"ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አፍሪካ የራሷን ሃብት ተጠቅማ ዕጣ ፈንታዋን የመወሰን ተምሳሌት ነው" ፕሬዚዳንት ሩቶ

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ "አፍሪካ የራሷን ሃብት ተጠቅማ ዕጣ ፈንታዋን መወሰን እንደምትችል ብቃት እንዳላት ማረጋገጫ ተምሳሌት" ነው ሲሉ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ተናገሩ።

ማክሰኞ ጳጉሜ 4/ 2017 ዓ.ም. የተካሄደውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ ሥርዓትን ለመታደም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ተገኝተው የነበሩት ሩቶ ይህንን ያሉት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ነው።

14 ዓመታትን የፈጀው እና አምስት ሚሊዮን ዶላር እንደወጣበት የሚነገረውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ ወጪ በኢትዮጵያውያን መሸፈኑን በዚህ መልዕክታቸው የጠቀሱት ሩቶ፤ ሕዳሴ "ከመሠረተ ልማት ፕሮጀክት በላይ ነው" ብለውታል።

ከ5, 450 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሕዳሴ "በአፍሪካ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንዲሁም የአህጉሪቱን የራስ አቅም እንዲሁም ዕድገት ማሳያ ነው" ሲሉ አሞካሽተውታል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ታሪካዊ ምርቃትን ከሌሎች መሪዎች ጋር ሆነው በመታደማቸው ክብር እንደተሰማቸው ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ለዚህ አስደናቂ ስኬት "ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለኬንያም ትልቅ ተስፋን እንደሚፈነጥቅ በዚሁ መልዕክታቸው አስፍረዋል።

መሪው የኬንያን የአይሲቲ ማዕከሎች፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ለመደገፍ እንዲሁም "ተወዳዳሪነታችንን በማጠናከር የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ዘላቂነት ያለው ዕድገት እንዲመጣ" ከኢትዮጵያ ጋር የኃይል ግዥ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።

ኬንያ ተጨማሪ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምጣት ዕቅድ መያዟን ከጥቂት ወራት በፊት የኬንያ የኢነርጂ እና ፔትሮሊየም ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ማስታወቁ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ኬንያ በባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ከኢትዮጵያ 3.63 ቢሊዮን ብር በሚያወጣ ወጪ ኃይል መግዛቷን ደይሊ ኔሽን አስነብቧል።ከዚያ ቀደም በነበረው ዓመት 1.32 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጋ እንደነበር የጠቀሰው ዘገባው ይህም በሦስት እጥፍ ማደጉን አስገንዝቧል።

ኬንያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መውሰድ የጀመረችው በአውሮፓውያኑ 2022፣ በ25 ዓመታት ስምምነት ነው። ስምምነቱ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት 200 ሜጋ ዋት የምትገዛ እንደሆነ ገልጾ በቀጣዮቹ ዓመታት ወደ 400 ሜጋ ዋት እንደሚያድግ አስፍሯል።

ኬንያ ከኢትዮጵያ የምትገዛው የኤሌክትሪክ ኃይል 6.5 የአሜሪካ ሳንቲም በኪሎ ዋት ሲሆን፣ ይህም ርካሽ ከሚባሉት መካከል እንደሆነ ይኸው ዘገባ ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ እና ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመገበያየት የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙት ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት ነበር።

ለምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ከፍተኛ ስፍራ ያለውና 1.3 ቢሊዮን ዶላር የፈጀው የዚህ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታን ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት ገንብታ መጨረሷ ይታወሳል።

አገራቱን የሚያገናኘው የኤሌክትሪክ መስመር 500 ኪሎ ቮልት እና ከኢትዮጵያ በኩል 412 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ በአጠቃላይ ከ1 ሺህ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ነው።

ሩቶ ሌላኛው በዚህ የኤክስ ገጻቸው ያሰፈሩት መልዕክት "የትኛውም አገር ለውጥ የሚያመጣ ሃብት የመገንባት ዕድል ሊነፈግ አይገባም፤ ምክንያቱም እነዚህ ከጊዜ በኋላ የጋራ የብልጽግና ምንጮች ናቸው" ብለዋል።

የናይልን 55.ሚሊዮን ኪዩቢክ ውሃን የምትጠቀመው እና ለዓመታት ኢትዮጵያ ግድብ እንዳትገነባ ስትከላከል ለዘመናት የቆየችው ግብፅ የግድቡን ግንባታ ከጅምሩ ተቃውማዋለች።

በሕዳሴ ግድብ የተካሄዱ አምስት የውሃ ሙሌቶችም ከግብፅ በኩል ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎችን ያስከተሉ ነበሩ።

ሩቶ ይሄንን ድል "ሰናከብር በናይል ተፋሰስ አገራት መካከል ያለውን የተለያየ አመለካቶች እንገነዘባለን። ኬንያ የጋራ ውሃን ፍትሃዊ መንገድ መጠቀምን ትደግፋለች" ብለዋል።

የኬንያው መሪ በዚህም መልዕክታቸው ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የሦስትዮሽ ውይይታቸውን በቅን መንፈስ እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ስትወተውት የቆየችው ግብፅ፣ የግድቡን ምርቃት ተከትሎ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አስገብታለች።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ለፀጥታው ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ግንባታዋ "የዓለም አቀፍ ሕግጋትን እና የምሥራቅ አባይ ተፋሰስን የሚመሩትን ደንቦችን የሚጥስ የአንድ ወገን ፕሮጀክት ነው" ብለዋል።

ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለንግግሮቹ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።

ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመውና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ ብላ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርኅ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ትቃወማለች።

ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሃዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።

ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ብትቆይም ከግብፅ በኩል ይህንን የመቀበል አዝማሚያ አልታየም።

ከኬንያው ፕሬዝዳንት በተጨማሪ በምርቃቱ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት፣ የጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌህ እንዲሁም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ተገኝተዋል።

እንዲሁም የኢስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ሚሶ ድላሚኒ፣ የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር አሞር ሞትሊ እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ታድመዋል።