ከ‘ሂውማን ሄር እስከ ውስኪ’ እንዳይገቡ የተከለከሉበት ምክንያት ምንድን ነው?

ኢትዮጵያ ‘ቅድሚያ የማይሰጣቸው’ የሚባሉ 38 ዓይነት ዕቃዎች እንዳይገቡ ዕገዳ ጥላለች።

አስመጪዎች እነዚህን ምርቶች ወደ አገር ቤት ለማስገባት የሚያስችላቸው ‘ኤልሲ’ እንዳይሰጣቸው መንግሥት ያገደው፣ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመግታት በሚል ነው ።

ቅድሚያ የማይሰጣቸው አሊያም የቅንጦት ከሚባሉት ዕቃዎች መካከል ተሽከርካሪዎች፣ የምግብ ምርቶች፣ የቤት እና የቢሮ ዕቃዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች እና የአልኮል መጠጦች ይገኙበታል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፃፈው ደብዳቤ፣ እነዚህን ዕቃዎች ወደ አገር ቤት ለሚያስገቡ አስመጪዎች ፈቃድ እንዳይሰጣቸው አዟል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት እንደሆነና አስፈላጊ የሚባሉ እንደ መድኃኒት፣ የግብርና ጥሬ ዕቃዎች፣ ለአገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ዕቃዎችን ለማስመጣት በቂ የውጭ ምንዛሪ እንዲኖር በማለት ነው።

እነዚህን ዕቃዎች በብዛት የሚያስገቡ አስመጪዎች መመሪያው እንዲነሳ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አማካኝነት ‘ይግባኝ’ እያሉ እንደሆነም ቢቢሲ ሰምቷል።

ይህ ትዕዛዝ ከመውጣቱ በፊት ኤልሲ የተከፈተላቸው ዕቃዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ መመሪያው ይፈቅዳል።

ለመሆኑ ኤልሲ ማለት ምን ማለት ነው? መንግሥት ይህን መመሪያ በማውጣቱ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ያተርፋል? የአስመጪዎቹ ይግባኝስ የት ደረሰ?

‘ሂውማን ሄር’

ከውጭ እንዳይገቡ ዕግድ ከተጣለባቸው ምርቶች መካከል አንዱና የማኅበራዊ ሚድያ መነጋገሪያ የነበረው ሰው ሠራሽ ፀጉር ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋጋው እየናረ የኪስ መለካኪያ መሆን እየጀመረ የመጣው ‘ሂውማን ሄር’ ከባንክ በወጣ ኤልሲ አገር ቤት እንዳይዘልቅ መመሪያ ወጥቶበታል።

ስሜን አትጥቀሱ ያለን አንድ ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ ፀጉር የሚያስመጣ ነጋዴ፣ ይህንን ምርት ከዚህ ቀደም በሕጋዊ መንገድ ያስመጣ እንደነበር ይናገራል።

አስመጪው “የሚከፈለው ቀረጥ፣ ገበያው ላይ የሚሸጠው እና የዕቃው ዋጋ ሲወዳደር ስለማይመጣጠን አብዛኛው ነጋዴ ከቀረጥ ውጪ ነው የሚያስገባው” ብሏል።

“የሚቀረጠው እጅግ ውድ ስለሆነ ሁሉም ነጋዴ ዕቃውን በመንገደኛ ሻንጣ ይዞ ነበር የሚገባው። ይህ አሁንም አለ፤ ነገር ግን ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር ቀንሷል። በሕጋዊ መንገድ የሚገባ ሂዩማን ሄር የለም።”

ምንጫችን፤ አሁን ኢትዮጵያ ገበያ ላይ ያለው በኮንትሮባንድ የሚገባ ‘ሲንቴቲክ’ ፀጉር ስለሆነ ይህንን ለመቆጣጠር ታስቦ የወጣ ሕግ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለው።

ነገር ግን አዲሱን መመሪያ ተከትሎ የሰው ሠራሽ ፀጉር ዋጋ በእጥፍ እንዲጨምር፣ የአቅርቦት ችግር እንዲፈጠርና ነጋዴዎች ጫና ላይ እንዲወድቁ ምክንያት መሆኑን ይገልጻል።

“አዎ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል። ሙሉ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ መላክ አቁሚያለሁ። ቀረጥ ከፍ አድርጎ ማስገባት ፍትሐዊ አይደለም። ከዚህ ቀደም 400 ግራም ፀጉር 120 ዶላር ነበር፤ አሁን ግን አምስት/ስድስት [የታሸገ] ፀጉር ይዞ የሄደ ሰው ሦስት እጥፍ [360 ዶላር] ቀረጥ ይከፍላል። ስለዚህ አያዋጣም።”

አዲሱን ዕቀባ ተከትሎ ሂውማን ሄር በአማካይ ዋጋ 15 ሺህ ብር ጭማሪ ማሳየቱን ነጋዴዎች ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም 18 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው ፀጉር፣ አሁን ዋጋው ወደ 29 ሺህ ብር ከፍ ብሏል።

ሂውማን ሄር ብቻ ሳይሆን ቸኮሌት፣ ትምባሆ፣ የታሸጉ ጭማቂዎች፣ ውሃ እና ለስላሳ መጠጦች፣ የተጠበሰ ድንች፣ የአልኮል መጠጦች፣ እንዲሁም ‘ሜክ አፕ’ የመሳሰሉ የመዋቢያ ዕቃዎች ከተከለከሉት 38 የዕቃ ዝርዝሮች መካከል ይገኛሉ።

የውጭ ምንዛሪ እጥረት

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ፤ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ አቅም አስፈላጊ የሚባሉ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና መድኃኒት ለመግዛት የሚሆን ብቻ ነው ሲል ይተነብያል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ አገር ቤት በአስመጪዎች እንዳይገቡ ከተከለከሉት ምርቶች በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ማትረፍ ይቻላል ይላል።

የአሜሪካ የውጭ ግብርና አገልግሎት እንደሚለው ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 18 ቢሊዮን ዶላር አውጥታ ከውጭ ዕቃ አስገብታለች።

በዚህም ምክንያት በገቢ እና በወጪ [ኢምፖርት-ኤክስፖርት] መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል።

ኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር የተሰኘው የምጣኔ ሃብት ተቋም ካንትሪ ኢኮኖሚስት የሆኑት ቴዎድሮስ መኮንን ይህ ሕግ የወጣበት ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ገበያው አደጋ ስለተደቀነበት ነው ይላሉ።

“በተለይ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ የክፍያ ሚዛን [ባላንስ ኦፍ ፔይመንት] ተዛብቷል። ኮቪድና የሰሜኑ ጦርነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው። ወደ አገር ቤት የሚመጡ ቱሪስቶች፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች እንዲሁም ከውጭ አገር የሚላክ ገንዘብ [ሬሚታንስ] ቅናሽ አሳይቶ ነበር።”

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው በጦርነቱ ምክንያት ‘ካፒታል አካውንት’ ተብለው የሚጠሩት እርዳታ፣ ብድር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፤ አሉታዊ ተፅዕኖ ደርሶባቸዋል ይላሉ።

“በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።”

መመሪያው በዋናነት የዶላር ዋጋ በባንክ እና በጥቁር ገበያው ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ተብሎ የወጣ እንደሆነ ተንታኙ ይናገራሉ።

አክለው አስፈላጊ ያልሆኑ ዕቃዎች ላይ የሚውለው ወጪ፤ በተለይ ደግሞ አንዳንድ ዕቃዎች የሚገቡት ከትይዩ ገበያ [ብላክ ማርኬት] ከሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ስለሆነ ያንን ፍላጎት ለመቀነስ ታስቦ የተደረገ ነው ይላሉ።

ክልከላው በጥናት የተደገፈ ነው የሚለው ብሔራዊ ባንክ፤ በ38ቱ ምርቶች ላይ የተላለፈው የኤልሲ ዕግድ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ መሆኑን አሳውቋል።

ምርቶቹ ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መበራከት ምክንያቶች መሆናቸውም ተገልጧል።

ኤልሲ መከልከል መፍትሔ ይሆናል?

ኤልሲ ማለት ‘ሌተር ኦፍ ክሬዲት’ ማለት “ዓለም አቀፍ ንግድን በቀላሉ ለማሳለጥ የሚያስችል መንገድ ነው” ይላሉ ቴዎድሮስ መኮንን።

አክለው ሲያብራሩ፤ “ከውጭ አገር ዕቃውን የሚሸጠው እና አስመጪው በባንኮች በኩል እርስ በርስ የሚስማሙበት፣ ዕቃው መላኩን እና መድረሱን የሚያረጋግጡበት” እንደሆነ ያስረዳሉ።

“አንድ ሰው ዕቃ ማስመጣት ሲፈልግ ባንክ ይሄድና ‘ይህን ዕቃ ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ እፈልጋለሁ’ ይልና የሚያስመጣበት ፈቃድ [ኢምፖርት ፐርሚት] ይሰጠውና ከዚያ ኤልሲ ይከፈታል።”

ኤልሲ፤ ዕቃ ለማስመጣት [ኢምፖርት] ብቸኛው መንገድ እንዳልሆነና ሌሎችም መንገዶች [ለምሳሌ ቲቲ የተሰኘ ቅፅ] እንዳለ ባሙያው ይናገራሉ።

አሁን መንግሥት ያወጣው ሕግ ለእነዚህ ዕቃዎች ኤልሲ እንዳይከፈት ያዛል። ስለዚህ እነዚህን ዕቃዎች በባንክ በኩል ማስመጣት አይቻልም ማለት ነው።

በእርግጥ ይህ እርምጃ በአገሪቱ ውስጥ ላለውን የውጭ ምንዛሪ ችግር የሚፈለገውን ውጤት ያስገኛል?

“አንድን ትልቅ ሚስማር ለመምታት ለሚስማሩ የሚመጥን መዶሻ መጠቀም ይኖርብሃል” በማለት የአገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ችግር ትልቅ ሆኖ ሳለ ከቁጥር የማይገባ እርምጃ መውሰዱ እውነተኛ መፍትሔ አይሆንም ይላሉ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው አየለ ገላን (ዶ/ር)።

በኢነርጂ፣ ንግድ፣ ግብርና እና በቱሪዝም ፖሊሲዎች ላይ የጥናት ፅሑፎች ያቀረቡት ምሑሩ በአሁን ወቅት በኩዌት የሳይንስ ምርምር ተቋም ተመራማሪ ኢኮኖሚስት ናቸው።

አየለ (ዶ/ር)፤ እነዚህ ምርቶች ከውጭ እንዳይገቡ የውጭ ምንዛሪ መከልከል ወይም ‘ሌተር ኦፍ ክሬዲት’ ላይ ገደብ መጣል የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቋቋም የሚረዳ እምርጃ ነው ብለው አያምኑም።

“መደረግ ያለበትን እና ለአገር የሚጠቅመውን ሳያውቁት ቀርተው አይደለም፤ ነገር ግን ዳር ዳር እያሉ ያልፉታል። ምክንያቱም እዚያው ውስጥ የመንግሥትን እጅ አሥረው እንደፈለጉ የሚያደርጉ ስላሉ ነው። ስለዚህ መሠረቱ ከተነካ የትላልቆቹ [ጥቅም] ይነካል” ይላሉ ተመራማሪው።

የኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር ኢኮኖሚስቱ ቴዎድሮስ በበኩላቸው በዋናው እና ጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ለማጥበብ ካሉት ሁለት መፍትሔዎች አንደኛው ቁጥጥርን ማጥበቅ እንደሆነ ይናገራሉ።

የመጀመሪያውና ዋነኛው የሚሉት መፍትሔ ግን “የውጭ ምንዛሪው በትክክለኛ መንገድ እንዲሠራ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችን መቅረፅ ነው።”

“ቁጥጥርን ማጥበቅ ዘላቂ የሆነ ለውጥ አያመጣም። ለምሳሌ በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ ሱቆችን መንግሥት ሲዘጋ ለተወሰነ ጊዜ የውጭ ምንዛሪው ይወርድና ከዋና ገበያ ጋር ይቀራረባል። ነገር ግን ትንሽ ቆይቶ ቁጥጥሩ ሲላላ ተመልሶ ከፍ ይላል።”

አሁን የተከለከሉት ምርቶች ወደ አገሪቱ ከሚገቡት ምርቶች ዋጋ አንጻር እዚህ ግባ የሚባሉ አይደለም የሚሉት አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከተፈቀደላቸው የውጭ ምንዛሪ አቅም በላይ የሚያወጡ ምርቶች ሲገቡ መንግሥት እርምጃ ባለመውሰዱ ኢትዮጵያ ማግኘት የነበረባትን የውጭ ምንዛሪ አጥታለች ይላሉ።

ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ያለውን ችግር መፍታት የሚቻለው “ችግሩ ከመሠረቱ ሲደርቅ ነው" የሚሉት ምሑሩ፣ ይህ እንዳይነካ የተፈለገበት ምክንያት “በዚህ ውስጥ ያለው አስመጪው ነጋዴ ብቻ ሳይሆን፣ ዶላር ሰብሰበው ውጭ እንዲቀር የሚሠሩ ነጋዴዎችና ፖለቲከኞች ስላሉ ነው” ሲሉ ይወቅሳሉ።

ሁለቱም ያነገራናቸው የምጣኔ ሃብት ሙያተኞች በአዲሱ መመሪያ ዘላቂነት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።

አየለ ገላን (ዶ/ር)፤ ሌላ የተሻለ የአጭር ጊዜ አማራጭ አለ ባይ ናቸው። አንደኛው አማራጭ ‘ዱዋል ኤክስቼንጅ ሬት’ [ባለሁለት የምንዛሬ ተመን] ነው ይላሉ። ይህ ምን ማለት ነው?

እንደ ምሑሩ ገለጻ ‘ዱዋል ኤክስቼንጅ ሬት’ ማለት መንግሥት በጥቁር ገበያው እንደ ነጋዴው በመሳተፍ የምንዛሪ እጥረትን ለመቀነስ የሚሞክርበት መንገድ ነው።

“ነጋዴው በውጭ አገራት በድፍረት በጥቁር ገበያው የሚሳተፈው ስለሚያዋጣው ነው” የሚሉት አየለ (ዶ/ር)፤ “መንግሥትም ነጋዴው የሚያደርገውን ለምን እራሱ አያደርግም?” ሲሉ በጥያቄ መልክ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን በማስረገጥ ይናገራሉ።

የጎረቤት አገር ኬንያን ልምድ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት ተመራማሪው፣ ማንኛውም ሰው ወደ ኬንያ ሲገባ የፈለገውን ያክል ዶላር መጠን መግዛት እንደሚችል ይገልጣሉ።

“መንግሥት ከነጋዴው በላይ ብር አለው። ነጋዴው በዓለም አገራት እየዞረ ሰብስቦ ውጭ የሚያስቀረውን ዶላር መንግሥት በጥቁር ገበያ በመሣተፍ ወደ አገር ቤት እንዲገባ ማድረግ ይችላል” የሚል የመፍትሔ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ።

ቴዎድሮስ መኮንን ደግሞ አዲሱ መመሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ምርቶችን የሚያስገቡ ሰዎች የበለጠ ትርፍ እንዲያጋብሱ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።

“ምርቶች በኮንትሮባንድ ሊገቡ ይችላሉ። አንድ ቁጥጥር ሲደረግ ሙሉ በሙሉ የማስፈፀም አቅም ስለማይኖር ክፍተቶች ይፈጠራሉ። ጥቂት ሰዎች እነዚህን ክፍተቶች ተጠቅመው ብዙ ያተርፋሉ። ቁጥጥሩን ማስፈፀም ከተቻለ ስኬታማ ይሆናል። ነገር ግን ተቋማዊ ክፍተቶች ስለሚኖሩ የተወሰኑ ግለሰቦች በጣም ተጠቃሚ ይሆናሉ።”

እንደ ቴዎድሮስ እምነት ይህንን ችግር በዘላቂነት መቅረፍ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንደኛው ትክክለኛ ፖሊሲ መከተል አስፈላጊ ነው መሆኑን በመጥቀስ፣ “የምናስገባውን ገቢና የምናወጣውን ወጪ ማመጣጠን አለብን” ይላሉ።

“መንግሥት በራሱ አንድ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ ነው። ብዙ ፕሮጀክቶች አሉበት። እነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ ብክነት ይታያል። በአገር ውስጥ ከሚመረተው ይልቅ ከውጭ የሚመጣው ይበልጣል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ የሚለወጥበት መንገድ መኖር አለበት።”