ለሩሲያ ሲዋጋ ዩክሬን ውስጥ የተገደለው ኬንያዊ ቤተሰቦች የልጃቸው አስከሬን እንዲመለስ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Ukraine Defence Intelligence
ዩክሬን ውስጥ ለሩሲያ ሲዋጋ የተገደለው የ29 ዓመት ኬንያዊ ቤተሰቦች፤ ወጣቱ ለሞስኮ ሲዋጋ የነበረበትን ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው እና አስከሬኑ ወደ አገሩ እንዲመለስ ጠየቁ።
ክሊንተን ኒያፓራ ሞጌሳ የተባለው ኬንያዊ ወጣት በአውሮፓውያኑ 2024 ከአገሩ የወጣው ኳታር ውስጥ ሥራ ለማግኘት እንደነበር ቤተሰቦቹ ገልጸዋል። ኋላ ላይ ግን ከኳታር ወደ ሩሲያ ማምራቱን እንደተረዱም ተናግረዋል።
ቅዳሜ ዕለት የዩክሬን ባለሥልጣናት በሰጡት መግለጫ፤ ኳታር ውስጥ የተመለመለው ኬንያዊው ወጣት በምሥራቅ ዩክሬን ዶኔትስክ ግዛት በተካሄደ ውጊያ መገደሉን አስታውቀዋል። ኬንያዊው በተገደለበት 'ሚት አሳልት' የሚል ስያሜ በተሰጠው ውጊያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንደሞቱም ተገልጿል።
ሩሲያ ወታደሮች አስከሬኑን ሳያነሱ መሄዳቸውን የተናገሩት የዩክሬን ባለሥልጣናት፤ ሟቹ የሌሎች ሁለት ኬንያውያን ፓስፖርትንም ይዞ እንደተገኘ አስረድተዋል።
የ29 ዓመቱ ሞጌሳ ሞት የተሰማው፤ ዩክሬን ውስጥ ለሩሲያ ጦር እንዲዋጉ የሚመለመሉ ኬንያውያን በተመለከተ የተፈጠረው ስጋት እየጨመረ ባለበት ወቅት ነው።
የሞጌሳ ቤተሰቦች፤ ልጃቸው ሥራ ፍለጋ ወደ ኳታር የሄደው መሬት ተሽጦ እና ገንዘብ ተሰባስቦ እንደሆነ 'ሲቲዝን ቲቪ' ለተባለው የአገር ውስጥ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
የሟቹ ወንድም ጆኤል ሞገሬ፤ "ሞቱ አስደንግጦናል" ብሏል። ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ እንደነበር ያስታወሰው ሞገሬ፤ "የቤተሰቡ ብቸኛ የገቢ ምንጭ እና ተስፋ ነበር" ሲል ገልጾታል።
የስኳር ታማሚ መሆናቸውን የተናገሩት እናቱ ሜለን ሞራ በበኩላቸው የሕክምና እና የመድኃኒት ወጪያቸውን ይሸፍን የነበረው እርሱ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ መጋባታቸውን አክለዋል።
"መንግሥት እርዳታ እንዲያደርግ እማጸናለሁ" ብለዋል።
ባለፈው ወር የኬንያ መንግሥት ሩሲያ ውስጥ ሲዋጉ የነበሩ 18 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስታውቆ ነበር። ኅዳር ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ኬንያውያን ለሩሲያ እየተዋጉ መሆናቸው እንደሚታወቅ እንዲሁም የምልመላ መረቡ አሁን በሥራ ላይ መሆኑ እንደሚታወቅ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸዋል።
ለሩሲያ እየተዋጉ ያሉ ዜጎች ያሏት ኬንያ ብቻ አይደለችም። ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ሩሲያ ውስጥ ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፍል ሥራ ታገኛላችሁ በሚል የተታለሉ ወጣቶች ዩክሬን ጦርነት ውስጥ እንዲገዋጉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።
የዩክሬን የስለላ መረጃ እንደሚያሳየው ከ36 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ1,400 በላይ ሰዎች ለሩሲያ እንዲዋጉ ተመልምለዋል ተብሎ ይገመታል።
ዩክሬን ከዚህ ቀደም ለሩሲያ የሚዋጋ ማንኛውም ሰው እንደ ጠላት ተዋጊ እንደምትቆጥር እንዲሁም ደኅንነቱ የተጠበቀው መውጫ መንገድ እጅ መስጠት እንደሆነ አስጠንቅቃለች።
የዩክሬን የስለላ ተቋም ቅዳሜ ዕለት በወጣው መግለጫ፤ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ሩሲያ እንዳይጓዙ ወይም በተለይም ሩሲያ ውስጥ የሚቀርቡላቸውን መደበኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎች እንዳይቀበሉ አሳስቧል።
ወደ ሩሲያ መጓዝ "ያለ በቂ ሥልጠና የመትረፍ ዕድል ጠባብ ወደሆነበት ውጊያ ግንባር በኃይል እንዲሰለፉ የመደረግ አደጋን እንደሚጋርጥ" በመግለጽ የዩክሬኑ ተቋም አስጠንቅቋል።















