ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከስምምነት የደረሱበት ሰነድ ምን ይዟል?
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን አለመግባባት በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደረሱ።
ከሁለቱ አገራት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ውጥረትን አንግሶ የቆየው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከፈረመች በኋላ ነበር።
ቱርክ በአገራቱ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ፕሬዝዳንቷን ጨምሮ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካይነት ለወራት ስትጥር ቆይታ ከስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን አስታውቀዋል።
ኤርዶዋን ስምምነቱን "ታሪካዊ" በማለት በሁለቱ አገራት መካከል "ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ" እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ አንካራ ላይ ተገኝተው በተደረገው ለሰዓታት ከተካሄደ ንግግር በኋላ ነው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለጸው።
የአገራቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊ በር እንደታገኝ የሚያደርግ ነው ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
"በነበረን ስብሰባ በተለይ ኢትዮጵያ ካላት የባሕር መተላላፊያ የማግኘት ፍላጎት አንጻር፣ ወንድሜ ሼክ ሐሰን ኢትዮጵያ ወደ ባሕር መተላላፊያ በር እንድታገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል ኤርዶዋን።
በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ "በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ስር አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ" እንድታገኝ የሚያስችል የንግድ እና የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቅርበት እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።
ለዚህም ሁለቱ አገራት ንግግሮችን በማካሄድ በወራት ውስጥ አጠናቀው ለስምምነት ለመቅርብ ተስማምተዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተናገሩት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውይይቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት መቻሉን አመልከተዋል።
"የኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ የማግኘት ፍላጎት ጎረቤቶቻችንን ጭምር የሚጠቅም ሰላማዊ ጥረት ነው፣ ይህ ፍላጎት በትብብር መንፈስ እንጂ በጥርጣሬ ሊታይ አይገባውም" ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "ገንቢ ውይይት" ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን "በትብብር፣ በወዳጅነት እና በጠላትነት ሳይሆን በጋራ ለመሥራት ከሚኖር ፈቃደኝነት ጋር ወደ ቀጣዩ ዓመት ያሸጋግራል" ብለዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በበኩላቸው አንካራ ላይ የተደረሰው ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን "ልዩነት ያበቃ" ነው በማለት አገራቸው "ከኢትዮጵያ መሪዎች እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ" መሆኗን አመልክተዋል።
የአንካራው ስምምነት ነጥቦች
የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በቱርክ ፕሬዝዳንት አማካይነት ውዝግቡ ከጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ አንካራ ላይ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ከስምምነት የደረሱባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች የሚያመለክት 'የአንካራ ውሳኔ' የሚል ሰነድ ይፋ ሆኗል።
ይህ በቱርክ መንግሥት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በኩል የወጣው የአንካራ ስምነት ሰነድ በዋናነት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል አወዛጋቢ የሆነውን የባሕር መተላላፊያ የማግኘት ጉዳይን ያነሳል።
በተጨማሪም ሶማሊያ ከመጪው ጥር ወር በኋላ ከግዛቷ እንዲወጣ የምትፈልገውን በአፍሪካ ሕብረት ስር የተሰማራውን የኢትዮጵያ ሠራዊትን በሚመለከትም ከዚህ በፊት የተሠረጨውን የሶማሊያን ወቀሳ የሚያነሳ ነጥብም ተካቶበታል።
የአንካራ ስምምነት ዋነኛ ነጥቦች
- የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት ደንቦች ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር ተስማምተዋል።
- በወዳጅነት የመከባበር መንፈስ ያለፉ ልዩነቶችን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ በመተው በትብብር ለጋራ ብልጽግና ወደፊት ለመሥራት ተስማምተዋል።
- ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።
- የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ።
- ሁለቱ አገራት በቱርክ አመቻቻነት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ የቴክኒካዊ ጉዳዮች ድርድር ማድረግ የሚጀምሩ ሲሆን፣ ይህም በአራት ወራት ውስጥ የሚቋጭ ይሆናል።
- በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር መተላላፊ እንድታገኝ የሚያስችል ለሁለቱም አገራት ጠቃሚ የሆኑ የኮንትራት፣ የኪራይ፣ እና ተመሳሳይ የንግድ አሠራር መንገዶችን በጋር በመሆን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል።
- ሁለቱ አገራት የቱርክን ድጋፍ በመቀበል በስምምነቱ አተረጓጎም እና አተገባበር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በቱርክ አማካይነት በንግግር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተስማምተዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ ዕጣ ፈንታ
ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና በወቅቱ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አዲስ አበባ ላይ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ነበር በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ውዝግብ የቀሰቀሰው።
የመግባቢያ ሰነዱ ዝርዝር እስካሁን ይፋ ባይደረግም ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ለምታገኘው የአገርነት ዕውቅና ለኢትዮጵያ ንግድ እና የባሕር ኃይል መገልገያነት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ጠረፍ ለመስጠት እንደተስማሙ ተገልጾ ነበር።
የመግባቢያ ሰነዱ በተፈረመ በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ምንም ሳይባል አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።
በሶማሊላንድ በኩልም ከአንድ ወር በፊት በተደረገ ምርጫ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት የተፈራረሙት ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በተቃዋሚያቸው ተሸንፈዋል።
ሶማሊያ ስምምነቱ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በማለት የተቃወመችው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አምባሳደርን ከግዛቷ እንዲወጡ አድርጋ የራሷን አምባሳደርም ከአዲስ አበባ መጥራቷ ይታወሳል።
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከአስር ዓመታት በላይ ውዝግብ ውስጥ ከምትገኘው ግብፅ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማ፣ ኤርትራን ጨምሮ የሦስትዮሽ የትብብር ስምምነት በቅርቡ ተፈራርማለች።
ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ንግግር ለማድረግ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው ስምምነትን ውድቅ ማድረግ አለባት የሚል ቅድመ ሁኔታን በተደጋጋሚ ስታቀርብ ቆይታለች።
አሁን በቱርክ አማካይነት ስምምነት ላይ ሲደረስ የመግባቢያ ሰነዱ ውድቅ ስለመደረጉ የታወቀ ነገር የለም።