የአሜሪካ ባለስልጣናት ቦይንግ 777 በአደገኛ ሁኔታ ድንገት ከፍታውን ለምን እንዳጣ ምርመራ ሊያደርጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የአየር ደኅንነት ባለስልጣናት ከወራት በፊት በነበረ በረራ ቦይንግ 777 አውሮፕላን በምን ምክንያት አደገኛ በሆነ ሁኔታ ከፍታውን እንደቀነሰ እንመረምራለን አሉ።
ዩናይትድ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 1722 ታኅሳስ 9/2015 ዓ.ም. ከሃዋይ ከተነሳ በኋላ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በፍጥነት ከፍታውን አጥቶ፣ አፍንጫውን ዘቅዝቆ በአደገኛ ሁኔታ ቁልቁል መብረሩ ተገልጿል።
አውሮፕላኑ ከፓስፊክ ውቅያኖስ ጋር ለመላተም ሰከንዶች ብቻ ሲቀሩት 775 ጫማ (236 ሜትር) ከፍታ ላይ የበረራ አቅጣጫውን አስተካክሎ ከ27 ደቂቃዎች በኋላ ሳን ፍራንሲስኮ ማረፉ ተገልጿል።
አውሮፕላኑ ከካሉሉኢ አየር ማረፊያ ከተነሳ በኋላ ምንም እክል ሳይገጥመው ለ71 ሰከንዶች ከበረረ በኋላ ድንገት ከፍታውን አጥቶ አደገኛ በሆነ ሁኔታ በፍጥነት ወደ መሬት መውረድ መጀመሩን ፍላይትራዳር24 አሳይቷል።
በአሜሪካ የአውሮፕላን አደጋዎች የሚመረምረው ብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ በቀጣይ ሶስት ሳምንታት ክስተቱን በተመለከተ ሪፖርት ያወጣል ተብሏል።
በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት ሮድ ዊሊያምስ ለሲኤንኤን ሲናገሩ፤ “በአውሮፕላኑ ውስጥ ጩኀት ነበር። ሁሉም ተሳፋሪ አንድ ያልተመደ ነገር መከሰቱን አውቆ ነበር” ካሉ በኋላ ከውቅያኖስ ጋር ሊላተሙ አምስት ሴኮንዶች ብቻ እንደቀራቸው ሲያስቡ ክስተቱ እጅጉን አሳዛኝ እንደሚያደርገው ጨምረው ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ በሳን ፍራንሲስኮ ካረፈ በኋላ አብራሪዎቹ ያጋጠማቸውን ለአየር መንገዱ ሪፖርት ማቅረባቸውን የዩናይትድ አየር መንገድ ተወካይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሁለቱ አብራሪዎች በድምሩ ከ25ሺህ ሰዓታት በላይ የበረራ ልምድ እንዳላቸው ተገልጿል።
አየር መንገዱ በክስተቱ ዙሪያ ምርመራ ካደረገ በኋላ አብራሪዎች ተጨማሪ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ማድረጉን ገልጿል።
ኩባንያው ባወጣው መግለጫ “ደኅንነት ቀዳሚ የምንሰጠው ጉዳይ ነው” ብሏል።
የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) እንዲሁ በተመሳሳይ ክስተቱን በተመለከተ ሪፖርት ደርሶታል። የፌደራል ኤጀንሲው “አግባብ የሆነ ዕርምጃ ወስጃለሁ” ከማለት ውጪ ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጠም።
ዩናይትድ አየር መንገድ አውሮፕላን ያጋጠመው ክስተት በአሜሪካ በቅርቡ ሪፖርት ከተደረጉ አደገኛ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው።
በዚህ ዓመት በኒው ዮርክ እና ቴክሳስ አደገኛ ክስተቶች አጋጥመው ነበር። ከሳምንታት በፊት ባጋጠመ ክስተት የፌዴክስ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ከሳውዝዌስት አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር ላለመጋጨት ሲል ለማረፍ ያደረገውን ጥረት በመጨረሻ ደቂቃዎች ሰርዟል።
በጆን ኤፍ ኬኔዲ ኒው ዮርክ ደግሞ የዴልታ አየር መንገድ አውሮፕላን ለመነሳት እየተንደረደረ ሳላ ከአሜሪካን አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር ላለመጋጨት ሲል ለመቆም ተገዷል።












