ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሲኤንኤን ጋዜጠኛ የቀረበላትን ጥያቄ ባለመቀበሏ ከኢራኑ መሪ ጋር የነበራትን ቃለ መጠይቅ ሰረዘች
የኢራን ዝርያ ያላት አንጋፋዋ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፑር ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ጋር በኒው ዮርክ ልታደርግ በነበረው ቆይታ ላይ ፀጉሯን እንድትሸፍን በመጠየቋ ቃለ መጠይቁን ሰረዘች።
አማንፑር ከዚህ ቀደም የነበሩ የኢራን መሪዎችን ከኢራን ውጪ ቃለ መጠይቅ በምታደርግበት ወቅት ፀጉሯን እንድትሸፍን ጥያቄ ቀርቦላት እንደማያውቅም ተናግራለች።
የፕሬዝዳንቱ ረዳት ይህ ጥያቄ አሁን የቀረበላት “በወቅት በኢራን ባለው ሁኔታ” ምክንያት እንደሆነ እንዳሳወቋትም ተናገራለች።
በኢራን ከቀናት በፊት ማህሳ አሚኒ የተሰኘች ሴት ፀጉርሽን አልሸፈንሽም በሚል በሃይማኖታዊ ፖሊሶች ቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አመጽ ተቀጣጥሏል።
ከሕዝባዊ ተቃውሞው ጋር በተያያዘም እስካሁን 17 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የ22 ዓመቷ አሚኒ “የሥነ-ምግባር” ፖሊሶች ከያዛት በኋላ ራሷን ስታ ስትወድቅ የሚያሳይ በደኅንነት ካሜራ የተቀረጸ ቪዲዮ በመላው ዓለም ተሰራጭቷል።
ይህንንም ተከትሎ ወደ ሆስፒታል ብትወሰድም ሕይወቷ ሳይተርፍ ቀርቷል።
ፖሊሶቹ የአሚኒን ጭንቅላት በዱላ መተዋል ብሎም ጭንቅላቷን ከመኪናቸው ጋር አጋጭተዋል የሚል ክስ እየቀረበባቸው ነው።
ነገር ግን ፖሊስ ይህንን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ እንደሌለ እና “በድንገተኛ የልብ ሕመም” የህልፈቷ ምክንያት እንደሆነ ግለጿል።
ሰባተኛ ቀኑን የያዘው ሕዝባዊ ተቃውሞው እስካሁን በ80 የኢራን ከተሞች ተስፋፍቷል።
ፕሬዘዳንት ራይሲ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤን ለመታደም ነው ወደ ኒው ዮርክ ያመሩት።
አማንፑር ከፕሬዚዳንቱ ረዳቶች በአንዱ ፀጉሯን እንድትሸፍን ጥያቄ እስከሚቀርብላት ድረስ ቃለ መጠይቁን ለማድረግ ዝግጁ እንደነበረች ተናግራለች።
በትዊተር ገጿ ላይ “የጭንቅላት መሸፈኛን በተመለከተ ሕግ ወይም ባህል በሌለበት ኒው ዮርክ ውስጥ ነው ጥያቄው የቀረበው” ስትል ተናግራለች።
የፕሬዝዳንቱ ረዳት ፀጉሯን የማትሸፍን ከሆነ ቃለ መጠይቁ እንደማይደረግ ግልጽ እንዳደረጉላት እና ይህም “የአክብሮት ጉዳይ ነው” በሚል እንደተገለጸላት ተናግራለች።
አማንፑር እና የፕሮግራሟ አዘጋጆች “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እና ያልተጠበቀ ሁኔታ” በማለት የጠራችውን ሁኔታ በመቃወም ቃለ ምልልሱን ሰርዘው ጥለው ወጥተዋል።
አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ፀጉሯን ሳትሸፍን ፕሬዝዳንቱ ሊቀመጡበት ተዘጋጅቶ የነበረ ባዶ ወንበር ፊት ለፊት ተቀምጣ የሚያሳይ ፎቶ ለጥፋለች።
ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ራይሲ በነሐሴ አዲስ ሕግ ፈርመው አጽድቀዋል።
ከሕጎቹ መካከልም የደኅንነት ካሜራዎችን ማስተዋወቅ እና የማይሸፋፈኑ ሴቶችን “ለመቅጣት ወይም ለመምክር” የሚያስችለው ይገኝበታል።
የአገሪቱን የሂጃብ ሕግጋት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ብሎም ያለ ሂጃብ ማንኛውንም ዓይነት ቪዲዮ የሚለቅ ሰው ላይ የእስር ቅጣትን የሚጥል ሕግ ነው።
በኢራን ተቃውሞዎቹን ተከትሎ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን መዝጋት ተጀምሯል።
ኢራናዊያን ሴቶች ፀጉራቸውን በመቁረጥ እና ሂጃባቸውን በማቃጠል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ እየለጠፉ ይገኛሉ።