ሩሲያ በዩክሬን የኃይል ማመንጫዎች ላይ 'ከባድ' ጥቃቶችን ሰነዘረች

የዩክሬን የኃይል አውታር ላይ ባነጣጠረ ጥቃት ሩሲያ በአገሪቱ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ከባድ ጥቃት አደረሰች።

ሩሲያ ባለፉት ሦስት ወራት በኃይል መሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ጥቃት ስትፈጽም የአሁኑ ለስምንተኛ ጊዜ መሆኑን የዩክሬን ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የአየር መከላከያ መሣሪያዎች ሩሲያ በተለያዩ ግዛቶች ካስወነጨፈቻቸው 16 ሚሳኤሎች 12ቱን እንዲሁም ደግሞ 13 ሰው አልባ አውሮፕላኖች መትቶ መጣሉን የዩክሬን አየር ኃይል አስታውቋል።

ቅዳሜ ዕለት በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን በምትገኘው ካርኪቭ በሩሲያ ቦምቦች ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ 18 የሚሆኑት መቁሰላቸውን ባለስልጣነት ተናግረዋል። በከተማው ውስጥ ቢያንስ አራት ፍንዳታዎች ተሰምተዋል ተብሏል።

“ይህ አንድ ተጨማሪ የሽብር ጥቃት ነው። በሲቪል መሠረተ ልማት ላይ የተደረገ ጥቃት። በአካባቢው ምንም አይነት ወታደራዊ ዒላማ የለም" ሲሉ የካርኪቭ ክልል አስተዳዳሪ ኦሌህ ሲኒዬሁቦቭ ተናግረዋል።

በመሰረተ ልማት ላይ በተፈጸመው ጥቃት በማዕከላዊ ዛፖሪዝሂያ ክልል ውስጥ ሁለት የመብራት ኃይል ሠራተኞችን ሲያቆስል፤ በምዕራብ የላይቪቭ ከተማ ደግሞ ጉዳት ማድረሱን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢቫኖ-ፍራንኪቭስክ ደግሞ በመኖሪያ ቤቶች እና በመዋለ ሕጻናት ላይ ጉዳት መድረሱን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ሩሲያ በዩክሬን የኃይል አውታሮች ላይ ጥቃት በድጋሚ በማድረሷ በመላ ዩክሬን ኃይል ደጋግሞ እንዲቋረጥ አስገድዷል።

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በቅርቡ እንደገለጹት ሞስኮ የአገራቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጫ ተቋማት ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ማጥቃት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ግማሹን ከጥቅም ውጭ አድርጋለች።

የዩክሬን ባለስልጣናት እንደገለጹት ከሆነ ሐሙስ ዕለት ሰባት ሠራተኞች ቆስለዋል። የኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጨምሮ የኢነርጂ መሠረተ ልማት በአንድ ሌሊት በተፈጸመባቸው ከባድ ጥቃት ተጎድትዋል።

ዩክሬን ከአውሮፓ ኅብረት አገራት ሃይል እየገዛች ቢሆንም ይህ ግን ጉድለቱን ለማሟላት በቂ አይደለም ተብሏል።

ይህ ማለት እንደ ሆስፒታሎች እና ወታደራዊ መገልገያዎች የመሳሰሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ ሲባል በአብዛኛው ቀናት በአገር አቀፍ ደረጃ የኃይል መቋረጥ ይኖራል።

ከዩክሬን ትላልቅ የግል ኢነርጂ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው የዲቲኢኬ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማክሲም ቲምቼንኮ “ሰማያችንን በአስቸኳይ መዝጋት አለብን ወይም ዩክሬን በዚህ ክረምት ከባድ ቀውስ ይገጥማታል” ብለዋል ።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የዩክሬን አጋሮች ተጨማሪ የአየር መከላከያ መሣሪያዎችን እንዲያቀርቡ ደጋግመው ጠይቀዋል።

የዛፖሪዝሂዝያ ገዥ የሆኑት የኢቫን ፌዶሮቭ በቴሌግራም ባስተላለፉት መልዕክት የዜሌንስኪን ጥያቄ አስተጋብተዋል።

"በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ጠላት መቼም አያቆምም። ዩክሬን የአየር መከላከያ መሣሪያዎች ያስፈልጓታል” ብለዋል።