ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ ካላስወጣች ማዕቀብ ሊጣልባት እንደሚችል የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናገሩ
ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ የማታስወጣ ከሆነ ማዕቀብ ሊጣልባት እንደሚችል አንድ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ገለጹ።
በስም ያልተጠቀሱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ፣ ማክሰኞ ኅዳር 06/2015 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ላይ ነው ይህንን የተናገሩት።
ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ ጦር በተጨማሪ የአማራ ልዩ ኃይል እና የአፋር ሚሊሻ በትግራይ ይገኛሉ ያሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የደረሱት የሰላም ስምምነት ኃይሎቹ እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው ሲሉ አስታውሰዋል።
በባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት የኤርትራ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል በመግባት ከፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች ጋር እንደተሰለፈ ሲነገር ቆይቷል። አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን እየሰማን ነው ያሉት ከፍተኛ ኃላፊው፤ የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዳይሆን እንቅፋት በሚሆኑት ላይ ግን ቅጣት ሊጣል እንደሚችል ገልጸዋል።
የሰላም ስምምነቱ እንዲከበር እና ተፈጻሚ እንዲሆን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ “ማዕቀብ ለመጣል አናንገራግርም” ብለዋል።
በስም ያልተጠቀሱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ኃላፊ ይህን ያሉት የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ሂደትን በተመለከተ ለጋዜጠኞች መረጃ በሰጡበት ወቅት ነው።
ኃላፊው በስልክ በሰጡት መግለጫቸው የሰላም ሂደቱ ምን እንደሚመስል እና አሁን ያለበትን ደረጃ አብራርተዋል።
ከስምምነቱ በኋላ ግጭት ቆሟል
ኃላፊው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ባሉት ከ48 እስከ 72 ሰዓታት ውስጥ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት ቆሟል ብለዋል።
ከስምምነቱ በኋላ ግጭት መቆሙ ሁለቱ ኃይሎች ለሰላም ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት የሚያሳይ ነው ያሉት ኃላፊው፤ የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋር እና አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመርዳት በሚደረገው ጥረት ግጭት መቆሙ ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።
የማይክ ሐመር የመቀለ ጉዞ
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በወታደራዊ አውሮፕላን የህወሓት ተወካዮችን ከመቀለ ይዘው ሲወጡ እና ይዘው ሲመለሱ እንደነበረ ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
ማይክ ሐመር ከህወሓት ተወካዮች ጋር አብረው ሲንቀሳቀሱ የነበረው በአፍሪካ ኅብረት ጥያቄ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።
ማይክ ሐመር የናይሮቢውን ንግግር መጠናቀቅ ተከትሎ የህወሓት ተደራዳሪዎችን ይዘው ወደ ትግራይ መቀለ ካቀኑ በኋላ፣ ከህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር መገናኘታቸውን እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ አምርተው ማክሰኞ ኅዳር 06/2015 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መገናኘታቸውን አክለዋል።
የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት
ሁለቱ ወገኖች በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ፤ ምንም እንኳን ጅማሮ ላይ ቢሆንም ነገሮች መንቀሳቀስ ጀምረዋል ብለዋል።
እርዳታ የጫኑ የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ተሽከርካሪዎች መቀለ ስለመድረሳቸው ሪፖርት ደርሶናል ያሉት ኃላፊው፤ ተጨማሪ 300 ሜትሪክ ቶን የእርዳታ ቁሳቁሶች የጫኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ወደ ማይ ጸብሪ እየተጓዙ ነው ብለዋል።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ትናንት ማክሰኞ ኅዳር 06/2015 ዓ.ም. በትዊተር ገጹ ላይ መድኃኒቶች፣ የአስቸኳይ ጊዜ እና የመጀመሪያ እርዳታ ድጋፍ የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች መቀለ መግባታቸውን አስታውቋል።
አሜሪካ የዲፕሎማሲ እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ማቅረቧን ትቀጥላለች ያሉት ከፍተኛ ባለሥልጣኑ፤ የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ በሌሎች ጉዳዮች ላይም ጥያቄ ከቀረበልን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
የመልሶ ግንባታ ወጪ
ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሱን የገለጹት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊ፤ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በአስቸኳይ መልሶ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኃላፊው፣ መልሶ ግንባታው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው ዓለም አቀፍ ድጋፍ የሚያሻው ጉዳይ ነው ብለዋል።