መንግሥት "በውጭ ምንዛሪ አሻጥር" የጠረጠራቸውን 112 ሰዎችን ሲይዝ ከ500 በላይ አካውንቶችን አገደ

በሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የባንክ አካውንቶች መታገዳቸውን የመንግሥት የፀጥታ እና ደኅንነት አካላት አስታወቁ።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የክልል የፀጥታ ተቋማት በወሰዱት እርምጃ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች እና አካወንቶች ናቸው ለእስር እና ለዕግድ የበቁት።

የፀጥታ ተቋማቱ በወሰዱት እርምጃ 112 የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው እና ኢትዮጵያውያን በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ መሆናቸውን እና ከዚሁ ጋር በተያያዘ 519 የባንክ አካውንቶች መታገዳቸው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገለግሎት ገልጿል።

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የመንግሥትን "የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመጻረር በተደራጀ መንገድ በሚፈጽሙ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮች" ላይ ተሰማርተው እንደነበር ተነግሯል።

ተጠርጣሪዎቹ ሕገ ወጥ የሃዋላ ሥራ፣ የገንዘብ ዝውውር፣ የውጭ ምንዛሪ ስወራ፣ የግብር ስወራ፣ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማስመሰል እና በሌሎች ወንጀሎች "በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ እንዲሁም አሸባሪዎችን እና የታጠቁ ቡድኖችን ሲደግፉ ነበር" ሲል የአገልግሎቱ መግለጫው ጠቅሷል።

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች በሕ ገወጥ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች፣ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች፣ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎች፣ ሕገ ወጥ የሃዋላ አዘዋዋሪዎች እና ደላላዎች መሆናቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም መግለጫው በወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ አሻጥር የፈጸሙ አስመጪዎች እና ላኪዎች፣ ሕጋዊ ንግድ ሳይኖራቸው በሕገ ወጥ ሃዋላ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ገንዘብ በማንቀሳቀስ በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ ላይ እርምጃ ተወስዷል ብሏል።

ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥም ከውጭ የሚላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በዚያው እንዲቀር በማድረግ ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው ሕገ ወጥ የሃዋላ አሰተላላፊዎች እንዲሁም ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎችን ሲጠቀሙ የነበሩ እንዳሉበት አመልክቷል።

በተጨማሪም የብሔራዊ ባንክ ሕግን በሚጥስ ሁኔታ እና ያለምንም ፈቃድ የክሪፕቶከረንሲ መተግበሪያን በመጠቀም በሕገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪን ሲያዘዋውሩ የነበሩ ግለሰቦችም እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተገልጿል።

በፀጥታ ተቋሙ እርምጃውን በተመለከተ ከወጣው መግለጫ ጋር የበርካታ ተጠርጣሪዎች ፎቶግራፍ እና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የተለያዩ ሰነፎች ንብረቶች ይፋ ተደርገዋል።

በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ያስተላልፋሉ ባሏቸው የሃዋላ ተቋማት፣ ገንዘብ ላኪዎች እና ተቀባዮች ላይ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ መሆኑን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

ገዢው በወቅቱ ለሽብርተኝነት ገንዘብ ማስተላለፍ ወይም ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሰማሩ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት እንዳሉ መንግሥት እንደደረሰበት እና "የተቀናጀ፣ ሰፊ እርምጃ" ለመውሰድ መዘጋጀቱን አመልክተው ነበር።