚል ስያሜ ሰጥቶታል።

ይህ አልማዝ በአፍሪካዊቷ አንጎላ መንግሥት የአልማዝ መሸጫ ኩባንያ አማካይነት ለዓለም ገበያ እንደሚቀርብ ተገልጿል።

የአንጎላ ማዕድን ሃብት ሚንስትር ዲአማንቲኖ አዜቬዶ “ይህ ሪኮርድ የያዘ እና አስደናቂ ሮዝ አልማዝ በሉሎ መገኘቱ አንጎላ በዓለም መድረክ አሁንም በአልማዝ ምርት ቀዳሚዋ መሆኗን ያሳያል” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በአንጎላ ከተገኘው አልማዝ ጋር ተቀራራቢ መጠን ያላቸው የከበሩ ድንጋዮች ማስተካከያ ከተደረገላቸው በኋላ ክብረ ወሰን በሰበሩ ዋጋዎች ሲሸጡ ነበር።

እአአ በ1999 በደቡብ አፍሪካ ተገኝቶ የነበረው 59 ካራት ሮዝ አልማዝ በ71.2 ሚሊዮን ዶላር 2017 ላይ ተሽጦ ነበር።

ዘ ፒንክ ስታር የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የከበረ ድንጋይ እስካሁን በውድ ዋጋ የተሸጠው አልማዝ ነው።

አንጎላ ነዳጅን ጨምሮ በርካታ የከበሩ ድንጋዮች መገኛ አገር ነች።

እንደ ስታቲስታ 2021 መረጃ ከሆነ፤ አንጎላ ከናይጄሪያ እና አልጄሪያ በመቀጠል፤ 7.8 ቢሊዮን በርሜል የነዳጅ ክምችት አላት።