በዘንድሮው የሐጅ ጉዞ ለምን በርካታ ሰዎች ሞቱ? የዐይን ምስክሮችስ ምን ይላሉ?

የዘንድሮው የሐጅ ጉዞ የተጠናቀቀው በአሳዛኝ ሁኔታ ነው። እንደ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ የተለያየ አገራት ዜግነት ያላቸው ቢያንስ 922 ሐጃጆች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የአብዛኞቹ ሞት ምክንያትም ከከፍተኛ ሙቀት ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

በዓለማችን በርካታ ሕዝብ ከሚታደምባቸው ሁነቶች ውስጥ አንዱ በሆነው የሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይጓዛሉ።

የገንዘብ አቅም ያላቸው እና መሄድ የቻሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሕይወት ዘመናቸው አንዴ የሚያደርጉትን ይህ ሃይማኖታዊ ግዴታ ረቡዕ ዕለት በይፋ ተጠናቋል።

በዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ቢቢሲ በገለልተኝነት አላረጋገጠም።

የሟቾች ቁጥርን በተመለከተ እንዲሁም አዘጋጆቹ እየቀረበባቸው ባለው ቅሬታ ላይ የሳዑዲ ባለሥልጣናት አስተያየት እንዲሰጡ ቢቢሲ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

ሆኖም ሳዑዲ ለዘንድሮው የሐጅ ጉዞ ይዞት የነበረው የጤና ዕቅድ ግቡን መምታቱን ገልጿል።

የሳዑዲ ጤና ሚኒስትር ፋህድ አል ጃላየል “ከሐጃጆች ቁጥር እና ከሙቀቱ ጋር በተያያዘ ከገጠሙ ፈተናዎች በስተቀር የሐጅ ወቅት ከየትኛውም ወረርሽኝ እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶች ነጻ ነው” ብለዋል።

የሳዑዲ ባለሥልጣናት እንዳሉት በዚህ ዓመት በሐጂ ሥነ ሥርዓት ላይ 1.83 ሚሊዮን የሚሆኑ ምዕመናን የተሳተፉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 1.6 የሚሆኑት የሌሎች አገራት ዜጎች ናቸው። በርካታ አማኞች ከተጓዙባቸው አገራት መካከልም ፓኪስታን፣ ዮርዳኖስ እና ቱኒዚያ ይገኙባቸዋል።

ሚሊዮኖች በተገኙበት በዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ በርካቶች ሕይወታቸውን ያጡበትን ምክንያቶች ቢቢሲ ተመልክቷል።

ከፍተኛ ሙቀት

ለተጓዦች በተዘጋጁ መጠለያዎች ውስጥ 51.8 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚደርሰው የሳዑዲ ሙቀት በበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።

የሳዑዲ ባለሥልጣናት ሐጃጆች ለሙቀት እንዳይጋለጡ እና በቂ ፈሳሽ እንዲወስዱ ቢያስጠነቅቁም በርካቶች በከፍተኛ ሙቀት (ሂት ስትሮክ) ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አንድ የአረብ ዲፕሎማት ሙቀቱ ከፍተኛ በሆነበት ወቅት ሕይወታቸው ባለፈ 658 ግብፃውያን ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥ በርካቶቹ ትክክለኛ የሐጅ ፈቃድ የሌላቸው ሲሆኑ፣ ይህም በቂ የሕክምና እና ሌሎች ድጋፎች እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።

አይሻ ኢድሪስ የተባለች ናይጄሪያዊት ሐጃጅ “በፈጣሪ ምህረት ነው የተረፍኩት። ሙቀቱ ኃይለኛ ነበር” ስትል ለቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ኒውስዴይ ተናግራለች።

“በመካ በሚገኘው መስጊድ ወደ ከዓባው የሚያስገባውን ሁሉንም በሮች ዘግተውት ስለነበር ከፍተኛ ሙቀት ያለውን የመጨረሻ ጣሪያ (ሩፍ ቶፕ) ለመጠቀም ተገደን ነበር” ብላለች።

“ጃንጥላ መጠቀም እና ያለማቋረጥም በዘምዘም ውሃ ራሴን ማቀዝቀዝ ነበረብኝ። የሆነ ሰዓት ላይ ግን ራሴን ልስት ደርሼ ነበር። የሆነ ሰው መጥቶ ጃንጥላ ዘርግቶልኝ ነው ተንፈስ ያልኩት። እንደዚያ የከፋ ሙቀት አልጠበቅኩም ነበር።”

ኔኢም የተባሉ ሌላ ሐጃጅም በሙቀት ምክንያት መሞታቸው ተዘግቧል።

“ከእናቴ ጋር ያለኝ ግንኙነት ድንገት ተቋረጠ፤ ለቀናት ስንፈልጋት ነበር። ከዚያም በሐጅ ወቅት ሕይወቷ ማለፉን ተረዳን” ሲል ልጃቸው ለቢቢሲ የአረብኛ ዜና አገልግሎት ተናግሯል።

ጨምሮም እናታቸው በመካ ለመቀበር የነበራቸውን ፍላጎት እንደሚያከብሩም ገልጿል።

ሐጃጆች ብዙም ባልለመዱት ሙቀት፣ በአድካሚ የእግር ጉዞ፣ መተፋፈግ ምክንያት እንዲሁም እና በርካቶች አረጋውያን እና ታማሚዎች በመሆናቸው አደጋ ገጥሟቸዋል።

በሐጅ ወቅት በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ የሚከሰት ሞት አዲስ አይደለም። ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲያጋጥም የኖረ ነው።

ባለፈው ዓመት ከ2 ሺህ በላይ ሐጃጆች በሙቀት ሳቢያ ለህመም ተዳርገው እንደነበር የሳዑዲ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ተመራማሪዎችም የዓለም ሙቀት መጨመር በሐጅ ወቅት ያለውን ሁኔታ ሊያባብሰው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የአየር ንብረት ተንታኙ ካርል ፍሬዲሪክ “የሐጅ ሥርዓት ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ በሞቃታማ የአየር ሁኔታ ወቅት የሚከናወን ሲሆን፣ የአየር ንብረት ለውጡ ሁኔታውን አባብሶታል” ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የዓለም ሙቀት መጠን በ1.5 ሴሊሺየስ መጨመሩን እና በሐጅ ወቅት ለከፍተኛ ሙቀት (ሂት ስትሮክ) የመጋለጥ አደጋ በአምስት እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል በጥናታቸው አመልክተዋል።

አሁን ላይ ያለው ትንበያም በ2030ዎቹ ዓለም በ1.5 ሴሊሺየስ ሙቀት ልትመታ እንደምትችል የጠቆመ ሲሆን፣ የወደፊት የሐጂ ተጓዦችን ፈተና እንደሚያብሰው ገልጿል።

መተፋፈግ እና የንጽህና ጉድለት

በርካታ ምንጮች እንደሚሉት የሳዑዲ ባለሥልጣናት ትክክለኛ ያልሆነ የሐጅ ጉዞ አስተዳደር ሁኔታውን አክፍቶታል።

እነዚህ ሐጃጆች እንደሚሉት የተዘጋጁት የእንግዳ ማረፊያዎች እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በቂ ማቀዝቀዣ እና መታጣቢያ ቤቶች የሌላቸው እና በሰዎች የተጨናነቁ ናቸው።

ከፓኪስታኗ ኢስላማባድ ከተማ ወደ መካ ያቀናችው የ38 ዓመቷ አሚና [ስሟ የተለወጠ] እንደምትለው እርሷ ባረፈችበት ድንኳን የአየር ማቀዝቀዣ አልነበረም። የተገጠሙት የውሃ ማቀዝቀዣዎችም ብዙውን ጊዜ ውሃ አልነበራቸውም።

“በእነዚህ ድንኳኖች መተፋፈግ ነበር። በላብ እንዘፈቅ ነበር። በጣም አሰቃቂ ሁኔታ ነበር የነበረው” ብላለች።

ፋውዚያህ የተባለች ከኢንዶኔዢያ ጃካርታ የሄደች ሐጃጅ በበኩሏ በድንኳኖች ውስጥ በርካታ ሰዎች በሙቀት እና በመተፋፈግ ምክንያት ራሳቸውን ሲስቱ መመልከቷን ተናግራለች።

“እስከ ሌሊት ድረስ እራት እንጠብቅ ነበር። በድንኳኑ ውስጥ በርካቶች በረሃብ ሲንገላቱም ነበር” ስትል አክላለች።

ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ መሻሻሎች እንዳሉ እና የተሻለ ቅንጅት የታየበት የሐጅ ሥርዓት እንደሆነ ታምናለች።

የትራንስፖርት እጦት

ሐጃጆች በከፍተኛው ሙቀት ረዥም ርቀት በእግራቸው እንዲጓዙ ይገደዳሉ። ለዚህም የመንገዶች መዘጋጋት እና የትራንስፖርት አገልግሎት አስተዳደር ደካማ መሆኑ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ፓኪስታናዊ ሐጃጅ “ያለምንም ውሃ እና ጥላ ሰባት ኪሎ ሜትር እንድንጓዝ ተደርገናል። ፖሊስ በየመንገዱ ባስቀመጣቸው ኬላዎች ምክንያትም አላስፈላጊ ርቀቶችን እንድንጓዝም ተደረግናል” ብለዋል።

እንደ ግለሰቧ ከሆነ የሳዑዲ መንግሥት ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ሲሰጡ የነበረ ቢሆንም፣ የታመሙ እና በሙቀቱ ምክንያት ራሳቸውን ለሳቱ ሰዎች አገልግሎት ሲሰጡ አልነበረም።

“በካምፕ ውስጥ ሰዎች እንደ ዶሮ አሊያም እንደ እንስሳት ነበር የታጎሩት። በአልጋዎች መካከል ለመተላለፍ ምንም አይነት መፈናፈኛ አልነበረም። የተዘጋጁት መታጠቢያ ቤቶች በመቶዎች ለሚቆጠሩት ሰዎች በቂ አልነበሩም” ብላለች።

በግላቸው ለተሰባሰቡ የቡድን ተጓዦች አስተባባሪ የሆኑት ሞሐመድ አቻም የእርሷን ሃሳብ ይጋራሉ።

“የሐጅ ጉዞ ሳስተባብር ይህ 18ኛዬ ነው። ባለኝ ልምድ የሳዑዲ ተቆጣጣሪዎች የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች አይደሉም። ይቆጣጠራሉ ግን እርዳታ አይሰጡም” ሲል ይወቅሳል።

እንደ አቻ ከሆነ በበጋ ወቅት አንድ ሐጅ በቀን ወደ 15 ኪሎ ሜትር በእግር ሊጓዝ ይችላል። ይህም ለከፍተኛ ሙቀት፣ ድካም እና ለውሃ እጥረት ያጋልጣቸዋል።

“ቀደም ባሉት ዓመታት መጠለያ ድንኳናቸውን ቶሎ ለማግኘት የሚረዳው መንገድ ክፍት ነበር። አሁን ላይ ግን ወደዚያ የሚወስዱት ሁሉም መንገዶች ተዘግተዋል። በመሆኑም አንድ ተራ ሐጃጂ ምንም እንኳን ድንኳኑ ቅርብ ቦታ ላይ ቢገኝም ድንኳኑ ጋር ለመድረስ 2.5 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅበታል” ሲልም አላስፈላጊ ርቀት ለመጓዝ እንደሚገደዱ ያስረዳል።

“በዚህ መንገድ ላይ ድንገተኛ አደጋ ቢያጋጥም ለ30 ደቂቃ ያህል ማንም አይደርስም። የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የተሠራ ሥራ አልነበረም። በእነዚህ መንገዶችም ውሃ የሚገኝባቸው ቦታዎች አልነበሩም” ብሏል አቻ።

የዘገየ የሕክምና እርዳታ

በርካታ የሐጅ ተጓዦች በቂ የህክምና ትኩረት አላገኙም።

እንደ ተጓዦች ብዛት በሙቀት ለደከሙ እና ሌሎች የጤና ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች አምቡላንሶች እና የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ዝግጁ አልነበሩም።

አሚና በመተፋፈግ ምክንያት የኦክስጅን እጥረት አጋጥሟቸው የነበሩ ሐጃጅ ጋር በአምቡላንስ ለመድረስ ከ25 ደቂቃ በላይ እንደወሰደ ተናግራለች።

“አምቡላንሱ ከደረሰ በኋላም ዶክተሩ ምንም እርዳታ ሳያደርግላቸው ‘ምንም አልሆኑም’ በማለት ጥሏቸው ሄዷል” ብላለች።

የሳዑዲ ጤና ሚኒስትር ግን የሐጃጆችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን እና እስፈላጊው ነገር መቅረቡን ተናግረዋል።

መንግሥት በሰጠው መግለጫ ከ6500 በላይ አልጋዎችን የሚይዙ እና ከ40 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች የተሰማሩበት 189 ሆስፒታሎች፣ የጤና ማዕከላት እና ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች መዘጋጀታቸውን ገልጿል።

እነዚህ ተቋማት ከ370 በላይ አምቡላንሶች እና ሰባት የአየር አምቡላንሶች ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን፣ 12 የጤና ምርመራ ቤተ ሙከራዎች፣ 60 መድኃኒት እና ቁሳቁስ አቅራቢ ተሽከርካሪዎች እና ሦስት ተንቀሳቃሽ የሕክምና መጋዘኖች በቅዱስ ከተማዋ በሚገኙ ቦታዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጾ ነበር።

የመካ ጤና ቡድን ባለሥልጣንም የሐጅ ወቅት ሲቃረብ ዝግጅታቸውን ጨምረው እንደነበር ገልጸው፣ ሠራተኞችን ሲያሰለጥኑ መቆየታቸውን፣ እንዲሁም በተለያዩ የጤና ተቋማት 654 የጽኑ ሕሙማን አልጋዎችን ጨምሮ 3944 የህሙማን አልጋዎች እንዲዘጋጁ መደረጉን ተናግረዋል።

ሰነድ የሌላቸው ሐጃጆች

አንድ ሰው የሐጅ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ልዩ የሆነ የሐጅ ቪዛ መጠየቅ አለበት። ሆኖም የተወሰኑ ግለሰቦች ትክክለኛ ሰነድ ሳይኖራቸው ይህንን ሃይማኖታዊ ጉዞ ለማድረግ ይሞክራሉ። ይህም የሟቾች ቁጥር ለመጨመሩ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።

እነዚህ ትክክለኛ ሰነድ የሌላቸው ሐጃጆች እርዳታ ቢያስፈልጋቸው እንኳን ባለሥልጣናትን አይጠይቁም።

ባለሥልጣናቱም በርካታ የእንግዶች ማረፊያ ድንኳኖች ለመጨናነቃቸው እነዚህን ተገቢ ሰነድ የሌላቸው ሐጃጆችን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

የኢንዶኔዢያ ብሔራዊ የሐጅ እና ዑምራ ኮሚሽን ኃላፊ ሙስቶሊህ ሲራጅ “የሐጅ ቪዛ የሌላቸው ግለሰቦች ሐጅ ወደሚደረግባቸው ሥፍራዎች ሰርገው እንደገቡ እንጠረጥራለን” ብለዋል።

ኤኤፍፒም የዜና ወኪል አንድ የአረብ ዲፕሎማትን ጠቅሶ እንደዘገበው በዚህ ወቅት ሕይወታቸው ካለፈ ቢያንስ 658 ግብፃውያን መካከል 630ዎቹ የሐጅ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው።

የሐጅ እና ዑምራ ብሔራዊ ኮሚቴ አማካሪ ሳዓዲ አል ቁራይሺም “የሐጅ ቪዛ የሌላቸውን እንደማይታገሱ እና ወደ አገራቸው መመለስ እንዳለባቸው” ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተገቢ ሰነድ የሌላቸው ተጓዦች ‘ኑሱክ’ በተባለ እና ፈቃድ ያላቸው ተጓዦች ወደ ቅዱስ ሥፍራው ለመግባት በሚያስችላቸው ምሥጢራዊ መለያ [ባርኮድ] ባላቸው ካርዶች አማካኝነት እንደሚለዩም አማካሪው ገልጸዋል።

አረጋውያን፣ የደከሙ ወይም የታመሙ ተጓዦች

በርካቶች የሐጅ ጉዞ የሚያደርጉት ሕይወታቸውን ሙሉ ገንዘብ ሲያጠራቅሙ ቆይተው፣ አሊያም ሞታቸው እንደተቃረበ በማሰብ እዚያ እንዲሞቱ በመሻት ዕድሜያቸው ከገፋ እና ከተዳከሙ በኋላ ነው።

በባንግላዴሽ ባሉ ሙስሊም ማኅበረሰቦች ዘንድ በሐጅ ወቅት የሞተ ሰው ዕድለኛ እንደሆነ ይቆጠራል። በዚያ ወቅት የሞተ ሰው በፈጣሪ ዘንድ የተለየ ሥፍራ እንደሚሰጠውም ይታሰባል።

በየዓመቱ በሐጅ ወቅት ለሚያጋጥሙ ሞቶች ሌላኛው ምክንያትም ይኸው ነው።

ባለፈው ዓመት በነበሩ የሐጅ ጉዞዎች ወቅት ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወት አልፏል።

አንድ ሰው በሐጅ ጉዞ ላይ ሕይወቱ ቢያልፍ ምን ይደረጋል?

አንድ ሰው ሐጅ እያደረገ ባለበት ጊዜ ሕይወቱ ቢያልፍ ሞቱ ለሐጅ ሚሽን ሪፖርት ይደረጋል። እጅ ላይ በሚጠለቀው ወይም አንገት ላይ በሚንጠለጥል መታወቂያ አማካይነት የሟቹ ግለሰብ ማንነት ይለያል። ከዚያም በዶክተር የሞቱ ምክንያት ተለይቶ የሳዑዲ መንግሥት የሞት ምስክር ወረቀት ይሰጣል።

እንደ ሞተበት አካባቢ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ሥፍራ በሚሰጣቸው በመካ በሚገኘው አል ሐራም መስጊድ ወይም በመዲና በሚገኘው የነብዩ መስጊድ የቀብር ዱዓ (ጸሎት) ይደረግለታል።

የሳዑዲ መንግሥት ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ አስክሬኑ ታጥቦ እና ተጠቅልሎ ማቀዝቀዣ ውስጥ ይገባል።

የቀብር ሥነ ሥርዓቱም የሟቹን ማንነት ከሚገልጽ ማስታወሻ ጋር ይፈፀማል። የሟች ቤተሰብ መቃብራቸውን መጎብኘት ከፈለጉ መጎብኘት ይችላሉ።

የሳዑዲ መንግሥት በቀይ ጨረቃ እና በሌሎች ቡድኖች ድጋፍ በሐጂ ጉዞ ላይ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች የቀብር ሥርዓት ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ መፈፀሙን አረጋግጣለሁ ብሏል።