ኢትዮጵያ በግብፅ ላይ የበላይነት የተቀዳጀችበት ግዙፉ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ

    • ፀሐፊ, ፋሩክ ቾቲያ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ኒውስ
    • ፀሐፊ, የማነ ናግሽ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ትግርኛ

ከአስር ዓመታት በላይ በዲፕሎማሲያዊ መድረክ በኢትዮጵያ የበላይነት የተያዘባት ግብፅ፣ የቅኝ ግዛት ውል የሰጣት በአባይ ወንዝ ላይ በብቸኝነት የመጠቀም መብት አብቅቶ ኢትዮጵያ ከዓለማችን ግዙፍ ግድቦች መካከል አንዱ የሆነውን የሕዳሴ ግድብ በይፋ ልታስመርቅ ነው።

በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የሕዳሴ ግድብ 5 ቢሊዮን ዶላር የወጣበት ሲሆን፣ የሚይዘው የውሃ መጠን የሚሸፍነው አካባቢ ደግሞ ከአዲስ አበባ እስከ ሻሸመኔ ይደርሳል።

ይህ ግድብ በብሔር ግጭት በምትናጠው አገር ውስጥ ሕዝቧን በአንድ መንፈስ በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ሞሰስ ክሪስፐስ ኦኬሎ "ኢትዮጵያውያን እንጀራን እንዴት መበላት አንዳለበት ላይስማሙ ይችላሉ፤ በግድቡ ላይ ግን ይስማማሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። የሚመለከቱትም በወንዝ መሀል እንደቆመ የኮንክሪት ክምር ሳይሆን ለስኬታቸው እንደቆመ ሐውልት ነው። ግንባታው በ2003 ዓ.ም. ሲጀመር ግድቡን በገንዘብ ለመደገፍ በርካቶች ቃል ገብተዋል።"

ኦኬሎ "መንግሥት ከተለያዩ ተቋማት እና ሠራተኞቻቸው በቦንድ ሽያጭ ገንዘብ ሰብስቧል። ስለዚህ ይህ ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ነው የሚለውን ስሜት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል፤ የግድቡ መመረቅ ደግሞ ለአገሪቷ ትልቅ ኩራት ነው" ብለዋል።

ተንታኙ አክለውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአፍሪካ ግዙፉ የውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ሲሆን፣ ለሕዝቧ የኤሌትሪክ ፍላጎት ብቻ የሚውል ብቻ ሳይሆን አገሪቱን "የኃይል የበላይነት" ይሰጣታል። እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ገቢዋን እንደሚያሳድግ ተስፋ ሰንቋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ኬንያ እና ጂቡቲ ላሉ የጎረቤት አገራት የምትሸጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሳደግ አቅዳ የነበረች ሲሆን፣ ቀይ ባሕርን አቋርጦ እንደ ሳዑዲ አረቢያ ላሉ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራትም ለመሸጥ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የመገንባት ዕቅድ አላት ብለዋል።

ለግብፃውያን ግን ግድቡ ከኢትዮጵያን ተስፋ እና ምኞት በተቃራኒው የቆመ ነው።

ግድቡ ወደ አገራቸው የሚደርሰውን የውሃ ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ በማድረግ የውሃ እጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል የሚል ስጋት አላቸው።

በግብፅ ካይሮ ዩኒቨርሲቲ ጂኦሎጂስት የሆኑት ፕሮፌሰር አባስ ሻራኪ "93 በመቶ የሚሆነው የግብፅ ግዛት በረሃ ነው፤ ምንም ዓይነት ሕዝብ አይኖርበትም። ሁላችንም፣ 107 ሚሊዮን ሰዎች በአባይ ወንዝ ላይ ኑሯችንን መሥርተናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም "የግብፅ ሥልጣኔ የተመሠረተው በአባይ ላይ ነው፤ አባይ ሕይወታችን ነው።"

ምሁሩ በግድቡ ምክንያት "የውሃ እጥረት" በግብፅ ሊባባስ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

ፕሮፌሰር ሻራኪ "በአብዛኛው ወደ ግብፅ ይፈስ የነበረውን፣ 64 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ነው የሚይዘው። ይህ ለእኛ ትልቅ ኪሳራ ነው። በአማካኝ ዓመታዊ ድርሻችን 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው። ሌላ የውሃ ምንጭ የለንም፤ ያለን የአባይ ወንዝ ብቻ ነው።"

አክለውም ሕዳሴ ግድን "የሚይዘው የውሃ መጠን በቻይና ውስጥ ካለው ስሪ ጎርጅስ ግድብ በእጥፍ ይበልጣል። ይህ ግድብ በዓለም ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ትልቁ ግድብ ነው።"

በሕዳሴ ጉዳይ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ የነበሩት ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ኢትዮጵያ ከግብፅ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና አልፎ ተርፎም የጦርነት ዛቻ ቢሰነዘርባትም፣ ለልማታዊ ፍላጎቷ አስፈላጊ በመሆኑ ግድቡን ለመገንባት በያዘችው ዕቅድ ቀጥላበታለች ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማያገኙት 60 በመቶ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዳረስን ያካትታል።

ይሁን እንጂ የአገሪቱ ሰፊ ተራራማ አካባቢዎች ላይ ትልልቅ የማስተላለፊያ መስመሮችን መገንባት ስለሚያስፈልግ ሥራው ቀላል እንደማይሆን ጠቁመዋል።

ፕሮፌሰር ሻራኪ እንዳሉት ብሉ ናይል "ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ" ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት "የተናጠል" እርምጃ ወስዳለች።

ይህ ማድረግ የቻለችውም አገሪቱን ለረዥም ጊዜ ያስተዳደሩት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን እንዲወገዱ ምክንያት የሆነው የአረብ አብዮት በግብፅ በመቀስቀሱ ነው።

"ግብፅ ያለ ፕሬዝዳንት በጣም መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ነበረች፣ የአገሪቱ ጦር ደግሞ በውስጥ ጉዳዮች ተጠምዶ ነበር" ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ የሰሜን አፍሪካዋ አገር አሁን በዓለም ትልቁን የውሃ ማጣሪያ በመገንባት እንዲሁም ከ5,000 በላይ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር አማራጭ የውሃ ምንጮችን ለማግኘት እርምጃ ወስዳለች።

ግብፅ በግብርና ዘርፏ ላይ ለውጥ እንድታደርግም ተገድዳ ነበር።

ለመብቀል ከፍተኛ ውሃ የሚፈልገውን ሩዝ የምትዘራበትን መሬት ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር ወደ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መቀነሷን ትናገራለች።

ፕሮፌሰር ሻራኪ "ኢትዮጵያ ወደ ግብፅ ይፈስ የነበረውን 64 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የምትገድብ ከሆነ ጉዳት አያስከትልም?" ሲሉ በመጠየቅ፣ ኢትዮጵያ ግድቡ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ላይ ተፅዕኖ እንደማያደርስ የምትናገረውን አጣጥለውታል።

ፈቅ አህመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ግብፅ የተወሰነ የውሃ መጠን በአስተማማኝነት ታገኝበት ወደነበረው ወደ ቀድሞው ሁኔታ እንደማትመለስ፣ ነገር ግን "የውሃ መለቀቅ እና የግድቡ ደኅንነትን በሚመለከት ሁልጊዜ ለመነጋገር ክፍት ናት" ብለዋል።

መቀመጫውን በኬንያ ያደረገው የሳሃን የምርምር ማዕከል ተንታኝ የሆነው ራሺድ አብዲ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በወቅቱ የቅኝ ገዢ የነበረችው ብሪታኒያ በ1920ዎቹ ለግብፅ 80 በመቶ የሚሆነውን የናይል ውሃ ዋስትና ለመስጠት ያደረገችውን ​​ስምምነት ማብቃቱን ያበሰረ ነው ብለዋል።

ራሺድ "ብሪታንያ ይህን ያደረገችው ግብፅ የአውሮፓ መግቢያ የሆነውን የስዊዝ ካናልን ለመቆጣጠር ስትራቴጂካዊ አገር በመሆኗ እርሷን ለማረጋጋት እና የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው።"

"ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን አቅሟን ስታሳይ፣ ግብፅ ደግሞ ያላት ዕድል ቀንሷል። በናይል ወንዝ ላይ የነበራትን የተለየ ጥቅም አጥታለች" ብለዋል።

ኦኬሎ "የፖለቲካ ብልሃት" የታየበት ሲሉ በገለጹት እርምጃ፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ በ2003 ዓ.ም. "ፕሮጀክት ኤክስ" ብለው የጠሩትን ግድብ ለመገንባት ማቀዳቸውን ተከትሎ ግብፅ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ምክንያት "የበላይነት ሥልጣኗን" እንድታጣ ሆኗል።

"ግብፅ እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ እንዳይሰጡ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። ይህም የኢትዮጵያን መንግሥት ቁርጠኝነት በማጠናከር፣ ከዜጎቿ ገንዘብ ለማሰባሰብ ትልቅ እንቅስቃሴ ጀምራለች።"

አክለውም "ስለዚህ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአገር ውስጥ ምንጮች ገንዘብ አግኝታለች፤ እንዲሁም ከኢጋድ (የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት) ትንሽ መዋጮ አግኝታለች። ከሌሎች ምንጮችም ገንዘብ አግኝታ ቢሆን ይህ ጎላ ብሎ አይነገርም" ብለዋል።

የግብፅ ጠንካራ አጋር የሆነችው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ለግድቡ "የገንዘብ ድጋፍ" ማድረጓን እና ወደ አባይ ወንዝ የሚፈሰውን ውሃ "በተጨባጭ" በመቀነሱ የግብፅን ስጋት አስተጋብተዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡ የተሠራው ከኢትዮጵያውያን በተሰበሰበ ገንዘብ መሆኑን በመግለጽ የፕሬዝዳንቱን ንግግር "ውሸት" በማለት ውድቅ አድርጋለች።

ኦኬሎ እንደተናገሩት ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው በግድቡ ላይ ስምምነት እንዲደረስ ጥረት አድርገው ነበር።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለግብፅ ማድላታቸውን በተመለከቱ ጊዜ ከድርድሩ ወጥተዋል።

ኦኬሎ "ትራምፕ ትንሽ ተሰምቷቸው ነበር። የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማግኘት ይፈልጉ ነበር። ግን ዐቢይ ኖቤል መሸለሙ ብቻ ሳይሆን ለትራምፕም አደራዳሪነት ዕድል አልሰጠም" ብለዋል።

ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ይመረቃል ተብሎ ከሚጠበቀው የሕዳሴ ግድብ በፊት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ መንግሥታቸው በግድቡ ላይ ያለውን ተቃውሞ የውሃ ደኅንነት ጉዳይ "ቀይ መስመር" ነው በማለት ገልጸዋል።

እንዲሁም ግድቡ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ላይ "የኅልውና ስጋት" ደቅኗል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ፕሮፌሰር ሻራኪ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት የመግጠም ዕድል የላትም ይላሉ።

"ወንድሞቻችን ናቸው። ከተመሳሳይ ውሃ ጠጥተናል። ናይል የሚመጣው ከእነርሱ ነው" በማለት ግብፅ አለመግባባቱን በንግግር እንደምትፈታው ይናገራሉ።

ፈቅ አሕመድ በበኩላቸው ግብፅ ግድቡን በቦምብ ልትመታ ብትሞክር ለራሷ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጎረቤት ለሆነችው ሱዳን "ራስን ማጥፋት" ነው የሚሆነው ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ውሃው በኃይል በመፍሰስ ለሁለቱ አገራት "አውዳሚ" ይሆናል በማለት ነው።

ግብፃዊው ጂኦሎጂስት ደግሞ ኢትዮጵያ ግድቡን በተለይ የግብፅ ስትራቴጂካዊ አጋር የሆነችው ሱዳን ላይ "ወታደራዊ አቅሟን" ለማሳየት ትጠቀምበታለች ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

"በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ውጥረት ወይንም ግጭት የሚኖር ከሆነ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ወይንም አውሮፕላን ሳትጠቀም በዚህ ግድብ ተጠቅማ ሱዳንን ልታወድማት ትችላለች" ይላሉ።

አክለውም ሕዳሴ "አዲስ የመሬት መንቀጥቀት ሥርዓት" ሊቀሰቅስ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይጠቅሳሉ።

ፕሮፌሰር ሻራኪ "64 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የምታጠራቅም ከሆነ፣ ያ ማለት የእሳተ ገሞራ አለቶች ባሉበት አካባቢ 64 ቢሊዮን ቶን ክብደት ትፈጥራለህ፤ በርካታ የመሬት መሰንጠቆች፣ እንዲሁም የዓለማችን ትልቁን ሸለቆ፣ የምሥራቅ አፍሪካን ሸለቆ እና ደግሞ ንቁ የሆነውን ሸለቆ ትፈጥራለህ" ይላሉ።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የግብፅ ስጋት መሠረተ ቢስ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያሳዩ በመግለጽ ያጣጣለች ሲሆን፣ ግድቡም ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ከሆነ አካባቢ እጅጉን የራቀ ነው ብላለች።

ኢትዮጵያ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠናቅቃ ስታስመርቅ እና ፊቷን በቀይ ባሕር ላይ ወደብ ወደማግኘት ስታዞር ግብፃውያን ግን ስሜታቸው እንደ ደፈረሰ ይቆያል።

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችው ኤርትራ በ1983 ዓ.ም. ነጻነቷን ማግኘቷን ተከትሎ ነው።

ሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ ውይይታቸው ላይ የቀይ ባሕር ጉዳይ "ነገ የሚታረም ስህተት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

"የባሕር በር ጉዳይ ልናፍርበት የሚገባው ጉዳይ አይደለም። የዓለም አተያይ ግልጽ ነው። ግዙፍ አገር ሆኖ ያለ ወደብ የተቀመጠ የለም። ይህ ደግሞ በድርድር መፈታት አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።

ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግንኙነታቸው ተሻሽሎ ነበር።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅትም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ የህወሓት ኃይሎችን ወግታለች።

አሁን ግን ግንኙነታቸው ሻክሮ የጦርነት ድባብ ሰፍኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀይባሕር ጉዳይ በቅርቡ ይታረማል ማለታቸውንም ተከትሎ ኤርትራ "ግዴለሽ የጦርነት ዛቻ" ነው በማለት ኢትዮጵያን ከስሳለች።

ኦኬሎ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ ላይ ከፊት ሆነው የታዩት ኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ፊታቸውን ወደ ቀይ ባሕር አዙረዋል።

አክለውም "ኢትዮጵያ ባሉት ፈታኝ ነገሮች ውስጥ ሁሉ ሆና ግድቡን ገንብታዋለች" ብለዋል።

"አሁን የባሕር በር ማግኘት እና የባሕር ኃይል መገንባት ትፈልጋለች። ነገር ግን እንዴት አድርጋ እንደምታገኝ ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን እንደ ታላቅ ሕዝብ ነው የሚያዩት፤ ወደብ አልባ ሆኖ ታላቅ የሆነ አገር ደግሞ የለም" ብለዋል።