የአእላፋት ዝማሬ: በገና ዋዜማ በመስቀል አደባባይ የተካሄደው ሥነ ሥርዓት በምሥል

በየዓመቱ ለገና በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የኢትዮጵያዊው ጀንደረባ ትውልድ ማኅበር የሚያዘጋጀው የአእላፋት ዝማሬ ሥነ ሥርዓት ታኅሳስ 28/2018 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ተካሂዷል።

ይህ በመስቀል አደባባይ የተካሄደው መንፈሳዊ ዝግጅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የበርካቶችን አድናቆት አግኝቷል።

በዝግጅቱ ላይ የተዋጣላቸው ድንቅ መንፈሳዊ ዝማሬዎች እና ማራኪ ትዕይንቶች ቀርበውበታል።

በገና በዓል ዋዜማ ለሦስት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የእምነቱ ተከታዮችን በማሳተፍ የሚካሄደው ይህ መንፈሳዊ የአደባባይ ዝግጅት በዚህ ዓመት ከቀደሙት በተለየ በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን የተካሄደ ሲሆን፣ አሁን በከተማዋ ትልቁ በሆነው መስቀል አደባባይ በነጫጭ አልበሳት የተዋቡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ዋዜማ በተለየ ሥነ ሥርዓት አክብረውታል።

ይህ ዝግጅት ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ቴሌቪዥን እና በሌሎችም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም በበርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በቀጥታ ሲተላለፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ተመልክቶታል።

ዓመታዊው የአእላፋት ዝማሬ የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ለማክበር እጅግ በጣም ብዙ ምዕመናን የሚታደሙበት እና መነሻውም "ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ መላዕክት እና እረኞች ያሰሙትን ዝማሬ መሠረት በማድረግ" ታዳሚው ከመመልከት ባሻገር በጸሎት እና በዝማሬው ተሳታፊ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

በገና በዓል ዋዜማ በሚካሄደው የአእላፋት ዝማሬ ላይ የሚሳተፉ ታዳሚዎች የሚያጠኗቸው የቤተ ክርሥቲያኗን ሥርዓት እና ደንብ የተከተሉ ዝማሬዎች ቀደም ብሎ በተለያዩ የበይነ መረብ መድረኮች ላይ ስለሚቀመጡ በቀላሉ እንዲያገኙት ይደረጋል።

የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ማኅበር እንደሚለው ማክሰኞ ታኅሣሥ 28/2018 ዓ.ም. በተካሄደው የአእላፋት ዝማሬ ሥነ ሥርዓት ላይ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በመስቀል አደባባይ ታዳሚ ሆነው ነበር።

በአገሪቱ ከሚገኙ ዋና ዋና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቀዳሚ ሽፋን ያገኘው ይህ የአእላፋት ዝማሬ ዝግጅትን የሚያሳዩ ድንቅ ቪዲዮዎች እና ምሥሎች በሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ መድኮች ላይ በስፋት እየተጋሩ ይገኛሉ።

በተለያዩ አካባቢዎች ሆነው ዝግጅቱን የተመለከቱ በርካታ ሰዎች ሥነ ሥርዓቱ የፈጠረባቸውን ስሜት እና አድናቆት ሲገልጹ ነበር።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በማስመልከት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተካሄደው "የአእላፋት ዝማሬ" ድንቅ ነው" በማለት ከተማዋንም እንዳደመቃት ምስክርነት ሰጥተዋል።

በትልቁ የአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተሰናደው ሥነ ሥርዓት በአግባቡ የታሰበበት እና የተዘጋጀ በሥርዓት የተመራ መሆኑ ብዙዎችን አስደንቋል።

በቪዲዮዎች እና በፎቶግራፎች ላይ እንደታየው የመድረኩ ዝግጅት የታዳሚው ቦታ አያያዝ የሥነ ሥርዓቱ ቅደም ተከተል ማራኪ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት አድርጎት የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

*ሁሉም ፎቶዎች የአእላፋት ዝማሬ አዘጋጅ ከሆነው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ማኅበር በተገኘ ፈቃድ የቀረቡ ናቸው።