ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎት የነበራት አትሌት ጎተይቶም

ከሁሉም ተጫዋች ነች፤ ሳቅ አይለያትም። ስትናደድ እንኳን ትስቃለች።

በውስጧ እያቃሰተችም ቢሆን ከፈገግታዋ መረጋጋት ይታያል።

በዚህ ላይ፣ ጥሩ ሙዚቃ እና ዳንስ ትጨምርበትና የቁጣ ስሜቶቿን ወዲያ ታሽቀነጥራቸዋለች፤ ትረሳቸዋለች።

ሁሉም ነገር ጠንክሮ በመስራት እና ስኬታማ በመሆን ማሸነፍ እንደሚቻል ስለምታምን ለተመሰቃቀሉ ስሜቶች እጅ አትሰጥም።

ግን አንድ ነገር ብቻ ያሸንፋታል፤ ናፍቆት በፍፁም አትችልም።

ስለሆነም ከተከዘች አልያም ካነባች ቤተሰቦቿን ናፍቃለች ማለት ነው፤ በተለይ ደግሞ ወላጅ እናቷን አደይ ብርሂት ካሱን።

በእያንዳንዱ ወሬዋ አንስታ የማትጠግባቸው እናቷን ብርሂት ከምድረ ገጽ እንዲጠፋላቸው የሚፈልጉት አንድ ነገር አለ፤ ያለ እድሜ ጋብቻ። በዚያ ምክንያት አብዝታ ትወዳቸዋለች።

በእናት እና ልጅ መካከል ስላለው ግንኙነት ወደ ኋላ ላይ እንመለስበታለን።

እንደ ማንኛውም ሰው ከቤተሰቦቿ መለየትን አትፈልግም። ሰው ወዳድ ስለሆነች ለጓደኝነት ልዩ ቦታ ትሰጣለች። ከጓደኞቿ ጋርም መልካም ግንኙነት አላት።

“ጓደኛ ሌላኛው እኔ ማለት ነው ብዬ ነው የማስበው” በማለት ትገልጸዋለች።

የ27 ዓመቷ አትሌት ጎተይቶም ገብረሥላሴ፣ በአሁኑ ወቅት በአትሌቲክስ ዓለም ውስጥ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሴት አትሌቶች መካከል አንዷ ናት።

በቅርቡ በአሜሪካዋ ግዛት ኦሪገን ውስጥ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን ውድድር ተሳትፋ ባስመዘገበችው ድል አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዝግባለች።

አትሌት ጎተይቶም ትግራይ እንደርታ ወረዳ ማይ ቀያሕ የምትባል ትንሽ መንደር ውስጥ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ነው የተገኘችው።

ሩጫን ትምህርት ቤት ውስጥ ነው የጀመረችው። በልጅነቷ የነበራት ምኞትና አሁን የሆነችው ግን ፈጽሞ እንደማይገናኝ ትናገራለች።

“ምኞቴ ጋዜጠኛ መሆን ነበር። ትምህርት ቤት ውስጥ የተማርኩትን ቤት መጥቼ አነብላቸዋለሁ፤ ልክ እንደ ጋዜጠኛ . . . ወረቀት ጠቅልዬ እጄ ላይ እይዝ ስለነበር እናቴ ምኞትሽ እሱ ነው ትለኝ ነበር። ልጄ ጋዜጠኛ ትሆንልኛለች ትል ነበር” ትላለች።

የወ/ሮ ብርሂት ቤተሰብ ግን ልጃቸው ጋዜጠኛ ትሆንልናለች የሚል ምኞት ቢኖራቸውም፣ እየነገሩ ያሳደጓት ግን ጎረቤት ስለነበረች ‘ስኬታማ’ ስፖርተኛ፣ አዳነች ጴጥሮስ፣ ታሪክ ነው።

በዚህም የተነሳ ጎተይቶም ወደ ስፖርት አዘነበለች።

ወደ ስፖርት እንድገባ ያበረታቱኝ እነሱ ናቸው ትላለች። የአዳነች ጴጥሮስ ታሪክ ደግሞ ይበልጥ ተጽእኖ ያሳደረባት።

“ገጠር ውስጥ ሴት ልጅ ቁምጣ ለብሳ ለስፖርት መሮጥ እንደ ነውር ይቆጠር ነበር፤ እኛ ቤት ውስጥ ግን ወላጆቼ ስፖርት ሙያ ነው ብለው ያምኑ ነበር [በተለይ አደይ]” ትላለች።

ከትምህርቷ ጎን ለጎን ሩጫን አጥብቃ በመያዝ ስፖርቱ ላይ ውጤታማነትን ማሳየት ጀመረች።

በወረዳው በትምህርት ቤቶች መካከል በሚደረጉ ውድድሮች አልፋ፣ በክልል ደረጃ በተደራጁ ክለቦች ለመታቀፍ ጊዜ አልወሰደባትም።

“እነዚያ የትምህርት ቤት ውድድሮች እንደ ትልቅ ሻምፒዮና አስባቸው ነበር” ስትል ታስታውሳለች።

በዚህ መልኩ እኤአ በ2000 በመስፍን ኢንዳስትሪያል ኢንጅነሪንግ ቡድን ውስጥ ለመታቀፍ በቃች።

በዚያን ወቅት መቀለ ውስጥ የማጣሪያ ውድድሮች ተደርገው በ5 ሺህ ሜትር አንደኛ፣ በ10 ሺህ ሜትር ደግሞ ሦስተኛ በመውጣት ከቡድኑ ጋር ተቀላቀለች።

“በተሰማራንበት ቦታ ሁሉ አሸናፊ መሆን አለብን ብለው ከሚያምኑ ሰዎች መካከል ስለነበርኩ ስፖርት እንደጀመርኩ ብዙም ሳልቆይ ወዲያው መስፍን ኢንጂነሪንግ ውስጥ ገባሁ።”

በ2011 ፈረንሳይ ውስጥ በተካሄደ የወጣቶች ዓለም አቀፍ ሻምፒዮና አገሯን ወክላ ተሳተፈች።

ውድድሩ የተካሄደው እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች በሆኑ አትሌቶች መካከል ሲሆን፣ ጎተይቶም በሦስት ሺህ ሜትር ተሳትፋ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳልያ አገኘች።

“ይህ ትልቅ መንገድ የከፈተልኝ ውድድር ነበር። አንዴ ሳሸንፍ ደግሞ ሞራል ስለሆነኝ ከዚያ በኋላ ጠንክሬ መስራት አለብኝ አልኩ።”

የአትሌት ጎተይቶም ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች

  • በ2015 በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በ5 ሺህ ሜትር አራተኛ ደረጃ
  • በ2013 በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ የአገር አቋራጭ በታዳጊ ሴቶች ፖላንድ ውስጥ ተሳተፈች
  • በ2012 ቤኒን በተዘጋጀው የአፍሪካ ሻምፒዮና 5 ሺህ ሜትር በመሳተፍ የነሐስ ሜዳልያ አሸነፈች
  • በ2011 ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተወዳድራ በ3 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ተሸለመች። [የዘመን አቆጣጠሮቹ በአውሮፓውያን ናቸው]

‘የእኔ ጀግና እናቴ ናት’

አሁን ደግሞ ከአትሌት ጎተይቶም አንደበት ወደ ማይጠፉት አደይ ብርሂት እንመለስ።

ጎተይቶም ‘የሴቶች ተምሳሌት’ የምትላቸው በተለይ አንዲት እንስት ላይ የሚደርሱ ባህላዊና ማኅበራዊ ጫናዎችን እየታገሉ እዚህ ደረጃ ላይ እንድትደርስ እናቷ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ትናገራለች።

“ገጠር ውስጥ ባለው አስተሳሰብ ሳቢያ ተገድዳ ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ትዳር ገባች። ይሄ ያማታል። ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሱ የነበሩ በርካታ ሴቶች በቤተሰብ ጫና ተገድደው ወደ ኋላ ሲቀሩ ስለምታይ ባህሉን እና አኗኗሩን ትታገለው ነበር” ትላለች።

እናቷ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል። ትምህርት ላይ ጎበዝ የነበሩ ቢሆንም ዕድሜያቸው 13 ሲሞላ በማግባታቸው ከሚወዱት ትምህርታቸው እንደተሰናከሉ ጎተይቶም ትገልጻለች።

በዚህ ዘወትር ይቆጩ የነበሩት እናት ያለ ዕድሜ ጋብቻ ታላቅ ልጃቸው ላይም በመድረሱ ይቆጩ ነበር። ቀጥሎም ‘ሴት ልጅ ገጠር ውስጥ አግብታ ኑሮ መመስረት አለባት’ የሚል አስተሳሰብ ልጃቸው ጎተይቶምንም ይከተላት ጀመር።

አሁንስ ለሁለተኛ ጊዜ አልሳሳትም ብለው ባለቤታቸውንና ሌሎች ይህንን ሃሳብ ይደግፉ የነበሩትን አጥብቀው መቃወምና ልጆቻቸውን ለዚህ ነገር ያጋለጡ ቤተሰቦችን መውቀስ ጀመሩ።

“አደዋይ፣[እናቴ] የ13 ዓመት ልጅ እያለች እንዳገባች ትነግረን ነበር። ሕመሙ ስለሚገባትና ያለፍላጎት ሲሆን የሚፈጥረውን ጫና ስለምታውቀው ከውስጥና ከውጭ የሚመጣ ጫና አያንበረክካትም። ጎልተን እንድንወጣ ራሳችንን እንድንችል የምትጥር ጀግና እናት ናት” ትላለች።

አትሌት ጎተይቶም በ5 እና በ10 ሺ ሜትር ውድድሮች

  • በሰኔ 29/2016 ሆላንድ ሄንግሎ ውስጥ በተካሄደ የ10 ሺህ ሜትር ውድድር 10ኛ ደረጃን ይዛለች።
  • የካቲት 4/2015 ኒውዮርክ በተካሄደ የሚልሮስ ጨዋታዎች ተብሎ በሚታወቀው ዓመታዊ የቤት ውስጥ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር ተሳትፋ የነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች።
  • በ2014 በአሜሪካ ቦስተን በተካሄደ የቤት ውስጥ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር የብር ሜዳልያ አግኝታለች።
  • በ2017 በአሜሪካ በተካሄደ ሌላ የ10 ሺህ ሜትር የግል ውድድር ሦስተኛ ወጥታለች።
  • በ2015 ደግሞ ቤልጅየም ባስተናገደችው ‘ናይት ኦፍ አትሌቲክስ’ ዓመታዊ ውድድር በ5 ሺህ ሜትር ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች። [የዘመን አቆጣጠሮቹ በአውሮፓውያን ናቸው]

* ምንጭ፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ድረ ገጽ

አትሌቲክስ ምን ይፈልጋል?

አትሌት ጎተይቶም ገብረሥላሴ አሁን በሴቶች ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ናት።

በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ በቀጥታ ተሳታፊ ትሆናለች።

አትሌቷን በግልም በቡድንም ያሰለጠኗት ሦስት አሰልጣኞች አሉ።

ሩጫ ጥረትን ይጠይቃል የምትለው አትሌት ጎተይቶም ከባድና ጥንቃቄ የሚሻ ሥራ እንደሆነም ትናገራለች።

“እግር ብቻ ሳይሆን አእምሮም አብሮ ይሮጣል፤ ሁለቱም ካልተናበቡ ውጤታማ አይኮንም። እንደ ዓላማ ከተያዘ ደግሞ በአጭሩ ህይወትን የሚቀይር ነው” ትላለች።

እዚያ ለመድረስ ግን ፈተና አለ፤ አልፎ አልፎ ደግሞ እንኳንም ሯጭ ሆንኩኝ ያስብላል። አንዳንዴ ዓመቱን ሙሉ ተሰርቶ ውጤት ሳይመጣ ሲቀር ተስፋ ያስቆርጣል።

ጎተይቶም ሰው በፈተና ውስጥ ማለፍ አለበት የሚል እምነት አላት። “ተስፋ አስቆራጭ ነገር ሲገኝ የምናማርር፣ ጥሩ ውጤት ሲገኝ ደግሞ የምንዘናጋ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ሩጫ በጣም ጥንቃቄን የሚሻ ሥራ ነው” ትላለች።

ኦሪገን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር አትሌቷ ጎልታ የወጣችበት ሲሆን በዚህ ውድድር የተለየ ውጤት ለማምጣት አልማ እንደተነሳች ትናገራለች።

ትግራይ ውስጥ ባለው ሁኔታ የተነሳ ከቤተሰቦቿ ጋር ልትገናኝ ባለመቻሏ፣ ያሉበትን ሁኔታ ባለማወቋ ጫና ቢፈጥርባትም “ይሄ ዓመት የእኔ ዓመት ነው ብዬ አስብ ስለነበር ጥሩ ውጤት ለማምጣት እሰራ ነበር” ትላለች።

“ማንኛውንም ነገር በሥራችን ነው የምናሸንፈው፤ ነገ መገናኘታችን አይቀርም። እኔ የተሻለ ህይወት ይዤ ከቆየሁ ነው ቤተሰቤን ማዳን የምችለው። አእምሮዬ ተጎድቶ ሌላ ጉዳት እንዲሆንባቸው አልፈልግም። ስለዚህ ሁኔታው አእምሮዬ ውስጥ ምንም ዕንቅፋት እንዳይፈጥርብኝ ብዬ ትኩረቴን ሥራዬ ላይ አድርጌ ነበር።”

ጎተይቶም በማራቶን ያስመዘገበቻቸው ድሎች

  • ሐምሌ 18/2022 - የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና - ኦሪገን - አንደኛ - የገባችበት ሰዓት- 2፡18፡11
  • መጋቢት 6/2022 - ቶኪዮ ማራቶን - ሦስተኛ - የገባችበት ሰዓት 2፡18፡18
  • መስከረም 26/2021 - በርሊን ማራቶን - አንደኛ - የገባችበት ሰዓት 2፡20፡09
  • ታኅሣሥ 12/2021 - ግማሽ ማራቶን - ማናማ ባሕሬን - አንደኛ - የገባችበት ሰዓት 1፡05፡36
  • ግንቦት 08/2022 - ግማሽ ማራቶን - ፖርቹጋል - ሦስተኛ - የገባችበት ሰዓት 1፡07፡11 [የዘመን አቆጣጠሮቹ በአውሮፓውያን ናቸው ]