ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ብሔራዊ ባንክ በሕገ ወጥ የገንዘብ አስተላላፊዎች ላይ "ሰፊ" እና "የተናበበ" እርምጃ ልወስድ ነው አለ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ያስተላልፋሉ ያላቸው የሀዋላ ተቋማት፣ ገንዘብ ላኪዎች እና ተቀባዮች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ሊወስድ መሆኑን በድጋሚ አስጠንቅቋል።
ለሽብርተኝነት ገንዘብ ማስተላለፍ ወይም ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሰማሩ "የተወሰኑ" ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት እንዳሉ ደርሰንበታል ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ በእነዚህ አስተላላፊዎች ላይ "በጣም የተናበበ፣ የተቀናጀ፣ ሰፊ እርምጃ" ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
"በሕጋዊ መንገድ አልሰራም፤ ከሕግ ውጭ እሄዳለሁ የሚሉት [ላይ] በእጃችን ላይ ያሉትን ማንኛውንም አቅም ተጠቅመን ይህንን የምናስቆም ነው የሚሆነው። ስለዚህ በዚህ ሥራ የተሰማሩ በሙሉ እንዲታቀቡ ማሳሰብ እፈልጋለሁ" ሲሉ "የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ" ሰጥተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው ይህን ያሳወቁት ከባንኮች ማኅበር የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ከሚገኙ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር "ውይይት" ካደረጉ በኋላ ለአራት ደቂቃ ገደማ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ነው።
ሕገ ወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ላይ የተሰማሩ የሀዋላ አስተላላፊዎች "የመጨረሻ ማስጠንቀቂያቸው ነው" ሲሉ ያሳሰቡት ገዢው "ጥንቃቄ" እንዲያደርጉ "ከወዲሁ" አሳስበዋል።
"የብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ የሚቆጠብ አይሆንም። አካውንት በመዝጋት ብቻ የሚመለስ እንዳልሆነም በግልፅ ማንሳት እፈልጋለሁ" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ይሁን እንጂ ዶ/ር እዮብ እንወስደዋለን ስላሉት እርምጃ አፈፃፀምም ሆነ ሌላ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ባለፈው ዓመት መጨረሸ ላይ ባንኩ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ አውጥቶ የነበረ ሲሆን፤ መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉ አራት የሀዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን በስም ዘርዝሮ፤ "በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ የማስመሰል እና ሕገ ወጥ ተግባራትን ፋይናንስ ማድረግ" ላይ እየተሳተፉ ነው ሲል ከስሷል።
በዚህ ክሱ ባንኩ በዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች ያሉ ገንዘብ አስተላላፊዎችን አካትቷል።
ብሔራዊ ባንክ እወስደዋለሁ ያለው "ሰፊ፣ የተናበበ እና የተቀናጀ" እርምጃ ገንዘብ አስተላላፊዎች ላይ ብቻ እንደማይገታ አስታውቀዋል።
"ተቀባዮችንም ያካተተ፤ ላኪዎችን ያካተተ ሰፊ የማጥራት ሥራ ሰርተናል። ወደ ተቀናጀ እርምጃ እየገባን ነው። ስለዚህ ገንዘብ በእነዚህ ሕገ ወጥ ተቋማት የሚልኩ ዜጎቻችንም ከዚህ እንዲቆጠቡ ማሳሰብ እፈልጋለሁ። ከእነዚህ [ተቋማት] ጋር የሚሰሩ በተለያዩ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አስመጪ እና ላኪዎችም ከዚህ ሥራ እንዲቆጠቡ ማሳሰብ እፈልጋለሁ።"
ዶ/ር እዮብ እንወስደዋለን ያሉት እርምጃ "የማያዳግም" መሆኑን ጠቁመው፤ "የኢትዮጵያን ሕግ የጠበቀ፤ የዓለም አቀፍ ሕግን የጠበቀ፤ የተናበበ እርምጃ" እንደሆነም ተናግረዋል።
በአገር ውስጥ "ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት አለ" ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ የማዕከላዊ ባንኩ የመጠባበቂያ ክምችቱ "በጣም እየጨመረ ነው" ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የሚያጫርተውን የውጭ ምንዛሬ እና የአገሪቱን የወጪ ንግድ ትንበያ እንደ መልካም ዕድል ማሳያነት የጠቀሱት ዶ/ር እዮብ፤ "አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን" ሲሉ በራቸው ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።