ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እንድሪያስ እሸቴ: ዋርካው ወደቀ
- ፀሐፊ, ሃሚድ አ. ይመር
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ አማርኛ
እንድሪያስ እሸቴ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ፖለቲካ እና ምሁራዊ ክበብ ውስጥ የሚታወቅ ስም ነው።
ፈላስፋነታቸው፣ ሰው ወዳድነታቸው፣ አንደበተ ርትዑነታቸው፣ ጎበዝ መምህርነታቸው፣ ጨዋታ አዋቂ እና ተረበኛ መሆናቸው በወዳጆቻቸው እና በቀድሞ ተማሪዎቻቸው ይነሳላቸዋል።
እንድሪያስ ሲጃራ ይወዳሉ፤ ጥቁር ቢትልስ ሹራብ ይለብሳሉ፤ ሙዚቃ ያዳምጣሉ። በተለይ ለጃዝ፣ ሞዛርት እና ሪቻርድ ቫግነር ስስ ልብ አላቸው።
የምሁርነት ጥግ፣ የአስተማሪነት መለኪያ የሚያደርጓቸው ያሉትን ያህል፤ ስማቸውን በጥሩ የማያነሱ ጥቂት የማይባሉ ነቃፊ እና ተቺዎችንም አላጡም።
ወዳጆቻቸውም ሆኑ ነቃፊዎቻቸው ግን ፕሮፈሰር እንድሪያስ ብሩህ አዕምሮ እንደነበራቸው አይክዱም።
እንድሪያስ የአራት ኪሎ ልጅ ናቸው። ከ79 ዓመታት በፊት በ1937 ከእናታቸው መንበረ ገብረማርያም እና አባታቸው እሸቴ ተሰማ በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ።
“ሶስት ቤተሰቦች ናቸው ያሳደጉኝ ማለት እችላለሁ” የሚሉት ፕሮፌሰሩ ወላጆቻቸው፣ አጎታቸው አቶ ጀማነህ አላብሶ እና የፓንክረስትን ቤተሰብ ያነሳሉ።
እንድሪያስ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት መሐል አራት ኪሎ በሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነው።
ከዓመታት በፊት ከሸገር ኤፍ ኤም ጋዜጠኛዋ መዓዛ ብሩጋር በነበራቸው ዘለግ ያለ ቆይታ፤ “ምኒልክ የአራዳ ትምህርት ቤት ነው። እኔም ያደኩት አራት ኪሎ ነው” ሲሉ የቀድሞ ተማሪ ቤታቸውን ገልጸውታል።
እንድሪያስ በአገረ አሜሪካ ከሚገኙ ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎች ፍልስፍና ተምረዋል፤ አስተምረዋል፤ ተመራምረዋል።
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኋላ ላይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል። ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዝዳንትነትም መርተዋል። የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ኃይለማርያም ደሳለኝን አማክረዋል።
የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት በማርቀቁ ሂደትም ውስጥ ጉልህ ሚና ነበራቸው።
እንድሪያስ ሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ የነበራቸው ሚና እንደ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ያሉ የሕገ መንግሥቱን ቀራጮች መርዳት እንደነበር ይገልጻሉ። “ያን ማድረግ ትልቅ ክብር ነበር” የሚሉት እንድሪያስ፤ “ሁለተኛ እድል ይኖረናል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር” ይላሉ።
ፕሮፌሰር ዳግማዊ ውብሸት የእንድሪያስ የረዥም ጊዜ ወዳጅ ነው። በፔንሲልቬኒያ ዩኒቨርሲቲ የስነጽሁፍ መምህር የሆነው ዳግማዊ ከ15 ዓመታት በፊት ከፕሮፌሰር እንድሪያስ ጋር ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር።
“በህይወቴ አፈራኋቸው ከምላቸው ምርጥ ጓደኞች መካከል አንዱ እንድሪያስ ነው” የሚለው ዳግማዊ፤ “እንድሪያስ ከሁሉም በላይ በጣም የፍቅር ሰው ነው። ፍቅርም ያሳይሃል፣ ደግሞም የነጻነት ሰው ስለሆነ የራስህን ነጻነት ይዘህ እንድትራመድ መንገድ የሚከፍትልህ ሰው ነው” ሲል የወዳጁን ሰብዕና ያስታውሳል።
ዳግማዊ “በዕድሜ እንራራቃለን ግን አብሬው ስቀመጥ እና ጓደኝነታችን እያደገ ሲመጣ በተዋረድ አልነበረም የምቀርበው” ይላል።
ጨዋታ አዋቂው እንድሪያስ፣ ፕሮፌሰሩ እንድሪያስ፣ አዋቂው እንደሪያስ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 23፤ 2016 ዓ.ም. ነው ህይወታቸው ያለፈው።
እንድሪያስ አብዮተኝነታቸው፣ ፈላስፋነታቸው፣ አስተማሪነታቸው፣ ሀገር ወዳድነታቸው፣ በብዙዎች ዘንድ እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል።
ዓለም አቀፉ አብዮተኛው እንድሪያስ
አብዮተኛው እንድሪያስ ግራ እጁን አንስቶ “መሬት ላራሹ” እያለ የታገለው ትውልድ አባል ናቸው። ራሳቸው የኢትዮጵያን ዘመናዊነትን አዋልዷል የሚሉት የተማሪዎችን ንቅናቄ ተሳተፊ ነበሩ።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ እስከ ወዲያኛው የቀየረው የ“ያ-ትውልድ” አባል ናቸው።
እንድሪያስ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ግድ የሚላቸው፣ለዕኩልነት የሚታገሉ ነጻነትን የሚሹ በሕዝባዊ ንቅናቄዎች ተሳታፊ ነበሩ።
ባለ አፍሮዎቹ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ስለ “ጭቁኑ ሕዝብ’ ሲታገሉ እንድሪያስ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር አባል ነበሩ።
እንድሪያስ በአገረ አሜሪካ እያሉ የጥቁር አሜሪካውያን ትግል የተቀጣጠለበት ወቅት ነበር። “የአፍሪካ አሜሪካውያን ንቅናቄ ሲጀመር በጣም በጉጉት እና በደስታ ነበር ያየሁት። ከልቤ እካፈል ነበር እዛ ውስጥ” ሲሉ ያስታውሳሉ።
እንድሪያስ በጊዜው አሜሪካን እያዳረሰ የነበረው የጸረ ቅኝ ግዛት የጥቁር አሜሪካውያን ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ በንቃት ተሳታፊ ነበሩ።
እንድሪያስ አሜሪካ ሲገቡ የገጠማቸው ዘረኝነት “በጣም እንግዳ እንደሆነባቸው” ለመዓዛ ብሩ ተናግረዋል። በዚሁ ቃለ መጠይቃቸው የገጠማቸውን ሲያብራሩ፤ “[ዘረኝነቱ] ምንም ያልጠበኩት ነገር ነበር፤ ስፋቱ፣ የመብት መገፋቱ፣ ልክ የለሽ መሆኑ እና ድህነቱ በጣም የተለየ ነው። በጣም በጣም የሚያስከፋ ነው” ብለዋል።
ይህ መከፋት እና እልህ በውስጣቸው ያለው እንድሪያስ የ”ብላክ ፓንተርስ” ፓርቲ በሚያካሂዳቸው ሰልፎች እና ተቃውሞዎች እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። ብላክ ፓንተርስ በስፋት በሚያካሂዳቸው የተማሪዎች ምገባ እና ጥናት እንዲሁም የጥቁር መራጮች ትምህርት ላይ የፊት ተሰላፊ ሆኑ።
የእንድሪያስ የፖለቲካ ተሳትፎ በአገረ አሜሪካ የተወሰነ ብቻ አልነበረም።
የሀገራቸው ልጆች የግራ ዘመም ፖለቲካ ሲያሽኮረምማቸው፣ ማርክስን እና ሌኒን በንግግሮቻቻው መሃል ሲጠቅሱ እንድሪያስም በዛው መንገድ ተጉዘው ነበር።
በአገረ አሜሪካ ሆነው ስለ የብሔር እና የመደብ ጭቆና፣ ነጻነት፣ ኢምፔሪያሊዝም፣ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም እና ስለብዝበዛ አስበዋል፤ ተክዘዋል፤ ተሟግተዋል፤ ጽፈዋል።
የብሔር ጥያቄ እና ጉዳይ ቀደም ብሎ ይነሱ የነበሩ ጉዳዮች ቢሆኑም በተማሪዎች ንቅናቄ ዘንድ ግን ሃሳቡ ግዘፍ የነሳው በ1960ዎቹ መጀመሪያ ነበር።
በዚህ ወቅት ነበር ዋለልኝ መኮንን “የብሔረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ” የተሰኘ ጽሑፉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ልሳን ላይ ያሳተመው።
“ኢትዮጵያ የአንድ ብሔር ብቻ አይደለችም” ባለበት በዚህ ጽሑፉ፤ “ብሔረሰባዊ የነጻነት ትግሎች የመገንጠል ዓላማ ቢኖራቸውም እንኳን ሶሻሊስታዊ እስከሆኑ ድረስ ሊደገፉ እንደሚገባቸው” አብራራ።
በዚህን ጊዜ በኢትዮጵያ የብሔሮች ጥያቄ ተማሪዎቹ ሊሸሹት የማይችሉት ርዕሰ ጉዳይ ወደመሆን ተሸጋግሯል።
እንድሪያስ አባል የነበሩበት በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር በጉዳዩ ላይ በዚያው ዓመት ባካሄደው ጉባኤ ተወያይቶ ነበር። ማኅበሩ ውይይቱን ሲያደርግ የመረጠው ገለጻ ከ“የብሔረሰብ ጥያቄ” ይልቅ “የአካባቢያዊነት ችግር” የሚለውን ነው።
የታሪክ ተመራማሪው ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ የማኅበሩ ጉባኤ “አካባባዊነትንና የመገንጠል እንቅስቃሴዎችን በማውገዝ የተራማጆች ዋነኛው ትኩረት በመደብ ትግል ላይ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት አስቀመጠ” ይላሉ።
ይህ የማኅበሩ አቋም በጊዜው አልጄሪያ በነበሩት አብዮተኞች ብርቱ ትችት ቀረበበት። አነዚህ አብዮተኞች ጥላሁን ታከለ በሚል የብዕር ስም፤ “‘የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል’ አብዮተኞች መርህ ሊሆን ይገባል አሉ።
ከአንድ ዓመት በኋላ ፕሮፌሰር እንድሪያስ ‘ቱምቱ ሌንጮ’ በሚል የብዕር ስም “The Question of Nationalities and Class Struggle in Ethiopia” የሚል ጽሑፍ የተማሪዎች መጽሄት የነበረው 'ቻሌንጅ' ላይ አወጡ። ለጥላሁን ታከለ መልስ መሆኑ ነው።
እንድሪያስ በቱምቱ ስም ባወጡት ጽሑፋቸው፤ “የብሔረሰብ ጥያቄ ከመደብ ጥያቄ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ሊታይ የሚገባው” መሆኑን በመጥቀስ ሞገቱ።
የነጻነት ንቅናቄዎች ከአብዮተኞች ድጋፍ የሚያገኙት “አውራ ለሆነው የፀረ-ፊውዳልና ፀረ-ኢምፔሪያሊስት ትግል ጋሬጣ እስካልሆኑ ድረስ ነው” አሉ።
እንድሪያስ በዚሁ ጽሑፋቸው “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዒላማው መገንጠል ሳይሆን ክፍለ አገራዊ ራስ ገዝነት” ሊሆን እንደሚገባው አስገንዝበው ነበር።
እንድሪያስ በቱምቱ ስም ያወጡት ጽሑፍ በጊዜው በ’ቻሌንጅ’ መጽሄት ላይ ይወጡ ከነበሩ ሌሎች መጣጥፎች የተሻለ እና የዳበረ መሆኑን ፕ/ር ባህሩ ‘The Quest for Socialist Utopia’ የተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።
የእንድሪያስ ወዳጅ ዳግማዊ ውብሸት ይህን የፕ/ር ባህሩ ምስክርነት ያስተጋባል። ዳግማዊ ውብሸት “እንድሪያስ በጣም ውስብስብ የሆኑ የፖለቲካ እና የፍልስፍና ሃሳቦችን በቀላሉ ማስተላለፍ ይችላል። ፈላስፋም ቢሆን በጣም ድንቅ ጸሀፊ ነው” ይላል።
ፈላስፋው እንድሪያስ እሸቴ
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ነው። በፍጥነት እያሽከረከረ የነበረ ባለ አፍሮ ጸጉር ኢትዮጵያዊ ወጣት፣ በአሜሪካን ቬርሞንት ገጠራማ አካባቢ በአንድ ፖሊስ እንዲቆም ይደረጋል።
ወጣቱ ተማሪ መሆኑን ገልጾ በፍጥነት በማሽከርከሩ ይቅርታ ጠየቀ።
ከይቅርታው ይልቅ የባለ አፍሮው ተማሪነት ላይ ቀልቡን ያሳረፈው ፖሊስ፤ “ምንድን ነው የምትማረው? ተማሪ ቤትህስ የት ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችን አቀረበ።
“በዊሊያምስ ኮሌጅ ፍልስፍና ነው የማጠናው” ጎረምሳው መለሰ።
“ከየት ነው የመጣኸው” የፖሊሱ ቀጣይ ጥያቄ ነበር።
“ኢትዮጵያ”
ፖሊሱ ሌላ ጥያቄ አስከተለ፥ “ፍልስፍና ምን ይሰራልሃል?”።
ይህ የተለመደ ጥያቄ እንደነበር የያኔው ጎረምሳ እንድሪያስ እሸቴ ያነሣሉ። እንድሪያስ ከ15 ዓመታት በፊት ከፕሮፌሰር ዳግማዊ ውብሸት ጋር በነበራቸው ጨዋታ፤ “ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ጥያቄ እንደሚጠይቁኝ አስታውሳለሁ” ይላሉ።
እንድሪያስ “በዚያን ጊዜ የማህበራዊ ሳይንስ የማይረባ ነበር” ሲሉ ለዚህ ምክንያቱን ይናገራሉ።
እሳቸው ወደ ትምህርት ቤት በሄዱበት ወቅት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ድሃ አገራት የሚመጡ ሰዎች ይማሩ የነበሩት እንደ ኢኮኖሚክስ እና ህክምና ያሉ ጠቃሚ ትምህርቶችን ነበር።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ ሌሎች ትምህርቶችን መማር ጀምረው ነበር፤ ግን አንዳቸውም ለነፍሳቸው አልቀረቡም።
በመጀመሪያ ዓመት ትምህርታቸው የተደሰቱበት ብቸኛ ኮርስ ስነ ግጥም መሆኑን የሚያስታውሱት እንድሪያስ ፍልስፍና ቀልባቸውን ገዛው።
ከዛ በኋላ ከፍልስፍና ጋር ቆረቡ፤ ፍልስፍናን ተማሩ፤ አስተማሩ፤ ተመራመሩ።
እንድሪያስ ከዊልያምስ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፍልስፍና ይዘዋል። የእርሳቸው ዲግሪ ለብቻው በብሔራዊ ጋዜጣ የወጣ ዜና ነበር። አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጊዜው፤ “እንድርያስ እሸቴ የማዕረግ ዲግሪ አገኘ” የሚል ዜና አስነብቦ ነበር።
እንድሪያስ ከዊልያምስ ኮሌጅ ከተመረቁ በኋላ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ዓመት አስተምረዋል። በመቀጠልም ወደ አሜሪካን አገር ተመልሰው ከየል ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፍልስፍና አግኝተዋል።
እንድሪያስ በፍትህ፣ በነጻነት፣ ዘመናዊነት እና ወንድማማችነት (fraternity) ላይ የጻፏቸው ጽሑፎች በፍልስፍና ደጃፍ ባላለፉት ሰዎች ዘንድ ሳይቀር ይታወቃሉ።
እንድሪያስ On Fraternity በሚል ርዕስ ከ43 ዓመታት በፊት የጻፉት መጣጥፍ አሁንም ድረስ ውይይት መቆስቆሻ የንግግር መደገፊያ ሆኖ ያገለግላል።
የፈረንሳይ አብዮት አምድ ተብለው የሚጠቀሱት ነጻነት፣ አኩልነት እና ወንድማማችነት ናቸው። “ወንድማማችነት ግን ብዙ ጊዜ ችላ የሚባል ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር እንድሪያስ፤ “ስለ እሱ ለማጥናት ሞክሬያለሁ” ይላሉ።
ፕ/ር እንድሪያስ “ወንድማማችነት በሶሻሊዝም እና በሕዝባዊ ንቅናቄዎች ውስጥ ከነበረው ስፍራ ውጭ መሰረታዊ ሃሳብ ሆኖ አይታይም እና ይህ ስህተት ይመስለኛል” ሲሉ ከመዓዛ ብሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረው ነበር።
ፕሮፌሰሩ አክለውም “ነጻነት እና ዕኩልነትን መሰረት ያደረጉ ስርዓቶች ድክመታቸው ለዚህ [ወንድማማችነት] ትኩረት አለመስጠታቸው ነው” ብለዋል።
“እኩልነት እና ነጻነት በፍልስፍናዊ ስነጽሁፍ እና ሃቲት ላይ በደንብ የተብላሉ ናቸው” የሚለው ፕሮፌሰር ዳግማዊ፤ “ወንድማማችነት [ግን] በደንብ የተብላላች ሃሳብ አይደለችም። እንድሪያስ የመጀመሪያው ፈላስፋ ነው ‘ለምንድን ነው [ወንድማማችነት] ትኩረት ያልተሰጠው? እሴቱ ምንድን ነው?’ ብሎ በመጻፍ” ይላል።
ወንድማማችነት “ከፍተኛ ቦታ ያለው ነገር ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር እንድሪያስ፤ ወንድማማችነት የነጻነት እና እኩልነት ጽንሰ ሃሳቦችን ስጋ ያለበሰ ነው።
ምዕራባውያን እናከብረዋለን የሚሉት ነጻነት እንኳን የሁሉም ሰው ልጆች መብት ሊሆን የቻለው ይህ የወንድማማችነት ስሜት ሲስፋፋ ነው። በሰው ልጅነት [ሁላችንም] ወንድማማቾች ነን፤ እህትማማቾች ነን የሚለው ስሜት ስር እስኪይዝ ድረስ ለሁሉም አልተዳረሰም” ሲሉ በሸገር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
ፕ/ር እንድሪያስ መጣጥፋቸውን፤ “ሰዎች በመካከላቸው የወንድማማችነት ስሜት እንዲኖር ምን ሊጋሩ ይገባል?” በሚል ጥያቄ ይጀምራሉ። እንድሪያስ የሲቪክ ወንድማማችነት የሚፈጠረው በተፈጥሮ ዝምድና ወይም ፍቅር ላይ ሳይሆን አንድን ዓላማ በሚጋሩ ግለሰቦች መካከል ባለው ግንኙነት ወይም ስምምነት ነው ይላሉ።
በዘመናዊነት ጽንሰ ሃሳብ ላይ የጻፉት መጣጥፍ ሌላው በብዙሃኑ ዘንድ የሚታወቀው የፕሮፌሰር እንድሪያስ ጽሁፍ ነው። ፕሮፌሰር እንድሪያስ በዚህ መጣጥፋቸው “ዘመናዊነት የሁሉም ነው፥ ዘመናዊነት የጋራ መዳረሻ ሳይሆን የጋራ እጣ ፈንታ እና የጋራ የሕዝብ ባህል ነው” ይላሉ።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ የዘመናዊነት መለኪያ የሚሉት፤ ሴኩላሪዝም የሚባለው ከኃይማኖታዊ ወይም በሌላ መልክ ሁሉም ሰው ከሚከተለው የዘልማድ ዕምነት መለየት/መነጠልን ነው። እንዲሁም የሰው ልጅ ነጻነትን እውን ማድረግ ነው።
ይህን ተከትሎም የሃሳብ ብዝሃነት ሊኖር እንደሚችል ያነሳሉ። ይህን ተከትሎም “የማይጣጣሙ የሚመስሉ የተለያዩ አስተሳሰቦች ይቀርባሉ” ይላሉ።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ በመጣጥፋቸው፤ “በዘመናዊ ሕይወት ውስጥ ብዝሃነት ወይም ብዙነት ማለት የመጨረሻ እሴት ያላቸው ጉዳዮች፣ በሕዝብ ሕይወት እና በፖለቲካ አጀንዳ ውስጥ ማዕከላዊ አይደሉም። ይልቁንም በግለሰቦች የግል ሕይወት እና በግለሰቦች የግል ማኅበራት ውስጥ በዋናነት የሚበለጽጉ ናቸው” ሲሉ ያብራራሉ።
ዘመናዊነት ከዘልማድ አስተሳብ መነጠል፣ ግለሰባዊ ነጻነትን መቀናጀት፣ ብዝሃነት ማስተናገድ የመሳሰሉ መልካም ሀሳቦች እንዳሉት ሁሉ አስከፊ ገጽታዎችን እንዳሉት ፕሮፌሰር እንድሪያስ ያስገነዝባሉ።
የ20ኛው ክፍለ ዘመን ክስተት የነበሩት የጦር ወንጀሎች እና የዘር ፍጅቶች የተፈጸሙት በዘመናዊ መንግሥት፣ ዘመናዊ ፕሮፓጋንዳ፣ ዘመናዊ ቢሮክራሲ፣ ዘመናዊ ጦር እና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች መሆኑን በመጣጥፋቸው ያነሳሉ።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ አክለውም፤ “ሆሎኮስት፣ ሂሮሺማ እና ሌሎች የሃያኛው ክፍለ ዘመን ከባድ ክፋቶች የሞራል እድገት በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀለበስ እንደሚችል ያሳያሉ” ይላሉ።
“የዘመናዊነት ጽንሰ ሃሳብ እዚህ ቦታ ነው የተጀመረው” የሚል ማብራሪያ አለመኖሩን የሚያነሱት ፕሮፌሰር እንድሪያስ። እሳቸውም ጭምር ተሳታፊ የነበሩበት የኢትዮጵያ ተማሪዎችን ንቅናቄ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት አዋላጅ መሆኑን በዚሁ መጣጥፋቸው ጠቁመዋል።
የዘመናዊነት አላባውያን የሚሏቸው ሕዝባዊ አስተዳደር፣ ዕኩልነት፣ ሴኩላሪዝም፣ በዘር ሃረግ የሚገኙ መብቶች እንዲከስሙ በሶሻሊዝም ስም በአደባባይ የተጠየቁት በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሆኑን ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ የተማሪዎች ንቅናቄ የኢትዮጵያን ዘመናዊነት ሲያዋልድ “ለመቅሰፍት አጋልጦናል” ይላሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ ኢትዮጵያ ከቅድመ ዘመናዊ ትናንቷ ለመላቀቅ ያደረገችው ጥረት ግቡን ባይመታም፤ ለሶሻሊዝም ያለው ዝግጁነት የተለያዩ ቅዠቶችን አሽሞንሙኖ አልፏል።
ከእነዚህ ቅዠቶች መካከል እንደ የኢኮኖሚው በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆንን የመሳሰሉ ጥቂት ወሳኝ እርምጃዎች የኢኮኖሚ እድገት እና ፍትህ ይሰጣል ያስገኛል የሚለው ነው።
“ገበሬዎች ከባላበቶች ግዴታዎች ነፃ ስለወጡ ብቻ ከድህነት እንዲላቀቅ እንዴት ይጠበቃል?” የሚል ጥያቄ የሚያነሱት ፕሮፌሰር እንድሪያስ፤ “ከረሃብና ከድህነት ነፃ መሆንም ሆነ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ መሻገር አልተቻለም። በተቃራኒው ገበሬዎች ቀደም ሲል በባላባቶች ከተጠየቁት የበለጠ ከባድ የመንግሥት ግዴታዎች ተገዢ ሆነዋል” ሲሉ አብራርተዋል።
የዲሞክራሲያዊ እሴቶች እና ልምምዶችን መስዋዕት መሆን ሶሻሊዝምን ጨምሮ የትኛውም ሕዝባዊ ዓላማዎች ማሳመን እንደማይችሉ ፕሮፌሰር እንድሪያስ ጽፈዋል።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ በኢትዮጵያ የሶሻሊስዝም ዓላማ በወታደራዊ ኃይል ተነጥቆ፣ የመንግሥትን ስልጣን ለመጨበጥ እና የዜጎችን መብትና ነፃነት የረገጠውን ጨካኝ አገዛዝ ለማጠናከር ውሏል ይላሉ።
የኔታ እንድሪያስ፦ ከፔንሲልቬኒያ እስከ ስድስት ኪሎ
ተማሪዎቻቸው ፕሮፌሰር እንድሪያስ የአስተማሪነት ሚዛን፣ የአዋቂነት መስፈሪያ መሆናቸውን ይናገራሉ። በምዕራቡ የእውቀት እና አካዳሚ ውስጥ ገናና ስም ባላቸው ተቋማት ፍልስፍናን አስተምረዋል።
ከእነዚህ ዩኒቨርስቲዎች መካከል ፔንሲልቬኒያ፣ በርክሊ፣ ብራውን እና ሎስ አንጀለስ የሚገኘው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ይጠቀሳሉ።
እንድሪያስ መምህርነትን የጀመሩት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ነው። ከዊልያምስ ኮሌጅ ከተመረቁ በኋላ ለአንድ ዓመት በዩኒቨርሲቲው ፍልስፍና አስተምረዋል።
አሜሪካን አገር በሚገኙት ስመ ጥር ትምህርት ቤቶችም በመምህርነት አገልግለዋል።እንድሪያስ ስለመምህርነት ሲያወሩ፤ “መምህርነት ማለት ወጣቶች በለጋ ዕድሜያቸው አዲስ ዓለም እንዲያዩ፤ እነሱም አዲስ ዓለም እንዲፈልጉ ማዘጋጀት [ነው]” ብለው ነበር።
የመምህር ኩራት “ከእሱ የላቀ እና የረቀቀ ሰው ማፍራት ነው” የሚሉት እንድርያስ፤ “እንደዚህ አይነት ሰዎች ጥቂትም ቢሆን አፍርቻለሁ የሚል እምነት አለኝ፤ በእሱ በጣም እኮራለሁ” ሲሉ ስለ አስተማሪነታቸው ተናግረዋል።
ፕ/ር እንድሪያስ በተማሪዎቻቸው የሚወደዱ መምህር ነበሩ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የሕግ ፍልስፍና አስተምረዋል።
የአሁኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የፕሮፌሰር እንድሪያስ ተማሪ ነበሩ።
ጌታቸው ስለቀድሞ መምህራቸው ያላቸውን ትውስታ “ፕሮፌሰርን እንድሪያስ በጣም ጎበዝ አስተማሪ፣ ሰው ሰው የሚሸት ፈላስፋ፣ ከባድ የሚመስሉ ሃሳቦችን በቀላል ቋንቋ መግለጽ የሚችል፣ ከምንም ነገር በላይ ግን ለሀገሩ ለሕዝቡም ትልቅ ፍቅር ያለው ነው” ሲል ለቢቢሲ አጋርቷል።
የፕሮፌሰር እንድሪያስ እና አቶ ጌታቸው ግንኙነት ከተማሪ እና አስተማሪነት ባለፈ የወዳጅነትም ነበር።
ጌታቸው “ብዙ ሰዎች ፊት ሁኜ በማብራራት በመናገር የማሳልፈው ነገር ካለ። እንድሪያስ ጋር ሲሆን በመስማት ብቻ ነው ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው” ይላሉ።
ሌላኛው የፕሮፌሰር እንድሪያስ ተማሪ ሃሰን መሐመድ የእሳቸውን ፈለግ ተከትሎ መምህር ሆኗል። በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሚያስተምረው ሃሰን፤ “እንድሪያስ መምህርነትን በጣም እንድንወድ አድርጎናል። እኔ በበኩሌ [መምህርነትን] እንድወድ እና ወደዚህ ሙያ እንድገባ ያደረገኝ እሱ ነው” ይላል።
እንድሪያስ ሰዓት አክባሪ ነበሩ። የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸው ከመጀመሩ 30 ደቂቃ ቀድሞው ክፍል እንደሚገኙ ሃሰን ያስታውሳል።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ ክፍል ያልተመደቡ ተማሪዎች ሳይቀር ትምህርታቸውን ሊከታተሉ እርሳቸው ክፍል ይገቡ ነበር። አንዳንዶች ዲግሪ ጭነው፣ ተመርቀውም እርሳቸውን ለመስማት ክፍል የሚገቡም ነበሩ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ቁምላቸው ዳኜ አንዱ ነው።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ እየሰሩ በነበረበት ወቅት የቁምላቸው አለቃ ነበሩ።
ቁምላቸው እንደ አለቃ የሚያውቃቸው ፕሮፈሰር እንከን የማይወጣላቸው መምህር መሆናቸውንም ይመሰክራል። “Jurisprudence የሚባለውን ትምህርት ሲያስተምር፣ በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ያስተምር ስለነበር ትምህርት ከጨረስኩም በኋላ እንደ መደበኛ ተማሪ ክፍል እየገባሁ አከታተል ነበር” ይላል።
ቁምላቸው “መቼም የሚተካ አይመስለኝም የእንድሪያስን እውቀት፣ ብስለት የአስተሳሰብ ልህቀት አቻ የሆነው ሰው የለም” ሲል እንድሪያስን ያስታውሳል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩሉ፤ “ወደር በሌለው አኳኋን ደግ የሚባል፣ ብሩህ አዕምሮ ያለው ሰው ነበር” ሲል ይገልጻቸዋል።
የእንድሪያስ ባለ ብሩህ አዕምሮነት አከራካሪ አይደለም። የፈላስፋው እንድሪያስ እሳቤ “ስፋትም ጥልቀትም ያለው” መሆኑን የሚያስታውሰው ዳግማዊ ውብሸት “ይህ ያልተለመደ መሰጠት ነው” ይላል።
ሃሰን መሐመድ፤ “እንድሪያስ መሬት ነው፤ ትሁት ነው፤ ትህትና ያለው ምሁር ነው። እንደ እውቀቱ አይደለም” ሲል አስተማሪውን ያስታውሳል።
አብዮተኛው እንድሪያስ፣ ፈላስፋው እንድሪያስ፣ ትሁቱ እንድሪያስ፣ ጥበብ ወዳጁ እንድሪያስ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በነበራቸው ሚና፤ በፍልስፍናቸው ሲታወሱ ይኖራሉ።