ትራምፕ በ2024ቱ ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ አስታወቁ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ዳግም ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ይፋ አደረጉ።

“አሜሪካን በድጋሚ ታላቅና ኃያል አገር ለማድረግ በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት እወዳደራለሁ” ብለዋል።

አክለውም “እንዲህ ፍቅር በተሞላበት ቦታ ላይ ሆኖ ማውራት በጣም ቀላል ነው” ሲሉ ንግግራቸውን ያዳምጥ የነበረውን ሕዝብ አሞካሽተዋል።

በንግግራቸው “ከዛሬ አንስቶ በ2024 ምርጫው እስከሚካሄድበት ቀን ድረስ ማንም ሰው አድርጎ በማያውቀው ሁኔታ እታገላለሁ። አገራችንን ከውስጥ ሆነው ለማፍረስ የሚሞክሩትን ጽንፈኛ ግራ ዘመም ዴሞክራቶችን እናሸንፋለን” ብለዋል።

ትራምፕ በማራላጎ ንግግር ሲያደርጉ የተሰበሰበው ሕዝብ ሲያጨበጭብ፣ ሲጮህ፣ ጥሩምባ በመንፋትም ድጋፉን ሲያሰማ ነበር።

ደጋፊዎቹ፣ ትራምፕ ተጨማሪ አራት ዓመታት እንዲመሩ "four more years!" (ተጨማሪ አራት ዓመታት) እያሉ መፈክር አሰምተዋል።

“አትፍረዱብኝ፣ የመረጥኩት ትራምፕን ነው” የሚል ጽሑፍ የሚያውለበልቡ መኪኖችም ታይተዋል።

ትራምፕ “በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት እየተወዳደርኩ ነው” የሚል ጽሑፍ አያይዘው ለደጋፊዎቻቸው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ኢሜል ልከዋል።

ሥልጣን ላይ ሳሉ ስኬታማ እንደሆኑም ትራምፕ ሳይናገሩ አላለፉም።

“በአራት አጭር ዓመታት ሁሉም ሰው ድንቅ ኑሮ ነበረው። ከመቼውም በላይ እየተመነደገ (ምጣኔ ሃብቱ) ነበር” ብለዋል።

የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት እያገገመ እንደነበረ ጠቅሰው፣ አሁን ግን “ዘቅጠናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ወቅታዊው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በፖላንድ በሚሳኤል ተመተው ስለሞቱ ሁለት ሰዎች ጉዳይ ከዓለም መሪዎች ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉ።

ባይደን የዩክሬንን ጦርነት የያዙበት መንገድ አሜሪካን የኒውክሌር ጦርነት ጫፍ ላይ ያደረሰ እንደሆነ ትራምፕ ተናግረዋል።

“ፖላንድ ላይ የወደቀው ሚሳኤል ምናልባትም በሩሲያ የተላከ ነው” ሲሉ ትራምፕ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ኢንዶኔዥያ የሚገኙት ባይደን፣ ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸውን በተመለከተ አስተያየት ካላቸው ሲጠየቁ “የለኝም፤ በፍጹም የለኝም” ብለዋል።

ከትራምፕ ጎን በመሥራት የምትታወቀው ልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ በበኩሏ፣ በ2024ቱ ውድድር እንደማትሳተፍ ገልጻለች።

“አባቴን በጣም እወደዋለሁ። አሁን ግን ቅድሚያ የምሰጠው ለታዳጊ ልጆቼ እና ለቤተሰባችን ነው” ብላለች ኢቫንካ።