ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአማራ ክልል መንግሥት የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ጥያቄ አቀረበ
በአማራ ክልል ክልል እየተባባሰ የመጣውን የታጣቂዎች እና የፀጥታ ኃይሎች ግጭትን ተከትሎ በክልሉ የተፈጠረውን ቀውስ እንዲቆጣጠር የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ የክልሉ መንግሥት ጠየቀ።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ተፈርሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈ ደብዳቤን አያይዞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው፣ በክልሉ ያለው የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቋል።
በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሁኔታን ስለማሳወቅ በሚል ከአማራ ክልል መንግሥት ለፌደራሉ መንግሥት ዛሬ ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም. በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ክልሉ ከባድ ችግር እንደገጠመው ጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት “የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ እንዲተገብር” የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረቡ በደብዳቤው ተገልጿል።
በክልሉ ያለው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የጠቀሰው የክልሉ መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥቱ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ለወራት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሲካሄድ የነበረው ተቃውሞ እና የታጣቂዎች ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ተባብሶ በበርካታ ቦታዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች እና ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
በዚህም ሳቢያ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ጉዳት፣ የትራንስፖርት እና መደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል እንዲሁም የቀውሱ አካባቢም እየሰፋ በርካታ ቦታዎችን አዳርሷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ቀውሱን ለመፍታት ከቀናት በፊት ከክልሉ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት አስተዳደራቸው ለውይይት ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን እንዲስቀምጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ዛሬ ርዕሰ መስተዳደሩ ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ የንግግር ጥረታቸው አለመሳካቱን አመልክቷል።
ስለዚህም ክልሉ ያጋጠመውን ቀውስ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል።
ይህንንም ተከትሎ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን እና ተግባርን በሚደነግገው ንዑስ አንቀጽ 14 መሠረት የመከላከያ ሠራዊት በክልሉ ይሰማራል።
የፌደራል መንግሥቱ “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሠረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል” ይላል።
ከዚህ በፊት በአገሪቱ እንደታየውም በክልሉ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ እና የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር ክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ አስፈላጊ ያሉትን ተግባር ሊያከናውኑ ይችላሉ።
የቀውሱን አሳሳቢ እየሆነ መሄድ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ትናንት ረቡዕ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ገልጸው፣ ችግሮችን ለመፍታት የተሻለው መንገድ ሰላማዊ የውይይት መንገድ መሆን እዳለበት አስፍረው ነበር።
በአማራ ክልል አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰው ቀውስ ከወራት በፊት የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደረጃት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነበር።
በዚህም ሳቢያ የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ማዋቀርን የተቃወሙ ነዋሪዎች እና የኃይሉ አባላት አማካይነት በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ ተቃውሞ እና ግጭቶች ያጋጠሙ ሲሆን፣ በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ታጣቂዎች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር መጋጨታቸው ተዘግቧል።
ይህንንም ተከትሎ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች ሕግ ማስከበር ባሉት እንቅስቃሴ ባለፉት ወራት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከታጣቂዎች ጋር በተካሄዱ ግጭቶች የሰው ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ተባሷል።
ከቀናት በፊት የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት በሰጠው መግለጫ በተለያዩ ስፍራዎች ታጣቂዎች በሠራዊቱ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ገልጾ፣ “በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ ሰላም በሚያውኩ" ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድስ ገልጾ ነበር።