በመጀመሪያው ዙር የጋዛ የሰላም ዕቅድ ላይ ከስምምነት መደረሱን ትራምፕ አስታወቁ

እስራኤል እና ሐማስ በመጀመሪያው ዙር የጋዛ የሰላም ዕቅድ ላይ እንደተስማሙ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "ሁሉም ታጋቾች በቅርቡ ይለቀቃሉ። እስራኤል ወታደሮቿን ወደተስማማንበት ክልል ትመልሳለች" ብለዋል።

ሐማስ ስምምነት ላይ መደረሱን ቢገልጽም፣ እስራኤል የምትለቃቸውን ፍልስጤማውያን ስም ዝርዝር ገና እንዳልተረከበ በፍልስጤም የሚገኙ የቢቢሲ ምንጭ ጠቁመዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ለእስራኤል ታላቅ ቀን ነው" ሲሉ ስምምነቱን ገልጸውታል።

ከአገራቸው ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተው ስምምነቱን ካጸደቁ ወዲያውኑ የተኩስ አቁም ስምምነት ይተገበራል።

በግብፅ የተደረገው የሰላም ዕቅድ ድርድር የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆማል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 20,179 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 67,183 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

የሰላም ዕቅዱ የመጀመሪያው ዙር ላይ ከስምምነት የመደረሱ ዜና እንደተሰማ በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ካሀን ዩኑስ ፍልስጤማውያን ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።

እስራኤላውያን የታጋቾች ቤተሰቦችም "ትራምፕን እናመሰግናለን፤ ታሪካዊ ስኬት ነው" ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

ሐማስ ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን እስረኞችን የምትፈታ ይሆናል።

ሁለቱ ወገኖች ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሁለት ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም ብዙም ሳይቆይ ውጊያው ተጀምሯል።

ሦስተኛው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፀና ዓለም አቀፍ አካላት ማስተማመኛ ስለመስጠታቸው ግልጽ አይደለም።

የትራምፕ የሰላም ዕቅድ ሐማስ ትጥቅ መፍታት እንዳለበት አቅጣጫ ያስቀምጣል። ሐማስ ግን በዚህ አልተስማማም።

የወደመችውን ጋዛ መልሶ ከመገንባት እንዲሁም በቀጣይ ጋዛን ማን ያስተዳድረታል? በሚለው ዙርያ የሰላም ዕቅዱ የያዛቸው ነጥቦች ላይ ከስምምነት ስለመደረሱም ግልጽ አይደለም።

ልጇ የታገተባት እስራኤላዊ እናት ማታን ዛንጉር "ልጄ ወደ ቤቱ ሊመለስ ነው። እህቶቹና ሚስቱ በጉጉት እየጠበቁት ነው። ይህ ቀን እንዲመጣ እያለቀስኩ ስጸልይ ነበር" ብላለች።

በካሀን ዩኑስ ሮይተርስ ያነጋገረው ዋይል ራድዋን "ትራምፕ ጦርነቱ መቆሙን አስታውቀዋል። ፈጣሪ ይመስገን። በጣም ነው ደስ ያለን" ብሏል።

ዋይል አክሎም "ደም መፋሰሱ እንዲቆም ያስቻሉት ወንድሞቻችን ምስጋና ይገባቸዋል" ሲል ደስታውን ገልጿል።

ሌላው የካሀን ዩኑስ ነዋሪ አብዱል መጅድ ራቦ "ግድያው ስለቆመ ፈጣሪን እናመሰግናለን። እኔ ብቻ ሳልሆን መላው የጋዛ ሰርጥ በደስታ ተሞልቷል። ሁሉም የዓለም ሕዝብ በተኩስ አቁሙ ደስተኛ ነው። ከኛ ጎን የቆማችሁትን ሁሉ እናመሰግናችኋለን" ብሏል።

የቢቢሲ የጋዛ ባልደረባ ሩሽዲ አቡሎር እንደሚለው፣ በጋዛ ደስታቸውን የሚገልጹ ፍልስጤማውያን በየጎዳናው ይታያሉ።

በተደጋጋሚ ለመፈናቀል የተገደዱት ፍልስጤማውያን ወደ ቤታቸው የመመለስ ተስፋንም ሰንቀዋል።

አሶሽየትድ ፕረስ ያነጋገረው አይማን ሳበር የተባለ ነዋሪ "ቤቴን መልሼ እሠራለሁ፤ ጋዛን መልሰን እንገነባታለን" ብሏል።

በጃባሊያ መጠለያ ውስጥ ያለው ፍልስጤማዊ አሕመድ ሻሕቢር "ቤቴ እስከምመለስ እጅጉን ጓጉቻለሁ" ብሏል።

ኢያድ አማዋዊ የተባለው ፍልስጤማዊ "ደስተኛ ብሆንም እስራኤል ስምምነቱን እንዳታሰናክል እፈራለሁ" ብሏል።

"በማመን እና ባለማመን ውስጥ ነን። ደስታና ሐዘን ተደበላልቆብናል። ከደረሰብን የሥነ ልቦና ሕመም ማገገም አለብን" ሲልም ተናግሯል።

የሰላም ዕቅዱ ላይ ከስምምነት እንዲደረስ በማሸማገል ረገድ ግብፅ፣ ካታር፣ ቱርክ እና አሜሪካ ጉልህ ሚና ነበራቸው።

የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጄምስ ኤልደር ጋዛ ሆነው ባስተላለፉት የቪድዮ መልዕክት "ያ የምንጠብቀው ቅጽበት ደረሰ ማለት ነው? ደስ ብሎናል" ብለዋል።

ትራምፕ ከአሜሪካዊው የቴሌቭዥን መሰናዶ አቅራቢ ሾን ሀንዲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ከዚህ በኋላ ያለው ዓለም የተለየ ይሆናል። መካከለኛው ምሥራቅ ተቀራርቧል" ብለዋል።

"ጋዛ ደኅንነቷ የተጠበቀ ትሆናለች። ጋዛን መልሶ ለመገንባት የቀጣናው ሃብታም አገራት ይተባበራሉ። በመካከለኛው ምሥራቅ ሰለም እንደሚሰፍን አልጠራጠርም" ሲሉም ትራምፕ አክለዋል።