የአሜሪካዋ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ባለቤት ቤታቸው ውስጥ ጥቃት ተፈጸመባቸው

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ባለቤታቸው በመዶሻ ጥቃት ከተፈጸመባቸው በኋላ ሐዘን እንደተሰማቸው እና ድንጋጤ ውስጥ እንደገቡ ገለጹ።

ፔሎሲ ጥቃቱ ካጋጠመ በኋላ ሕግ አስከባሪ አካላት በወሰዱት ፈጣን እርምጃ እና ለባለቤታቸው እየተደረገ ባለው የሕክምና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ባለፈው አርብ ጥቅምት 18/2015 ዓ.ም. አንድ ጥቃት አድራሽ ግለሰብ ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ ወደሚገኘው የአፈ ጉባኤዋ እና ባለቤታቸው መኖሪያ ቤት ዘልቆ በመግባት ፖል ፔሎሲን በመዶሻ መትቷል።

የ82 ዓመቱ ፖል ከደረሰባቸው ጉዳት እያገገሙ መሆኑን ናንሲ ፔሎሲ ገልጸዋል።

ፖል ፔሎሲ በደረሰባቸው ጉዳት በራስ ቅላቸው እና ቀኝ እጃቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ በሆስፒታል “ሕይወት አድን” ሕክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።

ጥቃቱን በማድረስ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው የ42 ዓመቱ ዴቪድ ዴፓፕ ወደ ጥንዶቹ መኖሪያ ቤት ዘልቆ ከገባ በኋላ ናንሲ ፔሎሲን የት እንዳሉ መጠየቁ ተዘግቧል።

ጥቃት ሲፈጸም በመኖሪያ ቤታቸው ያልነበሩተ ናንሲ፤ ባለቤታቸው ላይ ጉዳት መድረሱ ከተሰማ በኋላ ወደ ሆስፒታል አቅንተዋል።

ፖሊስ እንዳለው ጥቆማ ደርሶት በመኖሪያ ቤቱ ሲደርስ ተጠርጣሪው እና ፖል ፔሎሲ መዶሻውን ለመያዝ ትግል ላይ ነበሩ።

ፖሊስ ጥቃት አድራሹን በመጣል በቁጥጥር ሥር አውሎታል። ግለሰቡ ናንሲ ፔሎሲ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እስኪመለሱ ድረስ ፖል ፔሎሲን አስሮ ለማቆየት ሞክሮ እንደነበረም ምንጮች ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው፤ “ናንሲ የት ነች?” እያለ ሲጮህ ነበር ተብሏል።

በቁጥጥር ሥር የዋለው የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ጥቃት በማድረስ፣ መኖሪያ ቤት ሰብሮን ጨምሮ በርካታ ክሶች ይጠብቁታል።

የ82 ዓመቷ ናንሲ ፔሎሲ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል አንዷ ናቸው። ፔሎሲ ከምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በመቀጠል ለአሜሪካ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ናንሲ ፔሎሲ ለአራት ተከታታይ የሥራ ዘመን የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ተመርጠው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።