በኢራን በርካታ ሴቶች ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ሂጃባቸውን አቃጠሉ

በኢራን የሂጃብ ህግን በመተላለፏ በሞራል ደንብ አስከባሪዎች በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ለሞት የበቃችውን ግለሰብ ተከትሎ በርካቶች ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።

በዛሬውም ዕለት በርካታ ሴቶች ሂጃባቸውን ያቃጠሉ ሲሆን ለአምስተኛ ቀንም ተቃውሞው ቀጥሏል።

ተቃውሞውም ከዋናዋ ከተማዋ ቴህራን ወደ ሌሎች ከተሞችም ተዛምቷል።

ተቃውሞውንም ተከትሎ ሁለት ወንድ ተቃዋሚዎች በጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን የመብት ተሟጋቾች አስታውቀዋል።

ግድያው የተፈጸመው በሰሜን ምዕራብ በኡርሚያና በፒራንሻህር ግዛቶች ነው።

በደቡብ ክልል ሺራዝ ግዛትም የፖሊስ ረዳት ተገድሏል ተብሏል።

ማህሳ አሚኒ ሂጃብ አልለበሽም በሚል በሞራል ደንብ አስከባሪዎች ድብደባ ተፈጽሞባት ለሞት በቅታለች ተብሏል።

 የማህሳን ሞት ተከትሎም በርካቶች የሂጃብ ህጎችን እና የሞራል ደንብ አስከባሪዎችን በመቃወም በተቀሰቀሰ ሁከት ቢያንስ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል ተብሎ ይታመናል።

የ22 ዓመቷ ኩርዳዊት ማህሳ ለሶስት ቀናት ያህል በጽኑ ህሙማን ክፍል ከቆየች በኋላ ህይወቷ አልፏል።

ቴህራን ውስጥ ከወንድሟ ጋር በነበረችበት ወቅት ነው የሞራል ደንብ አስከባሪዎች የሂጃብ ህግ ጥሰሻል በሚል በቁጥጥር ስር ያዋሏት።

በህጉ መሰረት ሴቶች ሂጃብ መጠምጠም እንዲሁም ክርናቸውንና እግራቸውን የሚሸፍን ሰፋ ያለ ልብስ መልበስ ይጠበቅባቸዋል። እስር ቤት ከገባች በኋላም ራሷን ስታ ፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ገብታ ነበር። ፖሊስ የማህሳን ጭንቅላት በዱላ እንደበደባትና መኪና ውስጥም እንዳጋጯት ሪፖርት መደረጉን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ናዳ አል ነሺፍ ተናግረዋል።

ፖሊስ በበኩሉ ተደብድባ ነው የሞተችው የሚለውን የካደ ሲሆን “ድንገተኛ የልብ ድካም” እንዳጋጠማት ተናግሯል። ነገር ግን ቤተሰቦቿ ጤናማ እንደነበረች ተናግረዋል።