ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች ግጭት በላሊበላ በረራ መስተጓጎሉ ተነገረ
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላሊበለ ከተማ ዙሪያ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ::
በዚህም ሳቢያ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ማክሰኞ እኩለ ቀን ላይ አካባቢ ማረፍ የነበረበት አውሮፕላን መዳረሻውን ለመቀየር ተገዷል ብለዋል።
የታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ማክሰኞ ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም. ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ ባሉ አካባቢዎች በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል የነበረውን ግጭት “ከባድ” ሲሉ ገልጸውታል።
ቢቢሲ በከተማዋ ከሚገኙ ምንጭ ለመረዳት እንደቻለው ማክሰኞ ጠዋት የመጀመሪያው አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ተነስቶ ላሊበላ አርፏል። ከላሊበላም ወደ አዲስ አበባ መንገደኞችን አሳፍሮ ተመልሷል።
ነገር ግን እኩለ ቀን 6፡50 ላይ ማረፍ የነበረበት አውሮፕላን በከተማዋ ዙሪያ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ማረፍ ባለመቻሉ ተመልሷል ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገረው ሌላኛው ነዋሪ በትናንትናው ዕለት ከእኩለ ቀን በፊት የላሊበላ ሹምሸሃ አውሮፕላን ማረፊያ በፋኖ ታጣቂዎች ሥር ገብቶ እንደነበር ገልጿል።
ነዋሪው ተጨማሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በአውሮፕላን ወደ ላሊበላ እየመጡ ነው የሚል መረጃ ከተናፈሰ በኋላ የፋኖ ታጣቂዎች አየር ማረፊያውን ስለመቆጣጠራቸው ሰምቻለሁ ብለዋል።
ቢቢሲ በላሊበላ አየር ማረፊያ ስላጋጠመው ክስተት ከተጨማሪ ገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
በላሊበላ አየር ማረፊያ ስለተከሰተው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት እና ከአየር መንገድ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልሰመረም።
ነዋሪዎች የላሊበላ አየር ማረፊያ እራሳቸውን ፋኖ ብለው በሚጠሩ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ይገኛል ይበሉ እንጂ አየር መንገዱ ነገ ወደ ላሊበላ ለሚደረጉ በረራዎች ቲኬቶችን በድረ-ገጹ አማካይነት እየሸጠ ነው።
ታጣቂዎች ከላሊበላ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የላሊበላ ሹምሸሃ አየር ማረፊያ እካባቢ ሲይዙ በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የተባል ነገር የለም።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ነዋሪ ላሊበላ ከተማ ውስጥ ማክሰኞም ሆነ ዛሬ ረቡዕ ንጋት ላይ ምንም አይነት የተለየ እንቅስቃሴ እንደሌለ ገልጸው፤ በጋሸና እና በሰቆጣ አቅጣጫዎች ግን የተኩስ ድምጽ ይሰማል ብለዋል።
በረራ ያስተጓጎለው ግጭት የተሰማው በአገር መከላከያ ሠራዊት እና እራሳቸውን ፋኖ ብለው በሚጠሩ ታጣቂዎች መካከል የሚከሰተው ግጭት እተስፋፋ በመጣበት ወቅት ነው።
በአማራ ክልል ያለው ውጥረት እና የፀጥታ ችግር ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ችግሩ በንግግር እንዲፈታ ከሳምንት በፊት በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ መነሳቱ ይታወሳል።
ትናንት ማክሰኞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ከተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ከተወጣጡ የሃይማኖት መሪዎች እና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ዛሬ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ የፀጥታ ችግር እያጋጠመ መሆኑን ጠቅሰው “ልዩነት ያለው አካል ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት ይምጣ” ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በመግለጫው በአመጽ ዋና መንገዶች እየተዘጉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳት ደርሷል ካሉ በኋላ “እርስ በእርስ መጠፋፋት ዘላቂ ችግር እንጂ ዘላቂ ሰላም አያመጣም” ስለማለታቸው ተዘግቧል።
ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በመግለጫው “የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የተውጣጣ የኢትዮጵያውያን ነው” ማለታቸውን እና “የክልሉ ሕዝብ እየተካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ሂደት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ ይገባዋል” ብለዋል።
ከወራት በፊት የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደረጃት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ እና ግጭቶች ያጋጠሙ ሲሆን፣ በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ታጣቂዎች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡ ቆይተዋል።
ትናንት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል በፋኖ ስም በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወስድኩ ነው ማለቱ ይታወሳል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ባለፈው ሳምንት የሠራዊቱ አባላት በአማራ ክልል ባሉ በሁለት ስፍራዎች ድንገተኛ ጥቃት ተፈጽሞበት እንደነበር ተናግረው “በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ ሰላም በሚያውኩ ላይ እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል።
በጎንደር፣ በቆቦ፣ በወልዲያ፣ በሸዋ ሮቢት እና በሌሎችም አካባቢዎች ባለፉት ሳምንታት ታጣቂዎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ከመጋጨታቸው በተጨማሪ ጥቃቶች ተፈጽመው ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።