ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጦርነትና በጭንቀት ውስጥ ሆና የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ጉዳፍ
በዓለም አትሌቲክስ ዘርፍ ከተሳካላቸው አትሌቶችን አንዷ ናት ጉዳፍ ጸጋይ።
በተለይም በባለፈውና በዘንድሮው ስኬታማ የተባሉት ዓመታት አሳልፋለች።
የዓለም ሻምፒዮና ሆናለች፣ በ5000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች።
ይህንን ሁሉ ማሳካት የቻለችው በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሆና ነው።
ጉዳፍ ጸጋይ ትውልዷ ትግራይ ነው።
በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተውና ለሁለት ዓመት በዘለቀው የደም አፋሳሽ ጦርነት ወላጆቿም ሆነ እህቶቿ ስላሉበት ሁኔታ አታውቅም ነበር።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን የቀጠፈው እና በሚሊዮኖች ህይወት ላይ ከባድ ሰቆቃን ያደረሰው ይህ ጦርነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከተከሰቱት አንደኛው ደም አፋሳሽ በሚልም ተፈርጇል።
ጦርነቱን ተከትሎ ትራንስፖርት እንዲሁም ማንኛውም የመገናኛ ዘዴዎች፣ ስልክ እና ኢንተርኔት አንዲቋረጥ ተደረገ።
“በየእለቱ ለበለጠ ስኬት እንድተጋ ሲመክሩኝ ከነበሩ አባት እና ወንድሞች ጋር መነጋገር አለመቻል በጣም ከባድ ነው። ለማስረዳት እንኳን ከባድ ነው” በማለት ጉዳፍ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግራለች። “ቤተሰቦቼን ለ18 ወራት አላነጋገርኳቸውም” ብላለች።
የ25 ዓመቷ ጉዳፍ በዚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ ሆና በአስር ዓመት የአትሌትነት ጉዞዋ ስኬታማ የተባለ ዓመትን ያሳለፈችው።
ለስኬት የሚደረግ ትግል
ጦርነት፣ ጭንቀትና ከቤተሰብ ጋር መለያየት እንዳለ ሆኖ ጉዳፍ በአዲስ አበባ ከባለቤቷ እንዲሁም አሰልጣኟ ከሆነው ሕሉፍ ይሕደጎ ጋር ልምምዷን ቀጠለች። ለጉዳፍ ባለቤቷ በዚህ ፈታኝ ወቅትም የጥንካሬዋ መሰረትም ነበር።
“በቤት ውስጥ ባለቤቴ ነው፤ በሜዳ ላይ ደግሞ አሰልጣኜ ነው። በከፋኝ ወቅት ከጎኔ እያጽናናኝ ነበር። በብዙ ረድቶኛል” ትላለች ጉዳፍ።
ይህ ጥረታቸውም ባለፈው ዓመት በተደረጉት ታላላቅ ውድድሮች ፍሬ ማፍራቱን አሳይቷል። በኦሪጎን ከነበረው ውድድር በተጨማሪ በ1500 ሜትር በቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊ ሆናለች።
“በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙኝም ጠንክሬ ስለሰራሁ ተሳካልኝ። ስኬቶቼንም ከባለቤቴ እና ከጓደኞቼ ጋር ተጋራሁ፤ አብረን ተደሰትን”
“አትሌቶች ራሳቸውን ስኬት ላይ ደርሰናል የሚሉት የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮናዎችን ሲያሸንፉ ነው። ይህም ህልሜ ነበር አሳክቼዋለሁ” ብላለች።
በዩጂን የነበረውን ውድድር በአንደኛነት ስታጠናቅቅም የትግራይ ክልልን ባንዲራ የያዘ አንድ ግለሰብ ወደ ሜዳ እየሮጠ ገብቶ ደስታውን አትሌቷን በማቀፍ ገልጿል።
ሄይዋርድ ስታዲየም ላይ በነበረው ውድድር ስለ ጦርነቱ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ድጋፍ ለመስጠት ተሰባስበው ከነበሩ የትግራይ ተወላጆች አንዱ ነበር።
የጦርነቱ ዳፋ ለጉዳፍ ደርሷታል።
የምሽቱ ሽብር
ወቅቱ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ነበር። በአንድ ሌሊት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደቤታቸው መጥተው አንኳኩ።
ከእንቅልፋቸውም ነቁ። የጸጥታ ኃይሎች ሕሉፍን ይዘውት ሔዱ።
ይህ ሁኔታ አንድ ዓመት ቢያልፈውም ያችን የሽብር ሌሊት ትናንት የተከሰተ ያህል ነው የምታስታውሰው።
“በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶኛል። አትሌት እንደመሆኔ በኔ ላይ ይፈጠራል ብዬ አላስብም ነበር። እኛ ስፖርት ብቻ እንጂ ፖለቲካ አናውቅም” ትላለች።
“ሌሊቱን ሙሉ አለቀስኩ። በሩ በተንኳኳ ቁጥር እኔንም ሊወስዱኝ ይመለሳሉ እያልኩ ስጨነቅና ስሸበር ነበር” በማለት ያለፈችበትን ሁኔታ ታስረዳለች።
ከዚያም በኋላ በውድደሩ ላይ ማተኮር ባለመቻሏም ባለፈው ዓመት በፈረንሳይ ሊደረግ የነበረ ውድድርም ሰረዘች። ይህ ውድድር ክብረ ወሰን ለመስበር የምትሮጥበት ነበር።
“የዓለም ክብረ ወሰንን ለመስበር እየተዘጋጀሁ ነበር። በጥሩ ደህንነት ላይ ነበርኩ” ስትል ጉዳፍ ታስረዳለች።
ሕሉፍ ከአንድ ቀን እስር በኋላ ቢፈታም ነገር ግን ወታደሮች ‘ጁንታ’ ነህ እያሉ እንዳስፈራሩትም ተናግሯል።
“በእኩለ ሌሊት ላይ ነው 20 የሚሆኑ ወታደሮች ወደ ቤት የመጡት። ህወሃትን ትደግፋለህ፣ አትሌቶችን ወደ ውጭ ትልካለህ እንዲሁም ዶላር ቤት ውስጥ እያከማቸህ ነው ብለው ከሰሱኝ” ሲልም ህሉፍ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግሯል።
“ቤቴን ፈተሹት። ስለ ጉዳዩ አሁን መናገር ቀላል ቢመስልም ፈታኝ ነበር” ይላል።
ጥንዶቹ ይህ ሁሉ መከራ በማለፉም ደስተኞች ናቸው።
የሰላም ስምምነት ቢፈረምም ቤተሰብ ጋር አለመገናኘት
በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት በፌደራሉ መንግሥትና በህወሃት መካከል ተፈርሟል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ስልክ በመመለሱ ጉዳፍ ስለ ውድድሩ አሸናፊቷ ለቤተሰቦቿ ተናገረች። ደስታቸውንም ተካፈሉ።
“"ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ቤተሰቦቼ ደውለው ደስታቸውን ገለፁ"ትላለች ጉዳፍ
“ወላጆቼ ውድድሩን አይተውት ቢሆን ኖሮና ከኔ ጋርም አብረውኝ ቢሆን ኖሮ እያልኩ ነበር። ቤተሰቦቼ ውድድሩን እንዳዩት ነገሩኝ እና አለቀሱ”
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለትግራይ ተወላጅ አትሌቶች ወደ መቀለ ሄደው ቤተሰቦቻቸውን እንዲጎበኙ በማመቻቸቱ ወደ ትግራይ አምርተው ነበር።
ጉዳፍ በዚህ ጉዞዋ ጓደኞቿን ብታገኝም በሚያሳዝን ሁኔታ ቤተሰቦቿን ማግኘት አልቻለችም።
“ከቤተሰቦቼ ጋር እንደማልገናኝ አውቅ ነበር ምክንያቱም ይህ ድንገተኛ ጉዞ ነበር" ስትል ታስረዳለች።
"ቤተሰቦቼ የሚኖሩት ገጠር ውስጥ ነው። እናም ቀድሜም እንደምመጣ ልነግራቸው አልቻልኩም። ሆኖም አካቢውን መጎብኘትና የጓደኞቼን ዓይን ማየት በጣም ጥሩ ነበር።" ብላለች
የኦሎምፒክ ህልም
ጉዳፍ ቤተሰቦቿን በቅርብ ጊዜ በአካል እንደምትገናኛቸው ተስፋ አድርጋለች። በአሁኑ ወቅት በግንቦት ዶሃ ለሚደረገው የዳይመንግ ሊግ ውድድር እየተዘጋጀች ትገኛለች።
ዓመቱን በደማቅ ሁኔታ የጀመረችው ጉዳፍ በቤት ውስጥ ውድድሮች የበለጠ ስኬት አይታለች። በሶስት ሺሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበች ሲሆን የዓለም ክብረ ወሰንንም ለማሸሻል የዘገየችው በ9 ሰኮንዶች ብቻ ነው።
ሆኖም በያዝነው ዓመት ዋና አላማዋ በነሐሴ በቡዳፔስት በሚደረገው ውድድር የዓለም ሻምፒዮንነቷን ማስጠበቅ ነው። እንዲሁም በሚቀጥለው ዓመት በፓሪስ በሚደረገው የኦሎምፒክስ ውድድርም እየተዘጋጀች ትገኛለች።
"በድጋሚ የአለም ሻምፒዮናን ማሸነፍ እፈልጋለሁ" ብላለች።
“የቤት ውስጥ ውድድር ሻምፒዮን ነኝ፣ የዓለም ሻምፒዮን ነኝ። ነገር ግን ወደ ኦሎምፒክስ ውድድር ስንመጣ በጃፓን፣ ቶክዮ የ5ሺህ ሜትር የነሐስ ተሸላሚ እንጂ ሻምፒዮን አይደለሁም”
“ህልሜ የኦሎምፒክስ ሻምፒዮን መሆን ነው። ግቤን ማሳካት እንደምችል አምናለሁ።" ብላለች