ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፍሪካ ቀንድ ሚናዋ እየጎላ የመጣው የቱርክ የሽምግልና ጥረት እና የገጠሟት እንቅፋቶች
ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ቱርክ ባለፉት ዓመታት በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ በተለያዩ መስኮች ቀላል የማይባል ተሰሚነት አላት።
በዓለም ዙሪያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በወታደራዊ መስኮች ያላት ተጽእኖ እየሰፋ የመጣው ቱርክ ግጭቶችን ለማስቆም እና ሰላም እንዲወርድ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ አስተዋጽኦዋ እየጎላ በመምጣት ላይ ነው።
በፕሬዝዳንቱ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚመራው ይህ የቱርክ ተሳትፎ በዋና ዋና አሳሳቢ ዓለም አቀፋዊ ግጭቶች እና ጉዳዮች ላይ ይስተዋላል።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየተጠናከረ የመጣው ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ የምዕራባውያንን እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ትኩረትን በሳበበት በአሁኑ ወቅት የቱርክ ፕሬዝዳንት በአካባቢው ባለው ሁኔታ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ወደሆኑት ሁለት አገራት በዚህ ሳምንት ጉብኝት ያደርጋሉ።
በዚህም መሠረት ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ሰኞ የካቲት 9/2018 ዓ.ም. ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንዲሁም ማክሰኞ ወደ ኢትዮጵያ በማምራት ከአገራቱ መሪዎች ጋር ውይይት እንደሚደያርጉ ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የቅርብ ወዳጅ በሆኑት ሁለት አገራት በሚያደርጉት ጉብኝት በጋራ ጉዳዮች፣ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከመነጋገር ባሻገር የተለያዩ የስምምነት ሰነዶች እንደሚፈረሙ ተገልጿል።
ምንም እንኳን ባይጠቀስም ሦስቱንም አገራት በሚመለከታቸው የአፍሪካ ቀንድ ዋነኛ ጉዳይ በሆነው በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እንዲሁም ሶማሊያን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ንግግር እንደሚኖር ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንቱ በጉዟቸው ዕቅዳቸውን ምን ያህል እንደሚያሳኩ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም አስካሁን ቱርክ የተሳተፈችባቸው የሰላም ጥረቶች ምን ውጤት አስገኙ? ምንስ ተግዳሮት ገጠማት?
በተለያዩ ቀጣናዎች የሚገኙ ባላንጣ አገራትን ወደ አንድ ለማምጣት የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ የከረመችው ቱርክ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የአሸማጋይነት ሚና ለማሳደግ የምታደርገውን ሙከራ ጨምራለች።
አንካራ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን፣ ዩክሬን እና ሩሲያን፣ ታሊባን እና ፓኪስታንን በማሸማገል ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። በሌሎች ቀጣናዎችም ባላንጣዎችን ለማስታረቅ ጥያቄ ስታቀርብ ከርማለች።
የቱርክ ባላንጣዎችን የማሸማገል ጥረት አንካራ ገንቢ ሚና ያላት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ መረጋጋት አዎንታዊ አስተዋጽኦ የምታደርግ አገር ሆና እንድታትይ እንደሚያደርግ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እና የመንግሥት ደጋፊ ተንታኞች ይናገራሉ። ይህ አካሄድ ቱርክን በዓለም መድረክ ላይ ያላትን ክብር እንደሚያሳድግም ያስረዳሉ።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ባለፈው ኅዳር ላይ 'ኒውስዊክ' በተሰኘው የአሜሪካ ሳምንታዊ መጽሔት ላይ በወጣ ጽሁፋቸው አገራቸው ግጭቶች እንዲፈቱ ለማድረግ ወደ ኋላ አለማለቷን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ "ከካውካሰስ እስከ አፍሪካ እንዲሁም ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ባልካን በተዘረጋው ሰፊ ቀጣና ውስጥ ቱርክ ግጭቶች ፍትሃዊ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲገኝላቸው ከማድረግ እንዲሁም ዘላቂ እና ፍትሃዊ ሰላም እንዲመጣ ያለባትን ኃላፊነት ከመወጣት አልተቆጠበችም" ሲሉ ጽፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቱርክ "በዓለም አቀፍ የሰላም ሽምግልና መስክ መሪነቱን" የመያዝ ዓላማ እንዳላት ይገጻሉ። የፕሬዝዳንቱ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ደግሞ፤ ቱርክ "ዓለም አቀፍ ቀውሶችን ለመፍታት ቁልፍ አገር" እንደሆነች ይናገራሉ።
ምንም እንኳ ይህ ትጋት ተደጋግሞ ቢገጽም፤ በቅርብ ጊዜ ወዲህ አንካራ የአደራዳሪነት ሚናዋን ለመወጣት የምታደርገው ጥረት እንቅፋቶች በዝተውበታል።
የሩሲያ እና ዩክሬንን ጦርነት ለመቋጨት ጠንካራ ፍላጎት ያላቸው ኤርዶዋን "የመሪዎች ጉባኤ" ለማስተናገድ ፍላጎታቸውን ቢገልጹም፤ በቅርብ ጊዜያት በሞስኮ እና ኪየቭ መካከል የተደረጉት ንግግሮች የተስተናገዱት አቡ ዳቢ ውስጥ ነው።
በተመሳሳይ ቱርክ በተያዘው የካቲት ወር የተካሄደውን የአሜሪካ እና የኢራን ወሳኝ ድርድር ለማስተናገድ ተስፋ አድርጋ ነበር። በመጨረሻም ግን ውይይቱ ኦማን ውስጥ ተካሂዷል፤ ይህም የመንግሥት ደጋፊ በሆኑ የቱርክ ተንታኞች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
ቱርክ የትኞቹን አገራት አሸማግላለች?
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቱርክ አጎራባች በሆኑ አካባቢዎች እና በሰፊው ቀጣና ውስጥ ያሉ ባላንጣዎችን አሸማግላለች።
ለሶማሊላንድ ዕውቅና ያሰጣል የተባለው የአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ ስምምነት መፈረምን ተከትሎ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ውጥረት መፍትሔ ያገኘው በቱርክ አሸማጋይነት ነበር።
ቱርክ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ባለሥልጣናት መካከል የተካሄዱ "ቀጥተኛ ያልሆኑ ስብሰባዎችን" አስተናግዳለች። በመጨረሻም በታኅሣሥ 2017 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ወደ ቱርክ ተጉዘው ስምምነት ተፈራርመዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን መሃል ላይ ተቀምጠው በተፈጸመው ስምምነት ላይ ሁለቱም አገራት አንዳቸው ለሌላኛቸው ሉዐላዊነት እና ነጻነት ዕውቅና ሰጥተዋል።
ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 ዩክሬን ላይ ሙሉ በሙሉ ወረራ ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ፣ ቱርክ ዩክሬን እና ሩሲያን ለማስታረቅ የተዘጋጁ በርካታ ዙር ድርድሮችን ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ አስተናግዳለች። የመጨረሻው ንግግር የተካሄደው በሰኔ 2025 ነበር።
በቱርክ ከተካሄዱት ንግግሮች ውስጥ የተወሰኑት ተጨባጭ ውጤቶችን አስገኝተዋል። ሁለቱ አገራት በርካታ የጦር እስረኞችን እንዲለዋወጡ እንዲሁም በጥቁር ባሕር በኩል የእህል ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ እንዲቻል ያደረጉት ስምምነቶች የተደረሱት ቱርክ ውስጥ ነው።
የአፍጋኒስታኑ የታሊባን አስተዳደር እና ፓኪስታን ኳታር ውስጥ ባደረጉት ንግግር ላይ አሸማጋይ ሆና የቀረበችው ቱርክ ነች። ኋላ ላይም በ2025 ንግግሩ ኢስታንቡል ውስጥ ቀጥሏል። ይሁን እንጂ እነዚህ ንግግሮች ስምምነት ላይ ሳይደርሳበቸው ቆመዋል።
ትሪፖሊ ውስጥ በሚገኘው የፕሬዝዳንት ምክር ቤት ስር በሚተዳደረው የሊቢያው 'ራዳ' ሚሊሻ እና አገሪቱ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት መካከል ባለፈው መስከረም ላይ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነትም የተሳካው በቱርክ የስለላ ድርጅቶች ነበር።
ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ላይ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድሮኖችን እያቀረበች ነው የሚል ክስ ባሰማበት ወቅት ኤርዶዋን ካርቱም እና አቡ ዳቢን ለማሸማገል ጥያቄ አቅርበው ነበር።
መገናኛ ብዙኃን ምን ይላሉ?
የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ መገናኛ ብዙኃን፤ ብዙውን ጊዜ "የአመራር ዲፕሎማሲ አቅኚ" ሲሉ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋንን ያሞግሷቸዋል። ቱርክንም ወደ "የዲፕሎማሲ ማዕከልነት" እንደቀየሯትም ይገልጻሉ።
"[ግጭቱ] መፍትሔ የሚያገኝ ከሆነ፤ የሚፈታው ኤርዶዋን ነው" የሚለው አገላለጽ፤ የመንግሥት ደጋፊ ተንታኞች የፕሬዝዳንቱን "የአመራር ዲፕሎማሲ" ለማወደስ ደጋግመው የሚጠቀሙበት መፈክር ሆኗል።
የመንግሥት ደጋፊ የሆነው 'የኒ ሻፋክ' ጋዜጣ በግንቦት 2025 ባተመው ጽሁፍ፤ "[በኤርዶዋን] መሪነት የሚከናወኑ ጥረቶች ቱርክ ለቀጣናዊ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ሰላም አስተዋጽኦ የምታደርግ አገር መሆኗን ያሳያሉ" ሲል አገሪቱ "በዓለም ላይ ያሉ ከባድ ግጭቶችን" ለመፍታት ያደረገውን ሽምግልና አድንቋል።
ሌላኛው የመንግሥት ደጋፊ ጋዜጣ 'ሳባህ' ደግሞ "በዓለም መሪ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የተፈቱ ቀውሶች - ቱርክ ተመልካች ሳትሆን ሰላምን የምትፈጥር አገር ናት" ሲል ጥር ላይ ባወጣው ጽሁፍ ተመሳሳይ አድንቆት አቅርቧል።
የኤርዶዋን የዲፕሎማሲ እርምጃዎች "ቱርክን ተከታይ ከመሆን ወደ መሪ የዓለም አቀፍ ተዋናይነት ቀይረዋታል" ሲል ጋዜጣው ይከራከራል።
ቱርክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተቀናቃኞቿ ጋር ያላትን መሻከር ለማርገብ የተከተለችው ሰፊ የውጭ ፖሊሲ የአሸማጋይነት ሚናዋን ለማሳደግ ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ አድርጓል።
አንካራ ቀጣናዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ያላት ፍላጎት ከዚህ ቀደም ከበርካታ አገራት ጋር ዐይን እና ናጫ አድርጓት ቆይቷል። ይህ ፍላጎቷም እንደ ግሪክ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትቶች ያሉ አገራት ላይ ጫፍ የረገጠ አቋሞችን እንድትይዝ አድርጓት ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከተለችው የተለሳለሰ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአንጻሩ ባላንጣዎችን ወደ አንድ ማምጣት የምትችል "ፍትሃዊ" አሸማጋይ ሆና እንድትቀርብ ክፍተት የሰጣት ይመስላል።
ምን እንቅፋቶች አጋጠሟት?
ምንም እንኳ የቱርክ የአሸማጋይነት ሚናዋ እየጨመረ ቢመጣም፤ ሌሎች ተዋናዮች የሚያደርጉት ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እያበሳጫት ይመስላል።
አሜሪካ ሰሞነኛው ሩሲያን እና ዩክሬንን የማሸማገል ጥረትን ያስተናገደችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ነች።
ከሞስኮ እና ኪየቭ ንግግር በኋላ መግለጫ ያወጣው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ሁለቱንም ወገኖች አመስግኗል። መግለጫው ሁለቱ አገራት "በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በሚደረገው ጥረት የምትጫወተው ሚና ላይ ያላቸውን መተማመንን" አጉልቶ አሳይቷል።
ሌላኛዋ የመካከለኛው ምሥራቅ አገር ኦማን ደግሞ ከኢራን ጋር ያላትን ነባር ግንኙነት በመጠቀም ከሰሞኑ የተካሄደው የአሜሪካ እና የኢራን ንግግርን አስተናግዳለች። ይህም ቱርክን ከጨዋታ ውጪ አድርጓታል።
አንጋፋው ቱርካዊ ጋዜጠኛ ሙራት ዬትኪን፤ በቱርክ እና በእስራኤል መካከል ያለው ባላንጣነት አንካራ የአሜሪካ እና ኢራንን ንግግር ለማስተናድ ያደረገቸው ጥረት እንዳይሳካ አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
ጋዜጠኛው "በማሸማገል [ጥረቶች] ውስጥ እንቅፋት የሚሆነው ጉዳይ የቱርክ እና እስራኤል ግንኙነት እንደሆነ ግልጽ ነው። ለእስራኤል፤ አንካራ ያንን ያህል 'የምትታመን' ተዋናይ አይደለችም፤ ግን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ልትተው የማትችል' የግንኙነት መስመር ነች" ሲል ጽፏል።
የአሜሪካ እና የኢራን ንግግር ቱርክ መካሄዱ ቀርቶ ወደ ሌላ ቦታ መዛወሩ መንግሥትን ደጋፊ ተንታኞች አስቆጥቷል።
ኢራን፤ የቱርክ "ቀጣናዊ መሪነት" እና "ዲፕሎማሲያዊ ስኬት" ስለሚያስፈራት ንግግሩ ቱርክ ውስጥ እንዳይካሄድ ጠይቃለች የሚል ክስ ጭምር አቅርበዋል።
የመንግሥት ደጋፊው ሳባህ ጋዜጣ አምደኛ የሆነው ኦካን ሙዴሪሶግሉ ባሳተመው ጽሑፍ፤ "ኢራን ታሪክ እና የዘር ልጓም ስቧታል፤ ለዚህም ሲባል ለቱርክ ክብር ወይም ቀጣናዊ ሚና መስጠት አልፈለገችም" ብሏል።
እንዲህ ዓይነቶቹ አስተያየቶች፤ ቱርክ ገንቢ ሚና ያላት አስታራቂ ሆና ለመታየት የያዘቸውን ግብ ብዙዎች አግዝፈው እንደሚመለከቱት የሚጠቁም ነው።
ምንም እንኳ ቱርክ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንቅፋቶች እያጋጠሟት ቢሆንም ይህንን ጥረቷን ግን እንደምትቀጥል ያመላክታሉ።