ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራትን የዕድገት ትንበያ ከፍ አደረገ
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በዚህ ዓመት ፈጣን የሆነ የ3.8 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግቡ የዓለም ባንክ አስታወቀ።
ፖሊሲ አውጪዎች የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የወሰዱትን እርምጃ እንደ አንድ ምክንያት ያቀረበው የዓለም ባንክ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ዕድገቱ እንደሚቀጥል ጠቁሟል።
ዕድገቱ በሚያዝያ ወር ከነበረው 3.5 በመቶ የጨመረው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የውጭ ምንዛሪ እና የዋጋ ንረትን በማረጋጋት እና የወለድ ቅነሳ በመከናወኑ ነው ሲል ባንኩ በየሁለት ዓመቱ በሚያወጣው የአፍሪካ ፑልስ ዘገባው አመልክቷል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ "እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች የግል ፍጆታ እና ኢንቨስትመንት እንዲጨምር እያደረጉ ነው" ሲል ባንኩ በሪፖርቱ አስፍሯል።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ወደ 4.4 በመቶ ከፍ እንደሚል ባንኩ ገልጿል። ይህም 4.3 በመቶ ከነበረው የመጀመሪያው ትንበያ ከፍ ያለ ሆኗል።
የዓለም ባንክ፤ ከቀጣናው 47 አገራት መካከል የ30 አገራት ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ትንበያ ከፍ ተደርጎ ተሻሽሏል ሲል በሪፖርቱ አመልክቷል።
"አማካዩ የዋጋ ግሽበት ከ4% ያነሰ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ተዳክመው የነበሩት አብዛኛዎቹ መገበያያ ገንዘቦች አሁን አገግመው ተረጋግተዋል" ሲሉ በዓለም ባንክ የአፍሪካ ዋና ኢኮኖሚስት አንድሪው ዳባለን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
በቀጣናው ትልልቅ ምጣኔ ሃብት አላቸው ከሚባሉት መካከል የሆኑትን የኢትዮጵያን፣ የናይጄሪያን እና የአይቮሪ ኮስትን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ትንበያዎች ባንኩ አሻሽሏል።
የዜጎች ገቢም በዚህ ዓመት እና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በፍጥነት ያድጋል ሲል የአለም ባንክ ማስታወቁን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሪፖርቱ አክሎም፤ "ይህ ምጣኔ ሃብቱ ከአሥር ዓመታት ተከታታይ መዳከም በኋላ ቀስ በቀስ ማገገሙን የሚያመለክት ቢሆንም፣ መልሶ ማንሰራራቱ በአስተማማኝ ሁኔታ የፀና አይደለም" ሲል አስታውቋል።
የቀጣናው ምጣኔ ሃብት በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፖሊሲዎች ምክንያት በተፈጠረ የንግድ አለመረጋጋት እየተፈተነ መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም፤ ከፍተኛ የብድር ጫና እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ አጥነት ለአካባቢው አገራት ስጋት መሆኑን ጠቁሟል።
በዩናይትድ ስቴትስ እና በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው ቁልፍ የንግድ ስምምነት የሆነው አጎዋን በተመለከተ፤ "የንግድ ተግዳሮቶች አሁንም በጉልህ ይታያሉ። ይህ እንዴት እንደሚፈታ አናውቅም። ብዙ ድርድሮች እየተደረጉ ነው" ሲሉ በዓለም ባንክ የአፍሪካ ዋና ኢኮኖሚስት አንድሪው ዳባለን ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ፤ መንግሥታት አነስተኛ እና መካከለኛ ኩባንያዎችን ለማጎልበት የንግድ ሁኔታን በማሻሻል የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ላይ እንዲያተኩሩ አሳስቧል።
በዓለም ባንክ የአፍሪካ ዋና ኢኮኖሚስት አንድሪው ዳባለን "እነዚህ ሥራዎች ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኙ እና አስተማማኝ ሕይወት የሚፈጥሩ መሆን አለባቸው" ብለዋል።
አክለውም፤ በአገራቱ ውስጥ ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል ሦስት አራተኛው የሚሆነው መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የሥራ ዕድል አለመኖር እና ሌሎች ቅሬታዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኬንያ፣ በናይጄሪያ እና በማዳጋስካር በወጣቶች የተመሩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ቀስቅሰዋል።
ይህም ፖሊሲ አውጪዎች ያለባቸውን ፈተና ያሳያል።
"እነዚህን ችግሮች አለመፈታት የሚያስከትለውን መዘዝ ለማስላት አስቸጋሪ ነው። ምልክቶቹንም ማየት የጀመርን ይመስለኛል" ብለዋል አንድሪው ዳባለን ።