ከአሜሪካ ተባርሮ በሕዋ ምርምር እና በሚሳዔል ግንባታ ቻይና ተፎካካሪ እንድትሆን ያስቻለው ሳይንቲስት

ሺያን ሼሰን ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሺያን ሼሰን የሮኬት ማስወንጨፍ ላይ መሠረታዊ የሆነ ምርምር ሰርቷል

ቻይናዊው ተመራማሪ አንድ ሳይሆን ሁለት ኃያላን አገራት ጨረቃን እንዲረግጡ አስችሏል።

ታሪክ ስሙን የሚያነሳው፣ የሚያወድሰው ግን ነጥሎ በአንድ አገር ብቻ ነው።

ቻይና ሻንግሃይ ውስጥ 700 ቅርሳ ቅርሶችን የያዘ እና በአንድ በስሙ መታሰቢያ የሆነ ሙዚየም ይገኛል።

ሺያን ሼሰን "የሕዝብ ሳይንቲስት" እየተባለ የሚጠራ ሲሆን፣ በሻንግሃይ የሚገኘው ሙዚየም መታሰቢያም ለእርሱ የተሰጠ ተመራማሪ ነው።

ሳይንቲስት ሺያን ሼሰን የቻይና የሚሳዔል፣ የሕዋ ፕሮግራም አባትም በመባል ይታወቃል።

የሺያን ጥናት ቻይና ወደ ሕዋ ያመጠቀችውን የመጀመሪያ ሮኬት እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዋ አካል የሆኑትን ሚሳዔሎች እንድትገናበ አስችሏታል።

ሼያን ሼሰን በቻይና ብሔራዊ ጀግና ነው። በአሜሪካ ደግሞ ስሙን ደግመው ማንሳት የማይፈለጉት ሊቅ ነው።

ነገር ግን ከአስር ዓመታት በላይ በተማረበት እና በሠራበት ለሌላ ልዕለ ኃያል አገር ያበረከተው ጉልህ አስተዋፅዖ በጭራሽ አይታወስም።

የእርሱ ጉዳይ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ጉዳይ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ተከትሎ መነጋገርያ ሆኖ ነበር።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ሳምንት አስተዳደሩ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ወይም ወሳኝ በሆኑ መስኮች የሚማሩትን የቻይና ተማሪዎችን ቪዛ እንደሚሰርዝ አስታውቀዋል።

የሺያን ሼሰን የቀደመ ሕይወት

ሺያን ሼሰን የተወለደው የቻይና የመጨረሻው ንጉሣዊ አስተዳደር በሪፐብሊክ ሊተካ ሲል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1911 ነው።

ሁለቱም ወላጆቻቸው በሚገባ የተማሩ ሲሆን፣ አባቱ በጃፓን ከሠሩ በኋላ የቻይናን ብሔራዊ የትምህርት ሥርዓት ቀርፀዋል።

ሺያን ተሰጥኦ እንደነበረው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ግልጽ ነበር።

እናም በመጨረሻ በሻንግሃይ ጂያኦ ቶንግ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ውጤት መመረቁን ተከትሎ በወቅቱ ብርቅ እና ድንቅ የነበረውን በአሜሪካ በሚገኘው የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም (ኤምአይቲ) የነፃ ትምህርት ዕድል አገኘ።

እንደ አውሮፓዊያኑ በ1935 ሽቅርቅር ያለው ቻይናዊ ቦስተን ደረሰ።

በሰሜን ጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስ ጄስፐርሰን እንዳሉት ሺያን መጤ ጠል እና ዘረኝነት አጋጥሞት ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን "ቻይና በመሠረታዊ መንገዶች በጉልህ እየተቀየረች ነው የሚል የተስፋ እና እምነት ነበረው" እና እውቀቱን ከሚያከብሩ ሰዎች መካከል እንደሚገኝ ጥርጥር አልነበረውም።

ዶ/ር ዊልያም ፒክሪንግ፣ ዶ/ር ቴዎዶር ቮን ካርማን እና ዶ/ር ፍራንክ ጄ ማሊና በ1960 የተነሱት ፎቶግራፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ዊልያም ፒክሪንግ፣ ዶ/ር ቴዎዶር ቮን ካርማን እና ዶ/ር ፍራንክ ጄ ማሊና እአአ በ1960

ከኤምአይቲ፣ ሺያን ወደ ካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (ካልቴክ) ተዛወረ።

በወቅቱ በጣም ተደማጭነት ከነበራቸው ኤሮናውቲካል መሐንዲሶች በአንዱ፣ በሃንጋሪያዊው ስደተኛ ቴዎዶር ቮን ካርማን ስር ሆኖ ተማረ።

እዚያም ሺያን 'ሱሳይድ ስኳድ' በመባል የሚታወቁት አነስተኛ የፈጠራ ሰዎች ቡድን ቁልፍ አባል ከሆነው ከሌላ ታዋቂ ሳይንቲስት ፍራንክ ማሊና ጋር ቢሮ ተጋርቷል።

ቡድኑ ሱሳይድ ስኳድ የተባለው በመማሪያ ካምፓሳቸው ውስጥ ሮኬት ለመገንባት በመሞከሩ ነበር።

የስኬፕ ፍሮም አርዝ ደራሲ ፍራሰር ማክዶናልድ ሌሎች ምርምሮቻቸው ደግሞ በቀላሉ የሚፈነዱ እና አደጋ የሚያደርሱ ነበሩ ይላሉ።

አክለውም በእርግጥ የሞተ የለም ብለዋል።

አንድ ቀን ሺያን ከማሊና እና ከሌሎች የቡድኑ አባላት ጋር የተወሳሰበ የሂሳብ ቀመር ላይ ውይይት ከማድረግ አልፎ ብዙም ሳይቆይ በሮኬት ላይ ምርምርን በማድረግ የቡድኑ ወሳኝ አካል ሆነ።

በዚያን ጊዜ የሮኬት ሳይንስ "የቀውሶች እና የሕልመኞች" መስክ እንደሆነ ነበር የሚታሰበው ይላሉ ማክዶናልድ።

ማንም ሰው በቁም ነገር አይመለከተውም፤ የትኛውም የሂሳብ ዝንባሌ ያለው መሐንዲስ ይህ የወደፊት ሳይንስ ነው በማለት ስሙን አደጋ ላይ መጣል አይፈልግም።

ይህ ግን ይህ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመርን ተከትሎ በፍጥነት ተለወጠ።

በጦርነት ውስጥ ያለ ቡድን

የ'ሱሳይድ ስኳድ' ቡድን አባላት የአሜሪካ መከላከያ ኃይል አዛዦችን ቀልብ መሳብ ቻሉ።

ከዚያም አውሮፕላኖች በክንፋቸው ላይ በተገጠመላቸው ሞተር ታግዘው ከአጭር ማኮብኮቢያ ላይ ለመነሳት እና ለመብረር የሚያደርጉት ምርመር ላይ ገንዘብ ተመድቦላቸው መሥራት ቀጠሉ።

በ1943 በቴዎዶር ቮን ካርማን ዳይሬክተርነት የጄት ፕሮፐልሽን ላብ (ጄፒኤል) እንዲቋቋም የአሜሪካ መከላከያ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ሺያን ከፍራንክ ማሊና ጋር የፕሮጀክቱ ሳንባ እና ልብ ነበሩ።

በጦርነቱ ማብቂያ ላይ በጄት ፕሮፑልሽን ላይ ከዓለም ግንባር ቀደም ባለሙያዎች አንዱ ሆነ።

እናም ከቴዎዶር ቮን ካርማን ጋር ወደ ጀርመን ለልዩ ተልዕኮ ተላከ። በወቅቱ ጊዜያዊ የሌተና ኮሎኔልነት ማዕረግ ተሰጥቶት ነበር።

ግባቸው የጀርመን ዋና የሮኬት ሳይንቲስት ቨርንሄር ቮን ብራውንን ጨምሮ የናዚ መሐንዲሶችን ቃለ መጠይቅ ማድረግ ነበር።

አሜሪካ ጀርመኖች የሚያውቁትን በሙሉ በትክክል ማወቅ ፈልጋለች።

ነገር ግን በአስርት ዓመቱ መገባደጃ ላይ የሺያን ሼሰን ጀብድ የተሞላበት የምርምር ሥራ በድንገት ቆመ።

እናም ሕይወቱ ሌላ አቅጣጫ ያዘ።

ማኦ የቻይና ሕዝቦች ሪፐብሊክ ሲያውጁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና ሊቀመንበር ማኦ እአአ ጥቅምት 1 1949 የኮሚኒስት ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መመሥረቱን አወጀ

የቻይና ሊቀመንበር ማኦ በ1949 የኮሚኒስት ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መመሥረቱን አወጀ።

እናም ቻይናውያን በፍጥነት በአሜሪካ ውስጥ "ክፉዎች" ተደርገው መታየት ጀመሩ ይላል ክሪስ ጄስፐርሰን።

"ስለዚህ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከቻይና ጋር የነበረን የአጭር ጊዜ ፍቅር ደመና አጥልቶበት ቻይናን ማንቋሸሽ እና መሳደብ ጀመርን።"

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አዲሱ የጄፒኤል ዳይሬክተር በቤተ ሙከራ ውስጥ ሰላይ እንዳለ ስለተሰማው ስለተወሰኑ የሠራተኞች አባላት ያለውን ጥርጣሬ ለኤፍቢአይ አሳወቀ።

ፍሬሰር ማክዶናልድ "ሁሉም ቻይናውያን ወይም አይሁዳውያን መሆናቸውን አስተውያለሁ" ይላል።

ወቅቱ ቀዝቃዛው ጦርነት የተጋጋለበት ነበር። እና ፀረ-ኮሚኒስት የሆኑት ማካርቲ ዘመን በደጅ ነበር።

በዚህ ወቅት ውስጥ ነበር ኤፍቢአይ ሺያን፣ ፍራንክ ማሊና እና ሌሎችም ኮሚኒስቶች ናቸው ብሎ የከሰሰው፤ ለብሔራዊ ደኅንነትም አስጊ ናቸው ተባሉ።

ሺያን ሼሰን የተከሰሰው እአአ በ1938 የአሜሪካ ኮሚኒስት ፓርቲ ባወጣው ሰነድ ላይ ኤፍቢአይ የፓሳዴና ኮሚኒስት ፓርቲ ስብሰባ ነው ብሎ በጠረጠረው ላይ ተገኝቷል የሚል ነው።

ሺያን የፓርቲ አባል መሆኑን ቢክድም፣ አዲስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍራንክ ማሊና ጋር በተመሳሳይ ጊዜ በ1938 በአባልነት ተቀላቅሏል።

ሺያን ሼሰን በ1950 ከጠበቃው ግራንት ኩፐር ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሺያን ሼሰን በ1950 ከጠበቃው ግራንት ኩፐር ጋር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ግን የግድ ማርክሲስት አያደርገውም። በዚህ ጊዜ ኮሚኒስት መሆን የፀረ ዘረኝነት መግለጫ ነበር ይላል ፍሬሰር ማክዶናልድ።

ቡድኑ የፋሺዝምን ስጋት እና በአሜሪካ ያለውን የዘረኝነት አስከፊነት ለማጉላት ፈልጎ ነበር።

ለምሳሌ በአካባቢው የሚገኘውን የፓሳዴና የመዋኛ ገንዳ መለያየትን በመቃወም ዘመቻ ያካሂዱ፣ እና የኮሚኒስት ስብሰባዎቻቸውን ለመወያየት ይጠቀሙበት ነበር።

በካሊፎርኒያ ስቴት ፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ዙዩዌ ዋንግ ዢያን አሜሪካ በነበረበት ጊዜ ቻይናን እንደሰለለ ወይም የስለላ ወኪል እንደነበረ ምንም ዓይነት መረጃ የለም ይላሉ።

ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት የሰጠውን የደኅንነት ይለፍ ወረቀቱን ነጥቆ የቁም እስረኛ አደረገው።

ቴዎዶር ቮን ካርማንን ጨምሮ የካልቴክ ባልደረቦች የሺያንን ንፁህነት በመጥቀስ ለመንግሥት የተማጽኖ ደብዳቤ ጽፈው የነበረ ቢሆንም ውትወታቸው መና ቀረ።

እአአ በ1955 ሺያን አምስት ዓመታትን በቤት ውስጥ በቁም እስር ካሳለፈ በኋላ ፕሬዝዳንት አይዘንአወር እሱን ወደ ቻይና ለማስባረር ወሰኑ።

ሳይንቲስቱ ከሚስቱ እና ከሁለቱ አሜሪካ የተወለዱ ልጆቹ ጋር በጀልባ ተሳፍሮ አሜሪካን ተሰናበተ።

በስፍራው ለነበሩት ጋዜጠኞች ዳግም አሜሪካ እንደማይረግጥ ተናግሯል። የገባውንም ቃል ጠበቀ።

ጋዜጠኛው እና ፀሐፊው ቲያንዩ ፋንግ "በአሜሪካ ውስጥ በጣም ታዋቂ ከሆኑት ሳይንቲስቶች አንዱ ነበር። ብዙ አበርክቷል እና ብዙ ማበርከት ይችል ነበር። ስለዚህ ውርደት ብቻ ሳይሆን የመከዳት ስሜትም ጭምር ነው የተፈጠረበት።"

ሺያን ቻይና ሲደርስ የጀግና አቀባበል ተደረገለት። ነገር ግን ወዲያውኑ ወደ ቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አልገባም። ታሪኩ እንከን የለሽ አልነበረም።

የቻይና መንኮራኩር በጨረቃ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና መንኮራኩር በጨረቃ ላይ

ሚስቱ የታዋቂ ፓለቲከኛ እና ባለፀጋ ልጅ ነበረች።

እርሱ ከአሜሪካ ከፍታው እና ዝናው እስኪወርድ ድረስ አሜሪካ ውስጥ በደስታ ይኖሩ ነበር።

የአሜሪካ ዜግነት ለማግኘትም ማመልከቻ አስገብቶ ነበር።

በመጨረሻ በ1958 የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አባል ሆኖ በአገዛዙ ቀኝ ጎን ለመቆም ቃል ገባ።

ቻይና በደረሰ ጊዜ ስለ ሮኬት ሳይንስ ብዙም ግንዛቤ አልነበረም።

ከ15 ዓመታት በኋላ ግን የመጀመሪያውን የቻይና ሳተላይት ወደ ሕዋ ስትመጥቅ በበላይነት መርቷል።

ባለፉት አሥርተ ዓመታት አዲስ የሳይንስ ሊቃውንትን አሠልጥኖ ሥራው ለቻይና የጨረቃ ሃሰሳ ፕሮግራም መሠረት ጥሏል።

የሚገርመው፣ ሺያን በቻይና እንዲሠራ የረዳው የሚሳዔል ፕሮግራም ወደ አሜሪካ ተወንጭፏል።

በ1991 የባሕረ ሰላጤው ጦርነት የሺያን [ሲልክ ወርም ተብለው የተጠሩ] ሚሳዔሎች በአሜሪካውያን ላይ ተተኩሰዋል ይላል ፍሬሰር ማክዶናልድ።

በ2016 ደግሞ በየመን በሁቲ አማፂያን በዩኤስኤስ ሜሶን ላይ ተወንጭፏል።

"ስለዚህ ይህ ያልተለመደ አዙሪት አለው። አሜሪካ ይህን ምሁር አስወጥታለች እና እርሱ ደግሞ መልሶ አሳዳጇ ሆኖ መጥቷል።"

አሜሪካ በአገር ውስጥ ኮሚኒዝም ላይ ጠንካራ አቋም በመያዟ ከአገር እንዲወጣ ያደረገችውን "ከዋነኛ የኮሚኒስት ተቀናቃኞቻቸው አንዱ የራሳቸውን ሚሳዔሎች እና የሕዋ መርሃ ግብር የሚያዘጋጁበት ዘዴን በማዘጋጀት ረዳ። የተለየ የጂኦፖለቲካዊ ስህተት ነው" ብሏል።

የአሜሪካ የባሕር ኃይል የቀድሞ አዛዥ ዳን ኪምቦል፣ በኋላም የሮኬት ፕሮፑልሲንግ ኩባንያ ኤሮጄት ኃላፊ በአንድ ወቅት "ይህቺ አገር እስካሁን ካደረገችው ሁሉ የማይረባው የሞኝ ተግባር ነው" ብሏል።