ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እና የፈጠረው ተስፋ
- ፀሐፊ, ቃልኪዳን ይበልጣል
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ኒውስ
ለወጣቶቹ የሜካኒካል ኢንጂነሮች ቀድሞ ቀልባቸውን የሚሰርቀው የግድቡ ግንባታ የሚካሄድበት ስፍራ ግዝፈት ነው።
አሁን በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የአፍሪካ ግዙፉ የሃይድሮ ኤሌትሪክ ግድብ በ2003 ዓ.ም. የመሠረት ሥራውን ለማስጀመር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየቆፈሩ ነበር።
ሞገስ የሺዋስ በ2003 ዓ.ም. በሙያው በቂ ልምድ ለማግኘት ተስፋ ሰንቆ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሲደርስ ገና የ27 ዓመት ወጣት ነበር።
የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ አገሩን እንደሚቀይር ተስፋ ቢያደርግም የእርሱንም ሕይወት ቀይሮታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማክሰኞ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በይፋ ሲመረቅ ለአገሪቱ የኤሌትሪክ ብርሃን መስጠት ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ኃይል ያቀርባል ብለዋል።
1.78 ኪሎ ሜትር የተዘረጋው ይህ ግዙፍ ግድብ 145 ሜትር ከፍታ አለው።
11 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትሮች ካሉት ኮንክሪት የተገነባው የሕዳሴ ግድብ፣ ንጋት ተብሎ የተሰየመ ግዙፍ ሐይቅ ፈጥሯል።
በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ይህ ግዙፍ ግድብ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ብዙ አለመግባባቶችን ፈጥሯል።
በተለይ ከግብፅ ጋር ውጥረት የፈጠረው ይህ ግድብ፣ ወደ ግጭት የመግባባት አዝማሚያ የታየባቸው ምልልሶችም ተሰምተውበት ያውቃል።
ለኢትዮጵያውያን ይህ የሕዳሴ ግድብ የኩራት ምንጭ፣ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመለካከት በዓለም መድረክ በጽኑ መሠረት ላይ እንድትቆም የሚያደረጋት ነው።
አሁን 40 ዓመት የሞላው ሞገስ ደግሞ "የዚህ አካል በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል" ይላል።
"ቀን በቀን የግድቡን ዕድገት ማየት ጥልቅ እርካታ የሚሰጥ ነበር።ወደዚህ ሥራ ፈልጌ ነው የመጣሁት፤ ነገር ግን ከጊዜ ብዛት ሥራ የመሆን ስሜቱ እየጠፋ መጣ። ከፕሮጀክቱ ጋር ቅርበትን አዳበርኩ ልክ እንደራሴ መጻዒ ዕድል የእርሱም ያስጨንቀኝ ጀመር።"
ይህ ግን ተግዳሮትም ነበሩት።
"ከቤተሰብ ለረዥም ጊዜ ተለያይቶ መቆየት ፈታኝ ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሞገስ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ወደሚኖሩት ቤተሰቦቹ በዓመት ሁለት ሦስቴ ይሄዳል።
ግድቡ የሚገኝበት ሩቅ ስፍራ፣ አንዳንዴ 45 ዲግሪ ሴንቴግሬድ የሚደርሰው ከፍተኛ ሙቀት እንዲሁም ረዥም የሥራ ሰዓት ፈተናዎች መደቀናቸው አልቀረም።
"እንሠራ የነበረው ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ነበር፤ ለምሳ የአንድ ሰዓት እረፍት ብቻ ነበረን። ከዚያ ለምሽት ተረኞች እናስረክባለን። ምክንያቱም ግንባታው ሳይቋረጥ ነው መቀጠል ያለበት" ይላል ሞገስ።
የእርሱ ኃላፊነት የግንባታው ሂደት በአግባቡ መከናወኑን መከታተል እና የግንባታ መስፈርቶችን ያሟላ መሆኑን ማረጋገጥ ነው።
በፖለቲካ አለመግባባት እና በብሔር ፖለቲካ ለምትናጠው ኢትዮጵያ ይህ የሕዳሴ ግድብ ሕዝቦቿን በእኩል ስሜት እና መንፈስ አንድ አድርጎ ያነሳሳ ፕሮጀክት ነው።
እንደ ኢንጂነር ሞገስ ያሉ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በቀጥታ ቢሳተፉም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ የላባቸውን ጥሪት ውጤት አዋጥተዋል።
ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት፣ ስጦታ በመስጠት የሚችለውን አድርጓል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሺንግተን የግድቡን ግንባታ በገንዘብ ደግፋለች ሲሉ ቢናገሩም አዲስ አበባ ግን ከኢትዮጵያውያን ውጭ የማንም ሰባራ ሳንቲም በግድቡ ላይ አልዋለም ስትል አስተባብላለች።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ቅዳሜ ዕለት የሕዳሴ ግድቡን ምርቃት አስመልከተው በሰጡት መግለጫ ላይ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 233 ቢሊየን ብር ለግንባታው ወጥቶበታል ብለዋል።
አቶ ሞገስ ከአጠቃላይ ወጪው ውስጥ 223 ቢሊየን ብር ወይም 91 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘ ነውም ብለዋል።
ቀሪው 9 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከሕዝብ ተሳትፎ የተገኘ ገንዘብ መሆኑን በመጥቀስ 18.9 ቢሊየን ብር በኢትዮጵያውያን እና በትውልደ ኢትዮጵያዊን የቦንድ ሽያጭ፣1.6 ቢሊየን ብር በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያን የቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ፣ 3.2 ቢሊየን ብር ከስጦታ ተሰብስቧል ብለዋል።
ከደሞዛቸው በመቀነስ ለግድቡ ካዋጡ ሰዎች መካከል አንዱ ኪሮስ አስፋው ነው።
ነርስ የሆነው ኪሮስ የትግራይ ክልል ነዋሪ ሲሆን፣ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ከ2003 ዓ.ም አንስቶ በየዓመቱ ቦንድ ገዝቷል።
ከ100 ጊዜ በላይ ቦንድ ገዝቻለሁ የሚለው ኪሮስ፣ በትግራይ የባንክ እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎት ተቋርጦ በነበረበት የሁለት ዓመቱ ጦርነት ጊዜ ብቻ ማቋረጡን ይናገራል።
ኪሮስ ለግንባታው የሚሆን ገንዘብ ያለማቋረጥ ለማዋጣት የተነሳሳው የግድቡ ግንባታን ያስጀመሩት "የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በንግግራቸው የተከሉበት መነሳሳት" መሆኑን ያስታውሳል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መላው ኢትዮጵያውያን የግድቡን ግንባታ ለማገዝ መረባረብ እንዳለባቸው ተናግረው ነበር።
የአምስት ልጆች አባት የሆነው ኪሮስ "እስከ መጨረሻው ድረስ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገባሁ" ይላል።
አሁን ግድቡ ኃይል እንዲያመነጭ የተገጠሙለት ተርባይኖች ሁሉ ሥራ የጀመሩት የሕዳሴው ግድብ የሚያመጣው አስተዋጽኦ ላይ ሁሉም ዓይኑን ጥሏል።
ይህ ግድብ አገሪቱ ከምታመነጨው ግማሽ በላይ የሆነ የኤሌትሪክ ኃይል፣ 5100 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሲሆን፣ ሚሊዮኖችን የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ታሳቢ ተደርጓል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌትሪክ ተጠቃሚ አይደለም።
"በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ መቀነስ የምንፈልገው ይህንን ነው። በአውሮፓውያኑ 2030 ቢያንስ 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝባችን የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው የምንፈልገው" ብለዋል።
የ35 ዓመቷ ጌታነሽ ጋቢሶ የምትኖረው ከሐዋሳ በቅርብ ርቀት በሚገኝ አላሙራ የገጠር መንደር ውስጥ ነው።
የእርሷ ሕይወት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከሚኖሩ በርካታ ዜጎች ሕይወት ጋር ይመስላል።
እርሷ እና ባለቤቷ ከሦስት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩበት ከሐዋሳ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው በጭቃ የተሰራው ደሳሳ ጎጆ የኤሌትሪክ ብርሃን አይቶ አያውቅም።
ምግብ ለማብሰል በአካባቢዋ ከሚገኝ ደን እንጨት ትለቅማለች።
ለመብራት የምትጠቀመው ደግሞ በጋዝ የሚሠራ ኩራዝ ነው።
ባለቤቷ ገረምሳ ጋልቻ የቤተሰቡ ጤንነት ያሳስበዋል።
"እሷ ትልልቅ እና ውብ ዓይኖች ነበሯት።ይህንን ሁሉ ዓመት በጭስ ስትጨናበስ ዓይኖቿ ሟሙ። አሁን ዝም ብለው ያለቅሳሉ" ይላል።
"ጭሱ ልጆቼን ቢያፍንብኝ ምን እንደማደርግ አላውቅም" ሲል ጭንቀቱን ለቢቢሲ አጋርቷል።
ጌታነሽ በሚመሽበት ወቅት የባሏን ሞባይል ተጠቅማ እንደምትንቀሳቀስ በመግለጽ፣ "መብራት ገብቶ ቀን ወጥቶልን" ስትል እንደምታልም ትናገራለች።
"ቤቴ በብርሃን ሲጥለቀለቅ ማየት እፈልጋለሁ። አሁን ሌሎች የኤሌትሪክ መሳሪያዎች አያጓጉኝም። ሲመሽ ተግ የማደርገው የኤሌትሪክ ብርሃን ብቻ ነው የምፈልገው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
እርሷም ሆነች ባለቤቷ የሕዳሴ ግድቡ የሚያመጣውን ልዩነት ለማየት ጓግተዋል። የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ግን ከብሔራዊ የኃይል ማከፋፈያ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የኃይል ማስተላለፊያ ለመዘርጋት ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ይናገራሉ።
ትንንሽ ከተሞችን እና መንደሮችን የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በአስር ሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የኤሌትሪክ መስመር ዝርጋታ ይጠይቃል።
ነገር ግን ይላል ኢንጂነሩ ሞገስ በሕዳሴ ግድብ የተመረተው የኤሌትሪክ ኃይል ለውጥ ማምጣት ይችላል።
ሞገስ የሕዳሴ ግድቡ ሥራ ላይ እያለ አንድ ልጅ ወልዷል።
"የሚገባኝን ያህል አጠገቡ አለመሆኔን ሳስብ የሚረብሽ ስሜት ይሰማኛል" ያለው ሞገስ "ነገር ግን ባበረከትኩት አስተዋጽኦ የተነሳ መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን አውቃለሁ፤ ስለዚህም ሲያድግ ይህንን ስነግረው በኩራት ነው" ብሏል።