የአርሰናሉ ዚንቼንኮ አገሬ ዩክሬን ጥሪ ብታቀርብልኝ ለመዋጋት እዘምታለሁ አለ

የአርሰናሉ ተከላካይ አሌክሳንደር ዚንቼንኮ አገሬ ዩክሬን ጥሪ ብታቀርብልኝ ለውጊያ ለመዝመት ዝግጁ ነኝ አለ።
የ27 ዓመቱ ዚንቼንኮ ሩሲያ መጠነ ሰፊ ወረራ ከፈጸመችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ለአገሩ ዩክሬን የ1 ሚሊዮን ፓዎንድ ድጋፍ ማድረጉን ለቢቢሲ ተናግሯል።
እግር ኳሰኛው ዩክሬና መላውን አውሮፓ እየተከላከለች ነው ያለ ሲሆን አገሪቱ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋታል ብሏል።
ዩክሬን ሁለት ዓመት ባስቆጠረው ጦርነት ከፍተኛ ሠራዊት የተገደለባት ሲሆን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሠራዊት ቁጥር ለመጨመር የአዲስ ተመልማይ ወታደሮችን የዕድሜ ጣሪያ ከ27 ወደ 25 ዝቅ አድርገዋል።
ዜሌንስኪ ዩክሬን ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮች ያስፈልጋታል ብለዋል።
ዚንቼንኮ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ የዘመቻ ጥሪ ቢቀርብለት በፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋችነቱን ጥሎ ይዘመት እንደሆነ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥም፤ “ለዚህ ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው። ለመዋጋት እየሄዳለሁ” ብሏል።
በጦርነቱ እየተዋጉ ያሉ የቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ እንደሚገኙም ዚንቼንኮ ጨምሮ ተናግሯል።
“በአንድ ኳስ ሜዳ አብሬያቸው ስጫወት የነበሩ ጓደኞቼ አሁን ላይ አገራቸውን እየተከላከሉ እንደሆነ ማሰብ ቀላል አይደለም። እውነት ለመናገር ይህን አምኖ መቀበል ከባድ ቢሆንም ምንም ማድረግ አይቻልም። እጅ መስጠት አንችልም” ብሏል።
ዚንቼንኮ ምንም እንኳ በዩክሬን ያለው ሁኔታ “እጅግ ከባድ” ቢሆንም “በፕሬዝዳንታችን እንኮራለን” ብሏል።
እአአ 2016 ላይ ለሩሲያው ክለብ ኡፋ በመጫወት ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው ዚንቼንኮ፣ በአሁኑ ወቅት ሩሲያውያን ከሆኑ የቀድሞ የክለብ ጓደኞቹ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ይገልጻል።
“ከወረራው በኋላ ትንሽ ሰዎች የጽሑፍ መልዕክት ልከውልኛል። የእነርሱ ጥፋት ስላልሆነ እነርሱን አልወቅስም። ጦርነቱን ተቃወሙ አልላቸውም ምክንያቱም እስር ቤት ሊወረወሩ ይችላሉ።” ብሏል።
ከወረራው በፊት ሩሲያውያን ዩክሬናውያንን “ወንድም እና እህቶቻችን” ይሉ ነበር የሚለው ዚንቼንኮ፣ ከጦርነቱ በኋላ ግን “ሁሉም ዩክሬናውያን የእነርሱ ጓደኞች ልንሆን አንችልም” ሲል ተናግሯል።
“ያደረሱብንን በደል በጭራሽ አንረሳውም። ይህንም ለልጆቼ አስተምራለሁ። ልጆቼም ልጆቻቸውን ያስተምራሉ” ይላል።
እንደ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከሆነ በዚህ ጦርነት 31ሺህ ዩክሬናውያን ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን በሩሲያ በኃይል በተያዙ አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ዚንቼንኮ ጦርነቱ በተጀመረ ወቅት 1ሚሊዮን ፓዎንድ የሚጠጋ ገንዘብ ዩክሬናውያን ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ገንዘብ ልኮ እንደነበረ ተናግሯል።
የአርሰናሉ ተጫዋች በአሁኑ ሰዓት ዩክሬናዊ ከመሆን በላይ ምንም ነገር ሊያኮራኝ አይችልም ካለ በኋላ "ይህ ጦርነት በፍጥነት ቆሞ አገራችንን እንደምንፈልጋት አድርገን እንደምንገነባ ሕልም አለኝ" ብሏል።












