የዩክሬን የቀድሞ የኢነርጂ ሚኒስትር ከአገር ለመውጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ

ጀርመን ጋሉሽቼንኮ (በስተግራ) በዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ መንግሥት ውስጥ በሙስና ወንጀል ስማቸው ከተጠቀሰ በርካታ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጀርመን ጋሉሽቼንኮ (በስተግራ) በዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ መንግሥት ውስጥ በሙስና ወንጀል ስማቸው ከተጠቀሰ በርካታ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩክሬን የቀድሞ የኢነርጂ ሚኒስትር አገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ባለፈው ዓመት በሙስና ቅሌት ስማቸው ከተጠቀሱት ባለሥልጣናት መካከል አንዱ የሆኑት እና በኋላ ላይ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ጀርመን ጋሉሽቼንኮ፣ ዩክሬንን ለቅቀው ሲወጡ ባቡር ላይ መያዛቸው ተገልጿል።

በኅዳር ወር 100 ሚሊዮን ዶላር የዝርፊያ ወንጀል ውስጥ ከተሳተፉት በርካታ የመንግሥት ሰዎች አንዱ መሆናቸው ተጠቅሷል።

ይህ የሙስና ቅሌት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን አስተዳደር ይጥላል ተብሎ ተሰግቶ ነበር።

የዜሌንስኪ አስተዳደር ወደ ሥልጣን የመጣው ሩሲያ ወረራ ከመፈጸሟ በፊት ሙስናን ከአገሪቱ ጠራርጎ ለማጥፋት ቃል በመግባት ነበር።

ለዜሌንስኪ በጦርነቱ ወቅት የቅርብ አማካሪያቸው የነበሩት እና የጽህፈት ቤት ኃላፊው አንድሪ ይርማክ ቤታቸው ከተፈተሸ በኋላ ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል።

ፕሬዝዳንቱም ሆነ ይርማክ ጥፋት ሰርተዋል በሚል አልተከሰሱም።

ይሁን እንጂ ይህ የሙስና ቅሌት ከተሰማ በኋላ በዩክሬን ሕገ መንግሥት መሠረት እአአ ከ2022 ጀምሮ በሩሲያ ወረራ ምክንያት ሳይካሄድ የቀረውን ምርጫ እንድታካሂድ ከአሜሪካ የሚደርሰውን ጫና በርትቷል።

የዩክሬን ብሔራዊ የፀረ ሙስና ቢሮ (ናቡ) እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ መርማሪዎች የቀድሞውን የኢነርጂ ሚኒስትር "የአገሪቱን ድንበር ሲያቋርጡ" በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ይፋ አድርጓል።

ጋሉሽቼንኮን በግልጽ በመግለጫው ላይ ባይጠቀሱም፣ ነገር ግን በበርካታ የዩክሬን መገናኛ ብዙኃን ስማቸው ተገልጿል።

ጋሉሽቼንኮ ከሦስት ዓመታት የኢነርጂ ሚኒስትር ሆነው ካገለገሉ በኋላ ለአጭር ጊዜ የፍትህ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል።

በዚህ የኃላፊነት ቦታ በዜሌንስኪ በኅዳር ወር ሥልጣናቸውን እንዲለቁ እስኪነግሯቸው ድረስ ቆይተዋል።

እርሳቸውን የተኩት ስቪትላና ሂሪንቹክም በሙስና ወንጀል እጃቸው እንዳለበት ከተጠቀሰ በኋላ ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል።

ናቡ ስለ ጋሉሽቼንኮ እስር ምንም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም፣ ወቅታዊ መረጃዎችን በወቅቱ እንደሚያቀርብ ተናግሯል።

የድንበር ጠባቂዎች ለመሸሽ ከሞከሩ ለባለሥልጣናቱ እንዲያሳውቁ ከተነገራቸው በኋላ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ኪየቭ መወሰዳቸውን ሬዲዮ ፍሪ አውሮፓ ዘግቧል።

ናቡ እና የዩክሬን ሌላኛው የፀረ-ሙስና አካል የሆነው ልዩ ፀረ-ሙስና አቃቤ ሕግ ቢሮ (ሳፕ) እንደገለጹት፣ ኦፕሬሽን ሚዳስ ተብሎ የተሰየመው ግዙፍ የፀረ ሙስና ዘመቻ ለ15 ወራት ሲያካሄድ የቆየው የምርመራ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።