በኬንያ በቆሻሻ መጣያ ስፍራ የበርካታ ሴቶች አካል ተቆራርጦ ተጥሎ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኬንያ ፖሊስ ቅዳሜ ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም. በመዲናዋ ናይሮቢ በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በተቆራረጡ የሴቶች አካላት የተሞሉ 5 ከረጢቶች ማግኘቱን አስታወቀ።
በቆሻሻ መጣያው ስፍራው በሰው አካላት የተሞሉ ከረጢቶች የተገኙት ፖሊስ አርብ ዕለት የሌሎች የ6 ሴቶች አስክሬን በከረጢት ውስጥ ሆኖ ማግኘቱን ተከትሎ በተደረገ ፍለጋ ነው።
ቅዳሜ ዕለት የተገኙት ከረጢቶች ውስጥ የተቆራረጡ የሰውነት ክፍሎች መገኘታቸውን የገለጹት የፖሊስ ኃላፊዎች፤ ሰዎቹ ህይወታቸው ያለፈው ከባዕድ አምልኮ ወይም ከተቀናጀ የግድያ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የአገሪቱ የፖሊስ ተቆጣጣሪ አካል በሰዎቹ ሞት የፖሊስ ተሳትፎ መኖሩን አለመኖሩን እየመረመረ መሆኑን ባለፈው አርብ አስታውቋል። ይህ የሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጸረ-መንግስት ሰልፎች ላይ የፖሊስ መኮንኖች ሰፊ የሰብአዊ መብት ረገጣ ፈጽመዋል በሚል ክስ እየቀረበባቸው በሚገኝበት ወቅት ነው።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ፖሊሶች የግብር ጭማሪዎችን በመቃወም አደባባይ የወጡ በርካታ ሰዎችን በጥይት መትተዋል ብለዋል። የተወሰኑት ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ደግሞ በማፈን ወይም በዘፈቀደ በማሰር ፖሊስን ወንጅለዋል።
የተቆራረጡ የሴቶች አካላት በቆሻሻያ መጣያ ስፍራ ተጥሎ የሚገኘቱ ዜና ኬንያውያንን አስቆጥቷል።
በዜናው የተቆጡ እና በቆሻሻ ስፍራው የተገኙ ተቃዋሚዎች በሰው አስከሬን የተሞሉትን ከረጢቶችን እንከፍታለን በማለታቸውን ፖሊስ ቅዳሜ ዕለት አድማ በታኝ ኃይሎችን ወደ ስፍራው ለማሰማራት ተገዶ ነበር።
የአገሪቱ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት (ዲሲአይ) ኃላፊዎች ሰዎች ተረጋግተው ጉዳዩ እንዲያጣራ ዕድል እንዲሰጡ ከማሳሰብ ባለፈ ተቃዋሚዎቹ ለምርመራቸው እንቅፋት ሆነዋል ሲሉ ከሰዋል።
ገለልተኛው የፖሊስ ቁጥጥር ባለስልጣን (አይፒኦኤ) በበኩሉ በግድያዎቹ ውስጥ የፖሊስ ተሳትፎ መኖር አለመኖሩን እያጣራሁ ነው ብሏል።
በናይለን ገመድ በታሰሩ ከረጢቶች ውስጥ የተገኙ አስከሬኖች ላይ "የማሰቃየት እና የአካል ጉዳት ምልክቶች ነበሩት" ያለው ተቋሙ፤ አስከሬኖቹ የተጣሉበት ቦታ በአካባቢው ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ 100 ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
አክሎም “ፖሊስ በህገ-ወጥ እስራት እና አፈናዎች ውስጥ ተሳትፏል የሚሉ ውንጀላዎች” በመኖራቸው በዚህ ውስጥ የፖሊስ እጅ ስለመኖሩ ለማረጋገጥ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ እያደረኩኝ ነው ብሏል።
የኬንያ የፖሊስ አባላት ከህግ ውጭ ግድያ ጋር በተያያዘ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ይከሰሳሉ።
ከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኙት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከግድያው ጀርባ ያሉ አካላት እንደሚቀጡ ቃል ገብተዋል።
"እኛ በህግ የበላይነት የምንመራ ዲሞክራሲያዊ አገር ነን። በናይሮቢ እና በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል በተፈጸሙት ሚስጥራዊ ግድያዎች የተሳተፉ አካላት በህግ ይጠየቃሉ" ሲል ኤክስ ላይ አስፍረዋል።












