ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምላሽ ያላገኘው በኳታር ሲሠሩ የነበሩ የቀን ሠራተኞች ሞት
እሑድ ለእግር ኳስ ቤተሰቦች ተናፋቂ ቀን ናት።
ኳታር ቤቷን አሰማምራ የዓለም ዋንጫን ለማሰናዳት እንግዶቿን መቀበል ጀምራለች።
ለድግሱ ደግሞ ከደቡብ እስያ የመጡ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ተሳትፈዋል።
ኔፓል ለዓለም ዋንጫው ባትበቃም ሠራተኞችን በመላክ ተሳታፊ ሆናለች። ኔፓላዊያን ቤተሰቦች ዘመዶቻችንን ወደ ኳታር ለሥራ ብንልክም በደኅንነት ጉድለት ሞተውብናል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከስድስት ቀናት በፊት የኳታር አየር መንገድ በረራ ቁጥር ኪውአር 644 ኔፓል ካትማንዱ አውሮፕላን ማረፊያ እያስገመገመ ደረሰ።
ከአውሮፕላኑ ዕቃ መጫኛ ውስጥ ነጭ ትልቅ ሳጥን ብቅ አለ።
ስም- ኡሜሽ ኩማር ያዳቭ
ዕድሜ- 32
ጾታ- ወንድ
ዜግነት- ኔፓል የሚል ጽሑፍ የአስከሬን ሳጥኑ ላይ ሰፍሯል።
ጎልባዛር ከካትማንዱ 250 ኪሜ ትርቃለች።
የኡሜሽ አባት ቤታቸው ደጃፍ በሬያቸውን እያሰሩ ነው። ኔፓል ድሃ ከሚባሉ የዓለም ሃገራት አንዷ ናት።
አባት በድሃዋ አገር ብቻ ሳይሆን በድሃዋ አገር በድሆች መንደር ነው የሚኖሩት።
ልጅ ኡሜሽ ከዓለም ሃብታም አገራት አንዷ በሆነችው ኳታር የሥራ ዕድል አገኘ። ዕድሉን ለመጠቀም አባት 1500 ዶላር የሚያወጡ በሬዎችን ሸጡ።
ገንዘቡ ሥራውን ላመጣው አሰሪ እና ሠራተኛ አገናኝ ድርጅት የሚከፈል ነው።
እነዚህ ወኪሎች የኔፓልን የድሃ መንደሮች ያስሳሉ። በኔፓል ብቻ ግን አልታጠሩም። ወደ ባንግላዴሽ እና ሕንድም ያማትራሉ።
ጥሩ ደመወዝ ያለው ሥራ ያቀርባሉ። ለቪዛ የሚሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብም ይጠይቃሉ።
ሥራውን አገኘን ብለው የሚሄዱት ሁሌም አንድ ቦታ አይሠሩም። ከአንዱ ድርጅት ወደ ሌላው ይገላበጣሉ።
ቤተሰቦች ልጆቻቸው ለማን እንደሚሠሩ እና የት እንዳሉ እንኳን የማያውቁበት ጊዜ አለ።
በዳኑሻ አውራጃ የሁለት ሰዓት የመኪና ጉዞ ካደረጉ የክሪሽና ማንዳል ቤት ይደርሳሉ። አባቱ ሲቴሽ ከአራት ዓመት በፊት ለሥራ ወደ ኳታር አቀና።
ሲቴሽ አንዳንድ ጊዜ ሥራ ላይ ሆኖ ራሱን ፎቶ እያነሳ ለልጁ ይልካል። "የውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እንደሚሠራ ነገሮኛል። ብዙ ጊዜ ግን ስለሚሠራው በደንብ አልነገረንም" ይላል ክሪሽና።
ሲቴሽ ጥቅምት 12 ቤተሰቡን ለመጎብኘት መመለስ ነበረበት። ከዚህ ቀን ቀደም ብሎ ክሪሽና ስልክ ጥሪ ደረሰው። አባቱ በአደጋ መሞቱም ተነገረው።
ሲቴሽ ኳታር መዲና ዶሃ ይሠራ እንደነበር የቤተሰቡ ጓደኛ ይናገራል። ከሁለት ሜትር በላይ በሚጠልቅ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ውስጥ እየሠራ ነበር።
ዕድል ፊቷን ባዞረችበት ዕለት የአፈር ክምር ተደረመሰበት። የሞት የምስክር ወረቀቱም "በጠንካራ የቁስ አካል ተጽዕኖ ምክንያት ግልጽ ጉዳት ደርሶበታል" ይላል።
ክሪሽና ከአባቱ ቀጣሪ ድርጅት ካጃ ክፍያ ይቅርና አንድ የስልክ ጥሪ እንኳን አልደረሰውም።
ሲቴሽ ይሠራበት የነበረበትን ኩባንያ አስተያየት ለማግኘት ቢቢሲ በተደጋጋሚ ሞክሮ አልተሳካለትም።
ወደ ጎልባዛር እንመለስ። ላክስማን ልጁ በኳታር ስላለው ሕይወት ብዙም አያውቅም ነበር።
ተንቀሳቃሽ ስልክ የለውም። በዚህ ምክንያት ኡሜሽ በየዕለቱ ቲኪቶክ ላይ ይለጥፋቸው የነበሩትን ቪዲዮዎችን መከታተል አልቻለም።
አንዳንዴ በአብረቅራቂዎቹ የዶሃ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ፊት ሲደንስ ይታያል። ሌላ ጊዜ ደግሞ በዶርም መሰል መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ከሌሎች ስደተኛ ሠራተኞች ጋር ዳንሱን ያስነካዋል።
ኡሜሽ በግንባታ ቦታዎች እየሠራም ቪዲዮዎችን አጋርቷል። መሰላል ላይ ሆኖ ፈገግ ብሎ ይታያል። ወይም ቲክቶክ ወለድ የሆኑ ከባድ የኮንክሪት ጣሳዎችን እያነሳ ስፖርት ይሠራል።
ከወር በፊት ኡሜሽ ለእሑዱ የዓለም ዋንጫ ማስታወቂያዎችን ደረታቸው ላይ በለጠፉ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ፊት በምሽት ሲደንስ የሚያሳይ ቪዲዮ ለጠፈ።
ይህ የመጨረሻ ቪዲዮው ነበር።
በቀጣዩ ቀን ላክስማን በተመሳሳይ ዶሃ ከሚሠራ የአጎቱ የልጅ ስልክ ጥሪ ደረሰው። ሕይወቱ ማለፉም ተነገረው።
ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ወደ ግንባታ ስፍራው አቅንተው ነበር።
"ኡሜሽ ስካፎልዱን (በኮንስትራክሽን ስፍራ ዕቃዎችን ለማውጣት እና ለማውረድ የሚያገለግል የብረት ማማ) ወደ ላይ እየወሰደ ነበር። በመሃል ምን እንደነካው አይታወቅም ተሰብሮ መውደቁን ነግረውናል” ብሏል።
ላክስማን "በሥራ ቦታ ደኅንነታቸውን መጠበቅ ነበረባቸው። ሁሉንም ነገር መፈተሽ ነበረባቸው። ከፈተሹ በኋላ ብቻ ነው እንዲሠሩ መፍቀድ የነበረባቸው” ይላል።
ቢቢሲ ኡሜሽ ይሠራበት የነበረበትን የኮንስትራክሽን ኩባንያ ምላሽ ጠይቆ ነበር። ለሞት የተዳረገው በደኅንነት ችግር መሆኑን በፅኑ አስተባብሏል።
"አደጋው የደረሰው በቸልተኝነት እና በግዴለሽነት ነው። የሞተው ሠራተኛ በጣም ቸልተኛ ነበር። እንደ ሌሎች ባልደረቦቹ ሁሉ የደኅንነት ሁኔታዎችን እንዲያከብር ብዙ ጊዜ ተነግሮታል። ግን አልተሳካም" ሲል ኩባንያው ምላሽ ሰጠቷል።
ለዓለም ዋንጫ መስተንግዶ በሚል ግንባታ በኳታር ከተጀመረ ወዲህ የስደተኛ ሠራተኞች ሞት እና አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ መኖሩን የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።
የኳታር መንግሥት "በፕሮጀክቶቻችን ላይ የተቀጠሩትን ሠራተኞች ጤና፣ ደኅንነት እና ክብር ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ነኝ" ብሏል።
የጤና እና የደህንነት ደንቦችን ማሻሻሉንም ለቢቢሲ አስታውቋል።
የቢዝነስ እና የሰብአዊ መብት መርጃ ማዕከል ለቢቢሲ የሰጠው አዲስ አሐዝ እንደሚያሳየው ግን ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ወደ 140 የሚጠጉ የሠራተኞች መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።
ከእነዚህ ግማሽ ያህሉ ከጤና እና ከደኅንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው።
በቀልን ፍራቻ ዝም ያሉ ስለሚኖሩ እንጂ እውነተኛው አሐዝ ከዚህም ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ12 በላይ የሚሆኑ ከደቡብ እስያ የመጡ ሠራተኞች የሞት የምስክር ወረቀት ለቢቢሲ ደርሰዋል።
ብዙዎች የምስክር ወረቀቶች የሞት መንስኤን “በርካታ ግልጽ ጉዳት” በማለት ይጠቅሳሉ። ቤተሰቦች ግን አሁንም ምላሽ ይጠብቃሉ።
የኡሜሽ የሬሳ ሣጥን ከአየር ማረፊያ ወደ ጎልባዛር ጉዞ ጀምሯል። አባቱ ላክስማን እና የመንደሩ ነዋሪዎች ለሽኝቱ ተዘጋጅተዋል።
በባህላቸው አስከሬን ስለሚቃጠል ለእሳቱን የሚሆን እንጨት እና ሳር ሰብስበዋል።
በኔፓል ባህል ትልቁ ወንድ ልጅ ነው እሳቱን የሚያቀጣጥለው። ማብራት ወግ ነው።
ላክስማን አሁን ያለው ወንድ ልጅ ገና 13 ወሩ ነው። እንዲያቀጣጥልም በትንንሽ መዳፎቹ ላይ እሳት የያዘ እንጨት በአባቱ ድጋፍ ይዟል።
የኡሜሽ እናት ሱሚትራ ፊቷ በእንባ እየራሰ "ይደግፈን ነበር። እኛ የምንከፍለው ብድር እና ለልጆቻችንም ገንዘብ ያስፈልግናል። የኔ ጀግና ነበር" ስትል ተናግራለች።