ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ለመቀልበስ በማሴር ክስ ተመሰረተባቸው
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሸነፉበትን የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ በማሴር ክስ ተመሰረተባቸው።
ትራምፕ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል አሜሪካን ማጭበርበር፣ ምስክር ላይ ጫና ማሳደር እና በዜጎች መብት ላይ ማሴር የሚሉ ይገኙበታል።
ለዳግም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ መሆናቸውን ይፋ ያደረጉት የ77 ዓመቱ ፖለቲከኛ፣ "ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም" ያሉ ሲሆን በቀረበባቸው ክስ ላይም ተሳልቀዋል።
ትራምፕ በወንጀል ክስ ሲመሰረትባቸው ይህ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
ከዚህ ቀደም የአገር ምስጢር የያዙ ሰነዶችን አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ይዘዋል በሚል እንዲሁም አንዲት የልቅ ወሲብ ተዋናይን ዝም ለማሰኘት የከፈሉት ገንዘብ እንዳይታወቅ ወጪው ለንግድ ሥራ የተከፈለ አስመስለዋል የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸው ነበር።
ትራምፕ ላይ የቀረበው ሦስተኛው ክስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት 2020 ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ የተከናወኑትን እንዲሁም የትራምፕ ደጋፊዎች በካፒቶል ሂል ላይ ያደረጉትን ወረራን ተመልክቷል።
በትራምፕ ላይ የተከፈተውን ምርመራ ሲመሩ የነበሩት ጃክ ስሚዝ በካፒቶል ሂል ላይ የተፈጸመው ወረራ በአሜሪካ ዴሞክራሲ መቀመጫ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ብለዋል።
ጃክ ስሚዝ የትራምፕ የፍርድ ሂደት በፍጥነት እንዲታይ እንደሚጠይቁ እና ፕሬዝዳንቱ በቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ ሆነው እስኪገኙ ድረስ በነጻ የመገመት መብታቸው የተጠበቀ እንዲሆን አሳስበዋል።
ትራምፕ ነገ ሐሙስ ዋሽንግተን ዲሲ ባለ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ክስ ላይ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጋር ያበሩ ናቸው የተባሉ በስም ያልተጠቀሱ ስድስት ግለሰቦች ተካተዋል። አራት ጠበቆች፣ አንድ የፍትሕ ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊ እንዲሁም የፖለቲካ አማካሪ ከትራምፕ ጋር አብረዋል ተብሏል።
ክሱ ትራምፕ የፌደራል መንግሥቱ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ በማጭበርበር እና ሐቀኛ ባለመሆን እንቅፋት ሆነዋል ይላል።
በተጨማሪም የቀድሞ ፕሬዝዳንት ምክትላቸው ማይክ ፔንስ በምርጫው ጆ ባይደን ማሸነፋቸውን ማረጋገጫ እንዳይሰጡ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ይላል ትራምፕ ላይ የቀረበው ክስ።
ይህ ክስ ትራምፕ ላይ ከመመስረቱ በፊት ማይክ ፔንስን ጨምሮ የቀድሞ የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል።
በ2024 በሚካሄደው ምርጫ ሪፓብሊካንን በመወከል ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ትራምፕ፣ የቀረቡባቸው ክሶች ምርጫ ላይ ጣልቃ እንደመግባት ይቆጠራል ይላሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ደጋፊዎቻቸው ላይ የቀረቡት ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ክሶች በ1930ዎቹ የነበረን ናዚ ጀርመን፣ ሶቪዬት ኅብረት እና ሌሎች አምባገነን መንግሥታትን የሚያስታውስ ነው ብሏል የትራምፕ የምርጫ ቀስቀሳ ቡድን።