ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋዛ የሰላም ዕቅድ ላይ ከስምምነት ለመድረስ 'ጥሩ ዕድል' መኖሩን ትራምፕ ገለጹ
የጋዛን ጦርነት ለማስቆም አሜሪካ ያረቀቀችው የሰላም ዕቅድ በግብፅ ሻርም ኤል-ሸይክ ውይይት እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ቀጥተኛ ያልሆነው ውይይት የሰላም ዕቅዱ የመጨረሻ ስምምነት ላይ እንዲደረስበት ያስችላል ተብሏል።
የግብፅ እና ፍልስጤም አመራሮች ለቢቢሲ እንደገለጹት ውይይቱ እየተካሄደ ያለው እስራኤላውያን ታጋቾች እና ፍልስጤማውያን እስረኞች የሚለቀቁበትን "መንገድ ለማመቻቸት" ነው።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "በቀጣይ ቀናት" ታጋቾች እንደሚለቀቁ ተስፋ አለኝ ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድላችን ሰፊ ነው። ዘላቂ ስምምነትም ይሆናል" ብለዋል።
ሐማስ የሰላም ዕቅዱን በከፊል እንደሚስማማበት ቢገልጽም፤ ትጥቅ መፍታትና በቀጣይ ጋዛን የማስተዳደር ነጥቦች ላይ ከስምምነት አልተደረሰም።
በውይይቱ ሁለተኛ ቀን የግብፅና የካታር አመራሮች ከእስራኤልና ሐማስ ጋር ይወያያሉ።
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጥቃት 18,000 ሕጻናትን ጨምሮ ከ67,160 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
የጦርነቱን ሁለተኛ ዓመት መቃረብ አስታከው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ "የትራምፕ ዕቅድ አሳዛኙን ግጭት ሊያስቆም ስለሚችል ሁሉም አካላት ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል" ብለዋል።
የተለያዩ አገራት መሪዎች የሰላም ዕቅዱን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ደኅንነት ኃላፊ እንዳሉት የመጀመሪያው ዙር ውይይት ታጋቾችን ማስለቀቅ ላይ ያተኮረ ነው።
ሐማስ የመጀመሪያውን ደረጃ እንዲያጠናቅቅ ጥቂት ቀናት እንደሚሰጡት ተናግረዋል።
ጦርነቱን ለማስቆም ተስፋ የተጣለበት የሰላም ዕቅድ ስኬታማ ከሆነ ትልቅ እርምጃ ይሆናል።
የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ፣ የትራምፕ ልጅ ባለቤት ጃሬድ ኩሽነር እና የካታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼኽ መሐመድ ቢን አብዱልራሕማን አል ታሒኒ በውይይቱ ይገኛሉ።
የጋዛን ጦርነት በማስቆም ውስጥ እጃቸው ያሉ ባጠቃላይ "በአፋጣኝ እንዲሠሩ" ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው አሳስበዋል።
ታጋቾች የሚለቀቁበት የመጀመሪያው የሰላም ዕቅዱ ክፍል "በዚህ ሳምንት ይጠናቀቃል" ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።
"ሐማስ ጠቃሚ በሆኑ ነጥቦች እየተስማማነው ነው። ስምምነት ላይ እንደርሳለን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ" ብለዋል።
ለውይይቱ ቅርብ የሆኑ የፍልስጤም ባለሥልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት ሰኞ ከሰዓት የውይይቱ የመጀመሪያ ዙር የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ማክሰኞ ይቀጥላል።
አል-ቃሕራ የተባለው ለፍልስጤም መንግሥት ቅርብ የሆነው መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው የመጀመሪያው ቀን ውይይት "በአወንታዊ ሁኔታ" ተጠናቋል።
ትራምፕ እና ኔታንያሁ የተስማሙበት የሰላም ዕቅድ 48 እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲለቀቁና ግጭት እንዲቆም ያስችላል። ከታጋቾቹ መካከል 20 የሚሆኑን በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
እስራኤላውያን ታጋቾች ሲለቀቁ እስራኤል በምላሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትለቅ ተገልጿል።
ሁለቱም ወገኖች በሰላም ዕቅዱ ከተስማሙ "በአፋጣኝ ወደ ጋዛ ሰርጥ ሰብአዊ እርዳታ ይገባል" ተብሏል።
ሐማስ ጋዛን በማስተዳደር ሚና እንደማይኖረው የሚገልጸው የሰላም ዕቅዱ፤ በቀጣይ ፍልስጤም እንደ አገር የምትተዳደርበትን በር ይከፍታል።
ኔታንያሁ ግን የፍልስጤምን አገርነት ተቃውመዋል።
ሐማስ የሰላም ዕቅዱ ቅድመ ሁኔታዎች እስከተሟሉ ድረስ ሁሉንም ታጋቾች እንደሚለቅ አስታውቋል።
የጋዛ ሰርጥ "በገለልተኛ ፖለቲከኞች እንዲመራ" የሚያስችል ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ተጠቁሟል።
ይህ አስተዳደር በፍልስጤማውያን ብሔራዊ ስምምነት ያለው እና በአረብ አገራት የሚደገፍ መሆኑ ተገልጿል።
ሐማስ የሰላም ዕቅዱን በተመለከተ ያወጣው መግለጫ ትጥቅ ማውረድን በተመለከተ በቀጥታ ያለው ነገር የለም።
ጋዛን ለወደፊት ማን ያስተዳድራታል የሚለውን በሚመለከት "የፍልስጤማውያንን መብት ባስጠበቀ ሁኔታ ብሔራዊ ውይይት እየተካሄደ" እንደሚገኝና ሐማስም የውይይቱ አካል እንደሆነ ገልጿል።
ሐማስ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው በሰላም ዕቅዱ ላይ "ቀይ መስመሮች" በሚል የማይቀበላቸው ነጥቦች በግልጽ አለማስቀመጡ የውጭ ጫና እንደበረታበት ያሳያል ተብሏል።
የአውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች የሰላም ዕቅዱን ይደግፋሉ።
እስራኤል በይዞታ ሥር ያደረገችውን ዌስት ባንክ የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አመራር የትራምፕን የሰላም ዕቅድ "እውነተኛና ቆራጥ" ብሎታል።
ሐማስን በዋናነት የምትደግፈው ኢራንም ለሰላም ዕቅዱ ድጋፍ እንዳላት ጠቁማለች።
እስራኤል አሁንም በጋዛ ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው።
የጋዛ ሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ማሕሙድ ባሲል ለቢቢሲ "ከአራት ሳምንታት ወዲህ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ጋዛ እንዳይገቡ ተከልክሏል" ብለዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ለመፈናቀል ተገደዋል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 21 ፍልስጤማውያን እንደተገደሉና 96 የሚደርሱ እንደተጎዱ ተገልጿል።