ለወንዶች የተዘጋጀው የእርግዝና መከላከያ እንክብል የወንዴ ዘር እንዳይንቀሳቀስ አስቻለ

የወንድ የዘር ፍሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሆርሞን ጋር ግንኙነት በሌለው መንገድ ለወንዶች የተሰራው የእርግዝና መከላከያ እንክብል የወንዶች የዘር ፍሬ እንዳይንቀሳቀስ ማስቻሉን ተመራማሪዎች ገለጹ።

ቀደም ሲል እንክብሉ በአይጦች ላይ ተሞክሮ የወንዴ ዘር ቢያንስ ለተወሰኑ ሰዓታት ወደ ሴቷ ዘር ወይም እንቁላል እንዳይደርስ ማገድ ችሏል።

በሙከራ ደረጃ ያለው እንክብል ለሰዎች ከመሰጠቱ በፊት ጥንቸሎች ላይ በርከት ያሉ ሙከራዎች ይደረጋሉ።

ተመራማሪዎች እንክብሉ የሚሰራው ወንዶች ግንኙነት ከመፈጸማቸው ከአንድ ሰዓት በፊት ከወሰዱት ነው ብለዋል።

እንክብሉ እንዴት ይሰራል?

ሴቶች ከሚወስዱት የወሊድ እንክብል በተቃራኒ ይህ እንክብል ከሆርሞን ጋር ግንኙነት የለውም።

ይህ መሆኑ ወንዶች ላይ ከሆርሞን ጋር በተያያዘ የጎንዮሽ ጉዳት አያስከትልም። ይህ ደግሞ ተመራማሪዎች ያገኙት አንዱ ጥቅም ነው ተብሏል።

እንክብሉ የወንዴው ዘር ወደ እንቁላሉ እንዳይጓዝ አቅጣጫን ያስታል።

በአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋም የገንዘብ ድጋፍ ቀድም ብሎ በአይጦች ላይ የተደረገ ምርምር እንክብሉ የወንዴ ዘር እንዳይንቀሳቀስ ማድረጉን አሳይቷል።

እንክብሉ ለሦስት ሰዓታት ውጤታማ ሆኖ መሥራት የሚችል ሲሆን፣ በ24 ሰዓት ውስጥ ከሰውነት ይወጣል ተብሏል።

ከተመራማሪዎች መካከል አንዷ የሆኑት ዶክተር ሜላኒ ባልባች ምርምሩ የእርግዝና መከላከያን በቀላሉ ለመጠቀም ተስፍ ሰጪ ነው ብለዋል።

እንክብሉ በተፈለገ ጊዜ እና ድግግሞሽ መወሰድ የሚቻል ሲሆን ሰዎች የመውለድ ፍላጎታቸው በየቀኑ የመቀየር ዕድልን ይሰጣል ተብሏል።

ሆኖም እንክብሉ ከኮንዶም በተቃራኒ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚመተላለፉ በሽታዎችን አይከላከልም።