ሶማሊያ ጥያቄ ውስጥ ያስገባቸው የኢትዮጵያ ጦር የሰላም ማስከበር ሚና

ያለፉት አስር ወራት የጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸው የሻከረበት ጊዜ ነው። ለዚህም ምክንያት የሆነው ኢትዮጵያ በታኅሣሥ 2016 ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ነው።

ከዚህ ስምምነት በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል የቃላት ልውውጦች ሲካሄዱ ቆይተዋል። የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ጥሳለች የሚል ክስ በተደጋጋሚ ያቀርባሉ።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሱማሊያ አንድነት እና ሉዓላዊነት መከበር “መስዋትነት መክፈሉን” በተለያዩ አጋጣሚዎች ሚ ሲያነሱ ይደመጣሉ።

ይህ የኢትዮጵያ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮችን አስተያየት ውድቅ የሚያደርግ መግለጫ ከሰሞኑ በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ወጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ ባለፉት ጊዜያት በሶማሊያ ውስጥ ለሰላም ማስከበር የተደረገው የኢትዮጵያ ሠራዊት ስምሪት የአል-ሸባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር አድርጓል ሲል ወቅሷል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች ከግዛቷ እንዲወጡ ስትጠይቅ የቆየችው ሶማሊያ ከጥቂት ወራት በኋላ የሚያበቃውን የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ለመተካት በሚሰማራው ኃይል ውስጥ የየትኛው አገር ወታደሮች እንደሚሳተፉ የምትመርጠው ራሷ መሆኗን ገልጻለች።

የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ በአገሪቱ ወታደሮቻቸውን ካሰማሩ አምስት አገራት በተለየ የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ በማተኮር ተልዕኮው “የአል ሻባብ እንቅስቃሴ ከፍ እንዲል ከማድረግ ባሻገር ያስገኘው ለውጥ ውስን ነው” ሲል ተችቷል።

በቻታም ሐውስ ተመራማሪ እና የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ ዶ/ር አቤል አባተ፤ “በመግለጫው ላይ የተጠቀሱት እንዳንድ ነገሮች የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናትም የሚያምኑባቸው አይመስለኝም። አንዳንዶቹ የተጠቀሱት ጉዳዮች ግብታዊነት ይነበብባቸዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ይህ ግብታዊነት ዝም ብሎ የመጣ አይደለም” የሚሉት ዶ/ር አቤል፤ “ያልተቋጨው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት ትልቁ ምክንያት ነው” ይላሉ።

ተመራማሪው የሶማሊያ መንግሥት መግለጫ ሁለት ነገሮችን ያሳያል ይላሉ።

ዶ/ር አቤል በሰሞኑ መግለጫ የሶማሊያ መንግሥት “የኢትዮጵያ ጦር [በሶማሊያ] ይቀጥል የሚለውን ጉትጎታ ያስቆምልኛል ብሎ ያሰበው የሉዓላዊነት ቀይ መስመር ለማስመር የተፈለገ ይመስለኛል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተንታኙ አክለውም የሶማሊያ መግለጫ “[የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ] ስምምነት የንዴት መገለጫ አድርጌ ነው የምወስደው” ይላል።

የኢትዮጵያ ጦር ለአል ሸባብ ማንሰራራት ምክንያት ሆኗል?

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከገቧቸው ቃሎች መካከል ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሶማሊያን ሰላም የነሳትን አል ሸባብ ታሪክ አደርጋለሁ የሚለው አንዱ ነው።

አስረኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ በቪላ ሶማሊያ ሁለት ዓመታት ቆይተውም አል ሸባብን ማጥፋት አልቻሉም። አል ሸባብ አሁንም በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ የቦምብ ጥቃቶችን ይፈጽማል።

አሁንም ለሶማሊያ እና ሶማሊያውያን ስጋት መሆኑን የቀጠለው አል ሸባብ በኢትዮጵያ ስምሪት ምክንያት እንቅስቃሴው እንዲጨምር ሆኗል ሲል የሐሰን ሼክ መሐመድ መንግሥት ከስሷል።

ይህ ክስ በሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ የሚቀርብ አይደለም። ሌሎች ገለልተኛ ተንታኞችም አል ሸባብን ማንሰራራት እና እንቅስቃሴ መጨምር ከኢትዮጵያ ሠራዊት መሰማራት ጋር ያይዙታል።

በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግጭቶች እና የደኅንነት ተንታኙ ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ “የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን እናጠፋለን ብለን ገብተን አልሻባብን ነው የፈጠርነው” ብለው ነበር።

አብዱላሂ ሐሰን የተባሉ ግለሰብ እ.አ.አ በ2009 በጻፉት አንድ መጣጥፋቸው “የኢትዮጵያ ጦር አገሪቱን መቆጣጠር አል ሸባብ ከሶማሊያውያን ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል። ብዙ ሶማሊያውያን አልሸባብን ጥብቅ የጂሃዳዊ ዝንባሌው ምንም ይሁን ምን እንደ እውነተኛ የተቃውሞ ኃይል አድርገው ይቆጥሩት ነበር” ብለዋል።

ዶ/ር አቤል በበኩላቸው “ብዙ ጊዜ የሶማሊያ ባለሥልጣናትም ደጋግመው የሚያነሱት አል ሸባብ የኢትዮጵያ ወረራ ውጤት ነው የሚሉ ንግግሮችን በተደጋጋሚ እንሰማለን” ይላሉ።

“በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ኢትዮጵያ ወታደሮች መኖር ለአል ሸባብ ምልመላ ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥርለት እንደሚችል አስባለሁ” የሚሉት ተመራማሪው የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ መሰማራትን “የሃይማኖት እና የወረራ ቅርጽ እንዲይዝ ብዙ ትረት ተደርጓል በአልሸባብ በኩል በተወሰነ መልኩም ተሳክቷል” ብለዋል።

“ነገር ግን ከአጠቃላይ ሁኔታ እና ከሶማሊያ ፖለቲካዊ፣ የፀጥታ እንዲሁም የማኅበራዊ ሁኔታ አንጻር ስንገመግመው ሁሉንም ችግሮች የአል ሸባብ አልመሸነፍ እና የኢትዮጵያ ሠራዊት ከመኖሩ ጋር መያያዝ የለበትም” ሲል አክለዋል።

የአል ሸባብ ምሥረታ እና መስፋፋት ከኢትዮጵያ ሠራዊት መስፈር ጋር መያያዙ ትክክል አለመሆኑንም ዶ/ር አቤል ያነሳሉ።

“ለዚህም ሶማሊያ ችግር ውስጥ የገባችው ከአል ሸባብ መምጣት ጋር ተያይዞ እንደሆነ የሚያስመስሉ ብዙ ነገሮች አሉ” የሚሉት ተመራማሪው፤ “ነገር ግን ያንን ለማለት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጦር መሰማራት በፊት ምን ትመስል ነበር? የሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚሉትን ነገሮች በደንብ መፈተሽ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

“የሶማሊያ መንግሥት ከመቼ ጀምሮ ነው አገሪቷን ማስተዳደር ያቃተው? የአገሪቱ ሁኔታ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ምን ይመስላል?” የሚሉት ጉዳዮችም ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸውም ይጠቅሳሉ።

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኙ “እኔ በአብዛኛው ስፈትሸው የራሱ ውስንነቶች ቢኖሩበትም የኢትዮጵያ ጦር ከሌሎቹ አገራት ጦር አንጻር አንጻራዊ ሰላም በመፍጠር ረገድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምስክርነታቸውን ሰጥተውበታል” ብለዋል።

ተመራማሪው ይሄን ቢሉም ግን “በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ፣ ከአሚሶም ጋር በኅብረት የመሥራት ጉዳይ ከሌሎች ወታደሮች ካዋጡ አገራት ጋር አንድ ዕዝ እና አንድ ዓላማ ይዞ ከመንቀሳቀስ አኳያ ብዙ ውስንነቶች ነበሩበት” ይላሉ።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት ለሶማሊያ መንግሥት የዋለውን “ውለታ” በተደጋጋሚ ሲጠቅሱ ይደመጣሉ።

የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሰባት ወራት በፊት ለብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት “የሶማሊያ መንግሥት ሞቃዲሾ እንዲቀመጥ ያደረገው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው” ብለው ነበር።

ፊልድ ማርሻሉ አክለውም፤ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነገ ቢወጣ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ሞቃዲሾ የሚቀመጥ አይመስለኝም” ብለዋል።

“[የሶማሊያ ባለሥልጣናት] ሠራዊቱ ምንም እንዳላደረገላቸው ነው ሲያወሩ ነበረው፤ ይህም ውለታ ቢስነት ነው” ያሉት ኤታማዦር ሹሙ፤ ግማሽ በላይ የሚሆነው የሶማሊያ ግዛት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚጠበቅ መሆኑንም አመልክተዋልዋ።

ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ከትላንት እስከ ዛሬ

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ጦርነቶችን አድርገዋል። በተለይ ታላቋን ሶማሊያ የመፍጠር ህልም የነበረው ሲያድ ባሬ በወቅቱ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ከሚመራው የኢትዮጵያ ጦር ጋር ውጊያዎችን አድርጓል።

በሶማሊያ ሲደረግ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ተጋግሎ የሲያድ ባሬ ህልም ሲከሽፍ እና አስተዳደሩም ሲገረሰስ ሶማሊያ እንደ አገር የመቀጠሏ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገባ። ይህ የእርስ በእርስ ጦርነት ሶማሊያ ላለችበት ምስቅልቅል መነሻ ሆኗል።

ከማዕከላዊ መንግሥት መውደቅ በኋላ የጦር አበጋዞች የበላይነትን ለማግኘት ቢፋለሙም ቪላ ሶማሊያ መግባት የቻለ አልነበረም። ይህም በሶማሊያ መንግሥት እንዳይኖር፣ በጎሳ እና በሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲፋፋም አድርጓል።

ከእነዚህ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኃይል አቅሙ እየጎለበት በርካታ የሶማሊያ ግዛቶችን ለመቆጣጠር ችሎ ነበር። የቡድኑን ማንሰራራት እንደ ስጋት የተመለከተችው ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ አሰማርታ ኅብረቱ እንዲዳከም እና የያዛቸውን ግዛቶች ለቅቆ እንዲወጣ ማድረግ ችላለች።

ከዚህ የኢትዮጵያ እርምጃ በኋላ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ሶማሊያ ልኳል። ከ18 ዓመታት በፊት ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ከተለያዩ አገራት የተወጣጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለስድስት ወራት በሶማሊያ እንዲቆይ ተሰማራ።

ለስድስት ወራት የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ኃይል ግን ላለፉት 18 ዓመታት ገደማ በሶማሊያ ቆይቷል።

ከሁለት ዓመታት በፊት መጠሪያውን ከአሚሶም ወደ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) የቀየረው የሰላም ማስከበር ተልዕኮው በመጪው ጥር ወር ቆይታው ያበቃል።

የውጭ አገር ወታደሮችን ከሶማሊያ በማስወጣቱ ሂደትም በአገሪቱ የተሰማሩ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ቁጥር ወደ 2 ሺህ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

ይህን ሰላም አስከባሪ በመተካት በቀጣይ ከሚሰማሩት የሰላም አስከባሪዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲካተቱ እንደማትፈልግ ሶማሊያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ ፍንጭ ሰጥታች።

መግለጫው አክሎም ወታደሮች የሚያዋጡ አገራትን በተመለከተ የሚሰጠው ውሳኔ “ከሶማሊያ ብሔራዊ ጥቅምን እና ሉዓላዊነቷን ከማስከበር ጋር የተጣጣመ ሊሆን ይገባል” ሲል ቀጣይ ሊሆን የሚችለውን ጠቁሟል።

ይህ የሶማሊያ መግለጫ የወጣው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከኢትዮጵያ በስተቀር በሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ያላቸውን ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ቡሩንዲን እና ጂቡቲን ከጎበኙ በኋላ ነው።

የአባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው የህዳሴው ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገባቸው ግብፅ ለቀጣዩ ተልዕኮ ወታደሮችን ለማበርከት ፍላጎቷን ገልጻለች። አፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መግለጫ የግብፅን ፍላጎት በበጎ እንደሚቀበለው አስታውቋል።

ዶ/ር አቤል “በሉዓላዊነት እና በውጭ ጉዳይ ላይ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ስለሆነ፤ የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ አወቃቀር ውስጥ እንዲኖር አልፈልግም የሚለው የሶማሊያ አቋም በራሱ ከህግ አኳያ ምንም ዓይነት የህግ ክፍተት ሊገኝበት ይችላል ብዬ አላስብም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተመራማሪው አክለውም፤ “ዋና ጉዳይ መሆን ያለበት የትኛው አገር ወታደሮችን አያበርክት የሚለው ሳይሆን፣ የትኞቹ አገራት ናቸው ወታደር የሚያሰማሩት የሚለው ነው” ይላሉ።

ዶ/ር አቤል “ትንኮሳ የሚሆነው የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደሮችን አልፈልግም ማለቱ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ስጋት የሚያያቸውን አገራት ወታደሮች የኢትዮጵያ ጦርን ይተካሉ የሚለው ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

ዶ/ር አቤል “ሌሎች አካላትን ወደ አካባቢው ሲጠራ የሌሎች የጎረቤት አገራትን የፀጥታ ሁኔታ በአንድም ሆነ በሌላ ሁኔታ እንዴት ሊለወጥ ይችላል የሚለውን ነገር በስፋት እና በጥልቀት ማሰቡ ተገቢ ነው” ሲሉ ያክላሉ።።

በተጨማሪም “ብዙ አካላት ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ማን እንዴት ይሳተፍ? ይህ ደግሞ በኢትዮጵያን እና በአካባቢው አገራት የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ጥላ ሳያጠላ እንዴት መደረግ አለበት? የሚለው በደንብ መታሰብ ይኖርበታል።”

የግብፅ ጦር በሶማሊያ መስፈር የሚኖረውን ስጋት ሲያብራሩ “የግብፅ ጦር ሶማሊያ ውስጥ ሰፈረ ማለት ኢትዮጵያ አካባቢውን በጎሪጥ ማየት፥ አካባቢው ላይ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ማጠናከር፣ በድንበር አካባቢ ሠራዊት የማከማቸት እንቅስቃሴዎች ማድረግ አስፈላጊ ከሆነ ልምምዶችን ማደረግ [ይከተላል]” ይላሉ።

ግብፅ እና ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ የገቡት ከ150 ዓመታት በፊት መሆኑን ያስታወሱት ተመራማሪው፤ “አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ የግብፅ እና የኢትዮጵያ ወታደሮች ፊት ለፊት ሊገናኙ እና ወደ ቀጥታ ግጭት ሊያመራ የሚችለበትን ዕድል ሊፈጠር ይችላል። ትንሽ ስህተት ወይም ትንኮሳ ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አይተናል” ሲሉም ተናግረዋል።