በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ አዲስ መንግሥት ለመመሥረት ምርጫ እየተካሄደ ነው

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዘጠኝ ዓመት በኋላ አዲስ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ደግሞ ያልተሟሉ መቀመጫዎች በሕዝብ ተወካዮች የሚያዙበት ምርጫ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ነው።

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው አገራዊ እና ክልላዊ አጠቃላይ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት በቤኒሻንጉል ክልል ምርጫ ሳይደረግ መቆየቱ ይታወሳል።

በክልሉ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በወቅቱ ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉ ከዘጠኝ ዓመት በፊት የተቋቋመው ምክር ቤት አስካሁን ሲሠራ ቆይቷል። ዛሬ የሚካሄደው ምርጫም ነባሩን ምክር ቤት በመተካት ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች ዘግይቶ አዲስ ክልላዊ መስተዳደር እንዲመሠረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሰኔ 14/2013 ዓ.ም. እና መስከረም 20/2014 ዓ.ም. የተካሄደው ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ባልተካሄደባቸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ዛሬ ሰኔ 16/2016 ዓ.ም. ቀሪ እና የድጋሚ ምርጫን እየተካሄደ ነው።

ከሌሎቹ ክልሎች በተለየ ሁኔታ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ በሆነው በዚህ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤት ክፍት የሆኑ መቀመጫዎች በምርጫው ይሟላሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ክልሉ ከሦስት ዓመት መዘግየት በኋላ አዲስ አስተዳደር በሚቀጥለው ዓመት የሚመሠርት ይሆናል።

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘጠኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 99 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ቀደም ሲል ምርጫ ማካሄድ በተቻላባቸው የክልሉ አካባቢዎች ሦስት የፌደራል እና 28 የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች አሸናፊ ማግኘታቸው ይታወሳል።

ክልሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉት ቀሪ ስድስት መቀመጫዎች ወኪል አልባ ሲሆኑ፣ አብዛኛው ወይም 71 የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች የሕዝብ እንደራሴ ሳይመረጥባቸው ቆይቷል።

የቤንሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን)፣ ኢዜማ፣ አብን እና ብልጽግናን የመሰሉ ፓርቲዎች በተወዳደሩባቸው 28 የክልል ም/ቤት መቀመጫዎች ሁሉንም ብልጽግና አሸንፏል።

በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሠረት ግን ብልጽግና የክልሉን መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ ካለማግኘቱ በተጨማሪ አብዛኛው የምክር ቤቱ ወንበርን በእንደራሴዎች ለማስያዝ የሚያስችሉ ምርጫ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሳይደረግ ቆይቷል።

በዚህ ምክንያትም የክልሉ መስተዳደር የሥልጣን ዘመናቸውን ባጠናቀቁ የም/ቤት አባላት እና ሥራ አስፈጻሚዎች ሲመራ ቆይቷል በማለት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሲተቹ ቆይተው ነበር።

ነገር ግን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው አሁንም በቤንሻንጉልጉሙዝ ክልል 40 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች የፀጥታ ችግር በመኖሩ በዛሬው ዕለት ድምፅ አያሰጥም።

ዛሬ ስድስተኛው አገራዊ ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ የሚካሄደው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ ምርጫ ሳይካሄድባቸው በቀሩ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፉት ቀናት ለምርጫው አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ወደ ተዘጋጁ የምርጫ ጣቢያዎች መሠራጨታቸውን አስታውቋል።