ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከኢትዮጵያ ድንበር ወደ ሶማሊያ የሚደረገው አደገኛው ሕገወጥ የአልኮል ዝውውር ንግድ
በሶማሊያ የአልኮል መጠጥ መጠጣት፣ መሸጥ፣ መግዛት እንዲሁም ማከፋፈል በሕግ የተከለከለ ነው።
ሆኖም የአልኮል መጠጦች አሁንም ከኢትዮጵያ በድብቅ ወደ አገሪቷ ይገባሉ።
በመዲናዋ ሞቃዲሾ ጂን፣ ቢራ፣ ቮድካ፣ አረቄ መንቆርቆራቸው አልቀረም።
ለዚህ ደግሞ እንደ ጉሌድ ዲሪ ያሉ የአልኮል መጠጥ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ዋነኛ የጀርባ አጥንት ናቸው።
መጠጡ መነሻው ከኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ሲሆን፣ መዳረሻውን ሞቃዲሾ ያደርጋል።
እንደነ ጉሌድ ያሉ አዘዋዋሪዎች በሕይወታቸው ዋጋ ለመክፈል ቆርጠው ነው መጠጦቹን የሚያዘዋውሩት።
ለቀናት አለመተኛት፣ የታጣቂዎች ጥቃት፣ በአልሻባብ ወይም በፖሊስ እንያዝ ይሆን የሚለው ሰቀቀን እና ስጋት ሌላም ሌላም የሚያልፉባቸው ውጣ ውረዶች ናቸው።
ጉሌድ ከፍተኛ ድካም እንደሚነበብበት ፊቱ ያሳብቃል።
ቢቢሲ በሞቃዲሾ ያገኘው ከኢትዮጵያ ድንበር የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኖ ከጉዞው በተመለሰበት ወቅት ነው።
የ29 ዓመቱ ወጣት ነጠላ ጫማ በአቧሯ ተሸፍኗል።
ዓይኑ ላይ የሚታየው ድካም በርካታ ምሽቶችን ያለ እንቅልፍ በአደገኛ መንገዶች እና ታጣቂዎች ባሉበት የፍተሻ ኬላዎችን እንዳሳለፈ ይናገራሉ።
ይህ ብቻ አይደለም በጥይት ተመትቶ የተገደለው አዘዋዋሪው ጓደኛው ትዝታም ከእንቅልፉ የሚያባንነው ጉዳይ ነው።
“በዚህች አገር ሁሉም ይታገላል፣ መውጫም እየፈለገ ነው። እኔም አዘውትሬ ከኢትዮጵያ ድንበር ወደ ሞቃዲሾ በማደርገው ጉዞ የዕለት ጉርሴን አገኘሁ” የሚለው ጉሌድ በኮንትሮባንድ መንገድ የሚያደርገው የአልኮል መጠጥ ዝውውር ከራሱ አልፎ ቤተሰብ አስተዳዳሪ አድርጎታል።
ሶማሊያ የሸሪዓ ሕግን መሠረት አድርጋ ባወጣችው ሕግ የአልኮል መጠጥን ብትከለክልም የበርካቶችን በተለይም የወጣቶችን ፍላጎት መግታት አልቻለችም።
ጉሌድ ከአዘዋዋሪነት ሕይወቱ በፊት የሚኒባስ ታክሲ ሹፌር ነበር።
በሞቃዲሾ ባጃጆች ተመራጭ ሆነው ታክሲዎችን ከሥራ ውጭ ሲያደርጓቸው ጉሌድም መከራ ገጠመው። በዚህም ወቅት ነው ጎረቤቱ አብሽር የአልኮል ኮንትሮባንድ ንግድን ዓለም ያስተዋወቀው።
ሁለቱ ከጎረቤትነት አልፈው ፈታኝ መከራዎችን ያዩ እና ያሳለፉ የልጅነት ባልንጀሮች ናቸው። አብሽር የሚያምነው ሰው ነው።
“እሱን ወክዬ በሞቃዲሾ በተመረጡ ቦታዎች የአልኮል መጠጦችን ከተመረጡ ቦታዎች መውሰድ፣ ማዘዋወር እንዲሁም በሚልከኝ ቦታዎች ማራገፍ ጀመርኩ። በዚያን ወቅት ኮንትሮባንድ መሆኑን አላወቅኩም” ነበር ይላል።
ጉሌድ በዚህም ሕገወጥ የአልኮል ዝውውርን ዘው ብሎ ገባበት። በሶማሊያ ገጠራማ ቦታዎች ተጉዞ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመሄድም መጠጦችን ማጓጓዝ ጀመረ።
ሕግ እየጣሰ መሆኑን ቢረዳውም ከተዘፈቀበት ድህነት አንጻር ምንም አማራጭ የለኝም ይላል።
የኮንትሮባንድ ጉዞው የሚጀምረው በሶማሊያ እንደ አቡድዋክ፣ ባላንባሌ፣ ፌርፌር እና ጋልዶብ ካሉ የድንበር ከተሞች ነው።
የኢትዮጵያዋ ሶማሌ ክልል ከሶማሊያ ጋር አንድ ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የድንበር መሬትን ትጋራለች።
“የአልኮል መጠጡ መነሻው ከአዲስ አበባ ሲሆን፣ በመቀጠልም ወደ ጅግጅጋ ከተማ ይመጣል” ይላል።
አልኮሉ ከአዲስ አበባ ወደ ሶማሌ ክልል ተጭኖ ከመጣ በኋላ ከዚያም በድብቅ ወደ ሶማሊያ ድንበር ይሻገራል።
የድንበር ከተማዋ ጋልጋዶብ ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የሚመጡ የአልኮል መጠጥ ዋነኛ መሸጋገሪያ እና ማዕከል በመሆኗ ክፉኛ ተጎድታለች።
የአካባቢው የጎሳ ሽማግሌዎች በአልኮል መጠጦች ምክንያት በከተማዋ ላይ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው ስጋቶች ናቸው።
“አልኮል በርካታ ክፉ ነገሮች ለምሳሌ የተኩስ ልውውጦችን እያስከተለ ነው” ይላሉ የከተማዋ የጎሳ ምክር ቤት ሰብብቢ ሼክ አብደላ መሐመድ አሊ።
“በተለያዩ አጋጣሚዎች ይዘን ብናወድመውም ማቆሚያ የለውም። ከአልኮል ፋብሪካ አጠገብ የመኖር ያህል ነው። ምንም ብናደርግ የአልኮል መጠጦቹ መጉረፋቸውን አላስቆመውም” ይላሉ።
በዚህም ምክንያት ከተማዋ ሁልጊዜም አደጋ እንደተጋረጠባት ነው ሼክ አብደላ እንደሚያስረዱት።
ነገር ግን እንደ ጉሌድ ላሉ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ግባቸው መጠጡን በዚህች ከተማ አሻግሮ ወደ ሞቃዲሾ ማድረስ ነው።
“አትክልት፣ ድንች እና ሌሎች የምግብ ፍጆታዎችን የሚጭን መኪና እነዳለሁ። ነገር ግን ከፍተኛውን ገንዘብ የማገኘው ከማጓጉዘው የአልኮል መጠጥ ነው” ይላል።
አንዳንድ ጊዜም ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ መጠጡን ለመውሰድ ወደ ኢትዮጵያ ይሻገራሉ። በሌላ ወቅት ደግሞ ድንበር ላይ ሆነው ይቀበላሉ። ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረውም ሆነ ድንበር ላይ መጠጡን ቢቀበሉ ዋነኛው ጉዳይ እንዴት ይደበቃል የሚለው ነው።
ምክንያቱም ቢያዙ ያለው አደጋ በእጅጉ ከባድ ነው።
“መሠረታዊው ሥራ የጫኚው ሥራ ነው። ከማሽከርከር በበለጠ፤ ጫኚው በጭነት መኪናችን ውስጥ የሚጓዘውን የአልኮል መጠጥ የመደበቅ ኃላፊነት አለበት። ጫኚው መጠጡን በድብቅ ካልጫነ በቀላሉ እንዲህ መንቀሳቀስ አንችልም” ይላል።
“አንድ ሳጥን በአማካይ 12 ጠርሙሶች አሉት። በአንድ ጉዞ ከ50 እስከ 70 ሳጥኖችን አጓጉዛለሁ። አብዛኛውን ጊዜ የመኪናዬ ግማሹ ጭነት በአልኮል ይሞላል” ይላል ጉሌድ።
ደቡባዊ እና መካከለኛ ሶማሊያ የሚገኙ ትልልቅ ግዛቶች የፌደራሉ መንግሥት ያለው ቁጥጥር አናሳ ነው ወይም ከቁጥጥሩ ውጪ ናቸው። እነዚህን ስፍራዎች ሚሊሻዎች፣ ሽፍቶች እንዲሁም አልሻባብ በዋነኝነት ይቆጣጠሩታል።
“በፍጹም ብቻህን መጓዝ አትችልም። በጣም አደገኛ ነው። በዚህ ስፍራ ስንጓዝ ሞት ሁልጊዜም በሃሳባችን ይመላለሳል” የሚለው ጉሌድ ሆኖም የሞት ቅርብ መሆን ከጉዞው አላደናቀፈውም።
“በመንገዳችን ላይ ጥቃት ተሰንዝሮብን ከተጎዳሁ ጉዞውን የሚቀጥል አጋር ሊኖር ይገባል። አብረውን የሚሆኑት እንዴት መንዳት እንዳለባቸው እንዲሁም መንገዶቹን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው” ሲል ያስረዳል።
ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በጭቃማ፣ ኮረኮንች እንዲሁም ለአስርት ዓመታት እድሳት ባልተደረገባቸው መንገዶች ላይ መንዳት አለባቸው። ከዚህ ቀደም በነበሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች የተረፉ እና የተቀበሩ ፈንጂዎችም ሌላ ስጋት ናቸው።
“ሞቃዲሾ ለመድረስ ቢያንስ ከስምንት እስከ 10 ከተሞችን አቆራርጣለሁ። በዋነኝነት ከተሞቹን ሳይሆን የፍተሻ ኬላዎችን ማን እንደሚቆጣጠራቸው ነው ትኩረታችን” ይላል ጉሌድ።
በመንገዶቻቸው ሌላ የሚያጋጥማቸው የተለያዩ የጎሳ ሚሊሻዎች ናቸው።
“የጎሳ ሚሊሻዎች መንገዶቻችንን ከዘጉብን ከመካከላችን ያለሰው ከሚሊሻዎቹ ጎሳ ወይም ከንዑስ ጎሳ ከሆነ በሕይወት የመትረፍ ዕድላችን ይጨምራል። ለዚያም ነው በአንድ ላይ የምንጓዘው ሦስታችን ከተለያየ ጎሳ የሆንነው” ይላል።
በመንገዱ ላይ በርካታ ጥቃቶች አጋጥመውታል።
አንዱን ግን ሁልጊዜም አይረሳውም። አብሮት ከሚሠሩት ውስጥ አንዱ በአንጻራዊነት አዲስ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የተገደለውን ረዳቱን ተክቶ ነው የገባው።
በሚያቀልጥ ሙቀት ውስጥ ለስድስት ሰዓታት እየነዳ የነበረው ጉሌድ እረፍት ለመውሰድ ረዳቱን እንዲነዳ ጠየቀው።
ከጀርባ መቀመጫው ላይ ተኝቶ እያለም ከፍተኛ የጥይት ድምጽ አነቃው። “በሚሊሻዎች ተከብበናል። ጫኚው ከሹፌሩ አጠገብ ተጎንብሶ እየጮኸ ነበር” ይላል።
በዚህም ጥቃት ረዳት አሽከርካሪው ተገደለ። ነገሮች ሲረጋጉ የሞተውን ባልደረባቸውን ኋላ ወንበር ላይ አስተኙት።
መኪናው በደም ታጠበ። እስካሁን ድረስ ያ ትዕይንት ከአዕምሮው አይጠፋም። ከታጣቂዎቹ ራቅ ብለው ከነዱም በኋላ መንገድ ዳር ላይ አስክሬኑን አኖሩት። ሰውነቱን የሚሸፍኑበት አንሶላ እንኳን ስላልነበራቸው ጉሌድ ሸሚዙን አውልቆ አለበሰው።
“በጣም ከባድ ውሳኔ ነበር። ነገር ግን በመኪናዬ አልኮል ጭኜ አስክሬን ተሸክሜ መንዳት እንደማልችል አውቀዋለሁ። ከፊታችን ጥቂት የመንግሥት የፍተሻ ኬላዎች ነበሩ እናም ሕይወቴን አደጋ ላይ መጣል ሆነብኝ” ሲል የሚናገረው ጉሌድ ሆኖም ከሁለት ዓመት በኋላ መንገድ ላይ የጣለው አስክሬን ጸጸት የእግር እሳት ሆኖበታል።
የሟቹ ቤተሰቦች ምን ይሉ ይሆን? የሚለውም ሌላ በጸጸት የሚያንገበግበው ጉዳይ ነው።
ሌላኛው ሕገወጥ የአልኮል አዘዋዋሪ የ41 ዓመቱ ዳሂር ባሬ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያህል ከኢትዮጵያ የአልኮል መጠጦችን በማመላለስ ኑሮውን መሥርቷል።
ዳሂር አሁን በአሽከርካሪነት መጠጥ ከድንበር በማምጣት ከመሰማራቱ በፊት በሞቃዲሾ ባለ ሆቴል የጥበቃ ሥራ ይሠራ ነበር። ሆኖም የተጠመዱ የመኪና ቦምቦች እንዲሁም ሌሎች አደጋዎች ባሉበት 100 ዶላር በየወሩ እየተከፈለው መሥራት ፈታኝ ሆነበት። አንደኛው የጥበቃ ሠራተኞች በድንበር ላይ ከሚሠሩ ሰዎች ጋር አገናኘው።
“ከዘጠኝ ዓመት በፊት በአንድ ጉዞ 150 ዶላር አገኝ ነበር። በዚያን ወቅት አልሻባብ የበለጠ ግዛቶችን ይቆጣጠር ስለነበር የበለጠ አደገኛ ነበር “ የሚለው ዳሂር፣ አሁን በአንድ ጉዞ 350 ዶላር ወይም 42 ሺህ ብር ያገኛል።
በዚያን ጊዜ አልሻባብ ብቻ ሳይሆን “ሽፍቶች እና ሚሊሻዎችም የበለጠ አደገኛ ነበሩ” ይላል።
በወቅቱ ሚሊሻዎች መንገድ ላይ አግተው ገንዘብ መጠየቅ የተለመደ እንደነበር ይገልጻል።
የአልሻባብ ታጣቂዎች ደግሞ ከያዟቸው ሁኔታው የበለጠ የከፋ ይሆናል። የአልኮል መጠጦችንም ሆነ የትኛውንም ኮንትሮባንድ የማይታገሱት የአልሻባብ ታጣቂዎች፣ ካገኟቸው ተሽከርካሪውን በእሳት ካቃጠሉ በኋላ አዘዋዋሪዎቹን በቁጥጥር ስር አውለው ይቀጣሉ።
ሌሎች ታጣቂዎች ግን በገንዘብ ወይም በአልኮል መጠጥ በቀላሉ ይደለላሉ ይላል።
ከኢትዮጵያ ድንበር ወደ ሞቃዲሾ ለመድረስ በአማካይ ከሰባት እስከ ዘጠኝ ቀናት ይወስድባቸዋል። ሞቃዲሾ ከደረሱም በኋላ ቀድሞ ወደተዘጋጀ ማራገፊያ ቦታ ጭነቱን ይወስዱታል።
እዚያ ሲደርሱም የተወሰኑ ግለሰቦች መጥተው የጫኑትን ምግብ አራግፈው በሌላ የጭነት መኪና እንደሚወስዱት ጉሌድ ይናገራል።
ከዚያ በኋላ ሌሎች ሰዎች ይመጡና አንዳንዴም በሌላ መኪና ታጅበው የአልኮል ሳጥኖቹን እንደሚወስዱ ጉሌድ ይገልጻል። ከዚያ በኋላ የአልኮል መጠጡ በተለያዩ ሰዎች እጅ በኩል አልፎ በመጨረሻም በከተማዋ ውስጥ ካሉ ነጋዴዎች ጋር ይደርሳል።
እነዚህን ነጋዴዎቹ በቀላሉ በስልክ ማግኘት ቀላል እንደሆነ ነው ጉሌድ የሚያስረዳው።
የጉሌድ ጓደኛ አብሽር ይህንን የአልኮል ዝውውር ካቆመ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል።
አብሽር ሥራ አጥ ምሩቅ የነበረውን የወንድሙን ልጅ ወደ ሕገወጥ ዝውውር አስገባው። ልጁም በሦስተኛ ጉዞው ባደፈጡ ሽፍቶች ተገደለ። አብሽር ከዚህ በኋላ እርግፍ አድርጎ ፊቱን ወደ ፈጣሪው አዙሯል “ብዙም አላገኘውም” ይላል ጉሌድ።
ሆኖም “ሞት ዕጣ ፈንታችን ነው። ፍርሃት የዕለት ጉርሴን በማገኝበት ሁኔታ እንዲመጣብኝ አላደርግም። አዎ አንዳንድ ጊዜ ሁሉንም ትቼ ሕይወትን እንደ አዲስ መጀመር እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን ቀላል አይደለም። ድህነት ዓይኑን አፍጥጧል” ይላል ጉሌድ።
*በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ሰዎች ስም ተቀይሯል።