በአማራ ክልል ስለተፈጠረው የፀጥታ ችግር እስካሁን የምናውቀው

በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ግጭቶች እና ሕዝባዊ ተቃውሞዎች መሰማት ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል።

በሚያዝያ ወር የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌደራል ፀጥታ መዋቅሮች እና በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ማካተት መጀመሩን ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልሉ ከተሞች ተቃውሞ እና ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።

በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የታዩት ተቃውሞዎች “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ትጥቅ አይፈታም” በሚል የተቀሰቀሱ ነበሩ።

በዚያው የሚያዝያ ወር በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች እና በአማራ ክልል ልዩ ኃይል መካከል አለመግባባት እና “ከፍተኛ ውጥረት” መፈጠሩን በማመልከት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መግለጫ አውጥተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው “ለኢትዮጵያ አንድነት” እና “ለሕዝብ ሠላም” ሲባል አስተዳደራቸው የክልሉን ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌላ መዋቅር ማስገባት እንዳስፈለገ በወቅቱ ገልጸዋል።

ይህ ተቃውሞ እና ውጥረት በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የተስተዋለ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሮችም ጥብቅ ክልከላዎችን ጥለው ነበር።

የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ ለማዋቀር ይፋ ከሆነው ውሳኔ ጋር በተያያዘ የደብረ ብርሃን፣ የጎንደር እና የደሴ ከተሞች፣ ከፀጥታ ኃይል አባላት ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን ጨምሮ ሌሎች ገደቦችን ጥለው ነበር።

በወቅቱ የከተማ አስተዳደሮቹ ይህንን ያስተላለፉት የከተሞቻቸውን ሰላም እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል መሆኑን አስታውቀው ነበር።

ግጭት በታጣቂዎች እና በመከላከያ መካከል

ለመጀመሪያ ጊዜ በታጣቂ ኃይሎች እና በመከላከያ መካከል ግጭት መከሰቱ የተዘገበው ሚያዝያ 01/2015 ዓ.ም. በቆቦ ከተማ ነው።

በዚህች ከተማ በወቅቱ በአማራ ኃይሎች እና በአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል በከባድ መሳርያ የታገዘ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱ ተዘግቧል።

ምንም እንኳ ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን የሟቾችን ቁጥር ማጣራት ባይችልም፣ የፋኖ አባላት መሆናቸው የተገለፁ ሰዎች መሞታቸውን ከነዋሪዎች ሰምቷል።

ከዚህ በኋላም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከአማራ ኃይሎች ጋር ተጋጭቶ ሁለት ሰዎች እንደሞቱ እና አንዲት ሴት ጉዳት እንደደረሰባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ከዚህ በኋላም በጎንደር፣ በደብረሲና እና በሸዋ ሮቢት እና በሌሎችም ከተሞች የወትሮ እንቅስቃሴዎች መገታታቸውን እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሰማራታቸው ተናግሮ ነበር።

ከዚያ በተጨማሪም በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም፣ ጂጋ እና ደምበጫ ከተሞች በፀጥታ ኃይሎች እና በወጣቶች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ውሳኔን ተከትሎ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተነሳው ተቃውሞ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ እና ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች፣ በተወሰዱ እርምጃዎች እና በተፈጸሙ ጥቃቶች የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞችን ጨምሮ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት መከሰቱን ኮሚሽኑ በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

በወቅቱ ኢሰመኮ የፀጥታ አካላት ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፣ ሁሉም ሰው ሃሳቡን በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጽ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ መንግሥት ለደረሰው ጉዳት አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲሰፍንም ጠይቋል።

የባለሥልጣናት ግድያ

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸው የተሰማው ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም. ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ “ከእኛ የተለየ ሃሳብ ማሰብ አልነበረበትም ብለው የሚያምኑ ነውጠኞች እና ጽንፈኞች በፈጸሙት አስነዋሪ እና አሰቃቂ ተግባር” አቶ ግርማ የሺጥላን መገደላቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የአቶ ግርማ ግድያን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ኃላፊው የተገደሉት “በኢ-መደበኛ ኃይሎች” ነው ብሏል።

ከአቶ ግርማ ግድያ በኋላም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ ውስጥ ባሉ የአካባቢ የፀጥታ ኃላፊዎች ላይም ግድያ ተፈጽሟል።

በተጨማሪም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል።

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ምንውየለት ጭንቅሎ የተገደሉት አርብ ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም. እንደሆነ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል እና የፌደራል መንግሥቱ የክልሉ ነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሕግን የማስከበር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳውቀዋል።

የደብረ ኤልያስ ጥቃት

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሥላሴ ገዳም መሽገው ነበር የተባሉ 200 ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ያስታወቀው ክልሉ ውስጥ ውጥረት በነገሰበት በዚህ ወቅት ነበር።

የፀጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ባወጣው መግለጫ፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በሚገኘው የሥላሴ ገዳም “መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጽንፈኛ ኃይሎች” ባላቸው ላይ እርምጃ ተወስዷል ብሏል።

የመንግሥት ኃይሎች ይህንን ዘመቻ የጀመሩት ከግንቦት 18/2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከአራት ቀናት በላይ ለሚሆን ጊዜ በአካባቢው ከባድ ግጭት ሲካሄድ ቆይቶ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

የደብረ ኤሊያስ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ አዲስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ግን በገዳም ውስጥ ከተከሰተው ግጭት ጋር አዲስ የእምነት እንቅስቃሴ ለማስፋፋት አላማ የነበራቸው ተሳትፈዋል ብለው ነበር።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በገዳሙ ውስጥ መሽገው ነበር የተባሉት ‘የዓለም ብርሃን’ የተባለ እምነትን ለማስፋፋት አላማ የነበራቸው” ግለሰቦች ናቸው ።

የመከላከያ እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት በተባለው እርምጃ “በእስክንድር ነጋ እና በግብረ አበሮቹ ለውጊያ ሲውል የነበረ ምሽግ መሰበሩን እና 200 ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን” ተገልጿል።

እስክንድር ነጋ ቀድሞ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተባለው ፓርቲ መሥራች እና መሪ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከፓርቲው አመራርነት እና አባልነት በመልቀቅ ከባልደራስ መለየቱን በይፋ ማስታወቁ ይታወሳል።

እስክንድር በአማራ ክልል ያለው ውጥረት መጋጋሉን ተከትሎ “በአማራ ሕዝብ ላይ ይደርሳሉ ያሏቸውን በደሎች ለማስቆም እና አገሪቱ ገጥሟታል የሚሏቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም” በሚል በአገር ውስጥ እና በውጭ የሚንቀሳቀስ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

በተለያየ ከተሞች የተፈጸሙ ጥቃቶች

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን፣ ወልዲያ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ የተባሉ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የከተማዋ ነዋሪ እና ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም. ከምሽት ሦስት ሰዓት አንስቶ በታጣቂዎች የተከፈተው ተኩስ ለሰዓታት የቆየ ሲሆን፣ ቢያንስ ለሁለት ሰዎች ሞት እንዲሁም ለሌሎች ሁለት ሰዎች መጎዳት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

በወቅቱ የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በድንገት ተኩሱን የከፈቱት በተለያየ አቅጣጫ ወደ ከተማዋ የገቡ የታጠቁ ኃይሎች ናቸው ብለው ነበር።

ከዚህ በኋላም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ ዙሪያ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱ ተሰምቷል።

የታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ማክሰኞ ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም. ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ ባሉ አካባቢዎች በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል የነበረውን ግጭት “ከባድ” ሲሉ ገልጸውታል።

በዚህም የተነሳ ወደ ላሊበላ ይደረጉ የነበሩ የአየር በረራዎች ተስተጓጉለዋል።

በተጨማሪም ባለፉት ቀናት በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር እና በሌሎችም በክልሉ ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ ታጣቂዎች እና የመከላከያ ሠራዊት መጋጨታቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት ማስጠንቀቂያ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ማክሰኞ ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ “በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ ሰላም በሚያውኩ ላይ እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በሰጡት መግለጫ ላይም ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በጎንደር በሠራዊቱ አባላት ላይ ጯሂት እና ቆላድባ በተባሉ አካባቢዎች ድንገተኛ ጥቃቶች ተከፍቶባቸው እንደነበረ ተናግረዋል።

ነገር ግን በእነዚህ ድንገተኛ ጥቃቶች ስለደረሰ ጉዳትም ሆነ ስለ ክስተቱ የሰጡት ዝርዝር መረጃ ባይኖርም ሠራዊቱ ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከወጣቶች እና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት አካሂዶ ክስተቱ “በይቅርታ ተዘግቷል” ብለዋል።

ኃላፊው ጨምረውም ሐሰተኛ መረጃ እና የሠራዊቱን ስም የማጥፋት ድርጊቶች መፈጸማቸውን በማመልከት በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ጨምረውም ሠራዊቱ ባለው ኃላፊነት መሠረት ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር በታጣቂ ቡድኖች ላይ እርምጃ መውሰዱን እንደሚqጥል ገልጸዋል።

ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምን አሉ?

በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ የፀጥታ ችግር እያጋጠመ መሆኑን ጠቅሰው “ልዩነት ያለው አካል ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት ይምጣ” ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በመግለጫቸው በአመጽ ዋና መንገዶች እየተዘጉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳት ደርሷል ካሉ በኋላ “እርስ በእርስ መጠፋፋት ዘላቂ ችግር እንጂ ዘላቂ ሰላም አያመጣም” ስለማለታቸው ተዘግቧል።

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ጨምረውም “የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የተውጣጣ የኢትዮጵያውያን ነው” ማለታቸውን እና “የክልሉ ሕዝብ እየተካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ሂደት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ ይገባዋል” ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች “አሳሳቢ” እየሆኑ ምጣታቸውን አስፍረዋል።

አክለውም ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ሊኖሩ አንደሚችሉ አስቀምጠው “እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን ጠቃሚው መንገድ ሰላማዊ እና የውይይት አግባብ ነው” ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ጥያቄ

ከሚያዝያ ወር አንስቶ በተለያዩ የአማራ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ተባብሶ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች እየተካሄዱ ቆይተዋል።

በክልሉ ከዕለት ዕለት እየተስፋፋ እና አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን ቀውስ ለመቆጣጠር የክልሉ እና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ ክልሉ ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ተገዷል።

በዚህም መሠረት ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም. የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ የክልሉ መንግሥት ያለውን የፀጥታ ችግር በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አለመቻሉን በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል።

ይህም በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 14 መሠረት የፌደራል መንግሥቱ “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሠረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል” በሚለው ተግባራዊ ይሆናል።