ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በጋዜጠኛ ሺሪን ግድያ ምርመራ ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር አልተባበርም አለች
እስራኤል በጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አቅላ ግድያን ምርመራ በመተለከተ ከየትኛውም “የውጭ ኃይል” ጋር አልተባበርም አለች።
እስራኤል ይህን ያለችው አሜሪካ በጋዜጠኛዋ ግድያ ዙሪያ ምርመራ ጀምራለች መባሉን ተከትሎ ነው።
የእራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በጋዜጠኛዋ ግድያ ምርመራ መክፈታቸው ‘ስህተት’ ነው ብለዋል።
የፍልስጤም እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት የነበራት ጋዜጠኛ ሺሪን ባለፈው ዓመት ግንቦት 2014 ዓ.ም. በዌስት ባንክ የእስራኤል ጦር እያካሄደ የነበረውን ዘመቻ እየዘገበች ሳለ ጭንቅላቷን በጥይት ተመትታ መገደሏ ይታወሳል።
የዐይን እማኞች ሺሪን የተገደለችው ከእስራኤል ወታደር በተተኮሰባት ጥይት ነው ሲሉ፤ የእስራኤል ባለሥልጣናት ደግሞ ጋዜጠኛዋ ከጦር ኃይሉ አባል በተተኮስ ጥይት ተመትታ የመገደሏ እድል ሰፊ ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጽህፈት ቤት በበኩሉ ተዋቂዋ የአልጀዚራ ጋዜጠኛ የተገደለችው ከእስራኤል ጦር ኃይል አባል በተተኮሰ ጥይት እንደሆነ ከድምዳሜ ደርሻለሁ ብሎ ነበር።
አሜሪካም ብትሆነ ያካሄደችው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ጋዜጠኛዋ የተገደለችው ከእስራኤል ወታደር በተተኮሰ ጥይት የመሆኑ እድል ሰፊ መሆኑን አሳይቷል።
ትናንት ሰኞ ኅዳር 05/2015 ዓ.ም. አክሲዮስ የተሰኘው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ የፍትሕ ቢሮ በጋዜጠኛዋ ግድያ ዙሪያ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ምርመራ መጀመሩን ለእስራኤል ፍትሕ ቢሮ ገልጿል የሚል ዘገባን ይዞ ወጥቷል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ጋንትዝ ግን የአገሪቱ ጦር በጋዜጠኛዋ ግድያ “ሙያዊ እና ገለልተኛ ምርመራ” ማካሄዱን እና ውጤቱንም ለአሜሪካ ባለሥልጣናት ማጋራቱን ገልጸው፤ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት በእስራኤል ጦር ምርመራ እንደሚተማመኑ እና ከውጭ አካል ጋር ትብብር ለማድረግ ዝግጁ እንዳልሆኑ መናገራቸውን ገልጸዋል።
ከፍተኛ ቁጣን የቀስቀሰው የጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አቅላ ግድያ የተፈጸመው በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዌስት ባንክ ውስጥ ለዘገባ ተሰማርታ በነበረበት ወቅት ነው።
በአረቡ ዓለም ዝነኛ የሆነችው ጋዜጠኛዋ ለዘገባ በተሰማራችበት ወቅት የራስ ቅል መከላከያ (ሄልሜት) እና ‘ፕሬስ’ የሚል ጽሑፍ በግልጽ የሚያሳይ ሰማያዊ የሰውነት መከላከያ አጥልቃ ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት አንድ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ከፍተኛ መኮንን ጋዜጠኛዋ “በስህተት በእስራኤል ወታደር የመገደል እድሏ ሰፊ ነው” ካሉ በኋላ፤ ወደ ጋዜጠኛዋ የተኮሰው የጦር አባል ሺሪን “ጋዜጠኛ መሆኗን አለየም” ብለዋል።
ይህ የጦር መኮንን ጨምረው ሲናገሩ፤ ጋዜጠኛዋ ላይ የተኮሰው የጦር አባልን ማነጋገራቸውን ገልጸዋል። “ያደረገውን ነገር ነግሮናል፤ የተከሰተው በስህተት ነው” ብለዋል።
እስራኤል ጋዜጠኛዋ በተገደለችበት አካባቢ የእስራኤል ወታደሮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከባድ ተኩስ ተከፍቶባቸው ስለነበር ወታደሮቹ የነበሩበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት አግባብ ነው ትላለች።
እስራኤል ይህን ትበል እንጂ ጋዜጠኛ ሺሪን የተገደለችበትን ቅጽበት የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጋዜጠኛዋ በነበረችበት አካባቢ የተኩስ ልውውጥ እንዳልነበረ አሳይቷል።
ተንቀሳቃሽ ምስሎች የእስራኤል ወታደሮች 200 ሜትር ርቀት ላይ ሆነው ጋዜጠኛዋ እና ሌሎች ሰዎች ሲራመዱ ወደነበረበት አቅጣጫ ለደቂቃዎች ሲተኩሱ ያሳያል።
ጋዜጠኛ ሺሪን ትውልዷ እየሩሳሌም ቢሆንም ረዘም ያለ ጊዜን በአሜሪካ አሳልፋ ዜግነትም ተቀብላለች። በአልጀዚራ የአረብኛ ቋንቋ ክፍል ረዘም ላለ ጊዜ የእስራኤል-ፍልስጤም ግጭትን ስትዘግብ ቆይታለች።
“ጋዜጠኝነትን የመረጥኩት ለሕዝቡ ቅርብ ለመሆን ነው። እውነታውን መቀየር ቀላል ላይሆን ይችላል ነገር ግን ድምጻቸውን ለዓለም አቅርባለሁ” ብላ ነበር በአንድ ወቅት።