የሶማሌ ክልል ተወካዮች የትኛዎቹን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር አቀረቡ?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል ባደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ የክልሎች እና መንግሥት አወቃቀር፣ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ እንዲሁም የታሪክ አዘጋገብን የተመለከቱ አጀንዳዎች መቅረባቸውን ተሳታፊዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ክልሉን ወክለው አጀንዳ ማዋጣት ላይ ከተሳተፉት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል “አብዛኞቹ እውነተኛ ፌደራሊዝም” የመተግበርን ሀሳብ ሲያነሱ “የተወሰኑት ክልሎችን በኮንፌደሬሽን ማዋቀርን” በአጀንዳነት እንዳቀረቡም ተገልጿል።

በተለያዩ ክልሎች ውስጥ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደትን እያከናወነ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ከባለድርሻ አካላት አጀንዳ መሰብሰብ የጀመረው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም. ነበር።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከክልሉ መንግሥት ተወካዮች፣ ከልዩ ልዩ ማኅበራት እንዲሁም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተወጣጡ ከ1,200 በላይ ወኪሎች እንደተሳተፉ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ከወረዳ ጀምሮ በተሰበሰቡት አጀንዳዎች ላይ ለሦሰት ቀናት ሲመክሩ የነበሩት ክልሉን የወከሉ ተሳታፊዎች፤ ረቡዕ ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም. “ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ አጀንዳዎችን” ለይተው ለኮሚሽኑ ማስረከባቸው ተገልጿል።

የሶማሌ ክልል ተወካዮች ለኮሚሽኑ ካቀረቧቸው አጀንዳዎች መካከል የመንግሥት እና የክልሎች አወቃቀር፣ የሕገ መንግሥት ለውጥ፣ የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ፣ ከሀብት ክፍፍል እንዲሁም ከድንበር ግጭቶች ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች መቅረባቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ ለሀገራዊ ምክክሩ በአጀንዳነት መቅረቡን የጠቀሱት ቀዳሚው ጉዳይ የሀገሪቱ መንግሥት እና የክልሎች አወቃቀርን የተመለከተው ይገኝበታል። የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት የነበረው የፌደራሊዝም ትግበራ “ችግር ያለበት” እንደሆነ ማንሳታቸውን የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትን ወክለው የተሳተፉት አቶ ሙክታር አሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሶማሊ ነን ስቴት አክተርስ ኮሊዥን” የተባለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አሊ እንደሚገልጹት በፌደራሊዝም ሥርዓቱ ላይ ከተነሱ ጉድለቶች መካከል ከዚህ ቀደም በነበሩ መንግሥታት ይታይ የነበረው “ጣልቃ ገብነት” ይገኝበታል።

“[ከዚህ በፊት] ከፌደራል እየመጣ ጣልቃ ገብነት፣ ክልሉን እንደ ፈለጉ የሚጫወቱበት [ሁኔታ] ነበር። አሁን አብዛኞቹ የሚሉት ‘እውነተኛ ፌደራሊዝም እንፈልጋለን’ ነው” ሲሉ ተሳታፊዎች ያነሱትን ሀሳብ አብራርተዋል።

“በአብዛኞቹ” ተሳታፊዎች ተቀባይነት ያገኘው ሀሳብ ይህ ቢሆንም፤ “አንዳንዶች የኮንፌዴሬሽን አወቃቀርም” አጀንዳ እንዲሆን ማቅረባቸውን አቶ ሙክታር ገልጸዋል። ይህንን ሀሳብ ያነሱ ተሳታፊዎች የጠቀሱት ዋነኛ ምክንያት “ለክልሎች የበለጠ ሥልጣን ይሰጥ” የሚል እንደሆነ አቶ ሙክታር ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እና ምሁራንን የወከሉ ሌላ ተሳታፊም ይህ አጀንዳ ለኮሚሽኑ መቅረቡን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። እኚህ ተሳታፊ በበኩላቸው “ወደ አሃዳዊ ሥርዓት መመለስ የሚፈልጉ ቡድኖች አሉ” የሚለው ስጋት “ክልሎችን በኮንፌዴሬሽን ማዋቀር” ለሚለው ሀሳብ በምክንያትነት መጠቀሱን አስረድተዋል።

“[ኮንፌዴሬሽን] በአብዛኞቹ ተሳታፊዎች ተቀባይነት የነበረው ሀሳብ አይደለም። [ሀሳቡን የደገፉት] ከተሳታፊዎቹ 25 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ናቸው” ሲሉ “አብዛኞቹ” ተሳታፊዎች በሥራ ላይ ያለውን የፌደራላዊ ሥርዓት “ወደ ትክክለኛ ትግበራ” ማስገባት የሚለውን አጀንዳ መደገፋቸውን ገልጸዋል። ሁለቱም ሀሳቦች በአጀንዳነት መካተታቸውን አክለዋል።

ምሁራንን የወከሉት ተሳታፊ እንደሚገልጹት “በአብዛኞቹ” ተሳታፊዎች ዘንድ ተቀባይነት የነበረው ሀሳብ ተያያዥ ሃሳብ በሥራ ላይ ያለው “የብሔር ፌደራሊዝም መነካት የለበትም“ የሚል ነው። “አብዛኞቹ ያሉት ‘ልናምነው የምንችለው ብቸኛው ሥርዓት እውነተኛ የብሔር ፌደራሊዝም’ ነው” ሲሉ በአጀንዳነት የተካተተውን ሃሳብ አንስተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 39 ላይ የተቀመጠው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እስከ መገንጠል ድረስ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት “የማይነካ” ብለው ካቀረቧቸው ጉዳዮች መካከል እንደሆኑም ተወካዩ አስረድተዋል።

ተሳታፊዎች፤ “አንቀጹ ለሶማሊዎች መብት ዋስትና ነው። በሶማሊዎች በኩል የማይነካ [ጉዳይ] ነው። [አንቀጽ 39] ከኢትዮጵያውያን ጋር ያያዘን ሙጫ (glue) ነው” የሚል መከራከሪያ መቅረባቸውንም ጠቅሰዋል።

የአንቀጽ 39 ጉዳይ “ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻል ከሆነ መነካት የሌለባቸው ጉዳዮች” ተብለው በተሳታፊዎች ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል እንደሆነ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትን ወክለው የተሳተፉት አቶ ሙክታርም በተመሳሳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ፌደራሊዝሙን ለመጠበቅ [ሲባል] አንቀጽ 39 እስከ መገንጠል ሚለው ‘የማይነካ ነው’ ብለዋል” ሲባል አጀንዳው መቅረቡን አረጋግጠዋል።

ከፌደራሊዝም ሥርዓት ጋር በተያያዘ በአጀንዳነት እንደቀረበ ተሳታፊዎቹ የገለጹት ሌላኛው ጉዳይ የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋን የሚመለከት ነው። የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኩ ተሳታፊዎች የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ “ሁሉንም የሚያስማማ መሆን አለበት” የሚል ሀሳብ ማንሳታቸውን ሁለቱ ተወካዮች ተናግረዋል።

ተሳታፊዎች፤ የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ “ለምን አማርኛ ብቻ ይሆናል?” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን የሚናገሩት አቶ ሙክታር፤ “ሁሉም የሚቀበለው አንድ ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ ይሁን” የሚል ሀሳብ መቅረቡንም አንስተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደሚገልጹት የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋን በተመለከተ ሁለት አማራጮች የቀረቡ ሲሆን፣ አንድኛው “ሌሎች የሀገሪቱ ቋንቋዎችም በፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋነት ይካተቱ” የሚል ነው። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ “እንግሊዝኛ ቋንቋን” የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ማድረግ እንደሆነ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

አቶ ሙክታር እንደሚያስረዱት እንግሊዝኛ ቋንቋ በአማራጭነት የቀረበው “ዓለም አቀፍ ቋንቋ” በመሆኑ እና “ለሁሉም እኩል ነው” በሚል ነው።

“የሥልጣን ክፍፍል” ከፌደራሊዝም ጋር በተያያዘ የተነሳ አንዱ አጀንዳ እንደሆነ አቶ ሙክታር ጠቅሰዋል። “በፌደራል ደረጃ፣ በመከላከያ፣ በውጭ ጉዳይ ኢንባሲዎች ብዙ ሶማሌ ሠራተኞች የሉም" በሚል ይህ እንዲስተካከል የሚጠይቅ አጀንዳም መቅረቡን አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ተወካዮች በሀገራዊ ምክክር ላይ እንዲቀርብ ያነሱት ሌላኛው “ዋነኛ” ጉዳይ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል። የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ “ባለበት ይቀጥል ወይስ ይቀየር” የሚለው በመድረኩ ላይ የተነሳ ጉዳይ ነበር።

አቶ ሙክታር እንደሚገልጹት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዲቀየር የሚጠይቅ አጀንዳ ያቀረቡ ተሳታፊዎች የጠቀሱት ምክንያት “ክርስትናን መሠረት ያደረገ ነው። ሁሉንም አይወክልም” የሚል ነው። “አንዳንዶቹ ደግሞ መሃል ላይ ያለው ኮከብ ሁሉንም ሕብረተሰብ ስለሚወክል እንደዚያው ቢተው ብለዋል” ሲሉ በተቃራኒነት የተነሳውን መከራከሪያ አስረድተዋል።

ምሁራንን የወከሉት ተሳታፊ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማው እንዲቀየር የሚጠይቁ ተወካዮች “በዚህ ሰንደቅ ዓላማ ስር ግፍ አስተናግደናል” የሚል መከራከሪያ ማንሳታቸውን ተናግረዋል። ይህንን ጨምሮ ሀገሪቱ የቀን አቆጣጠር ላይ የተነሱ ተመሳሳይ ሀሳቦች በአጀንዳነት መቅረባቸውን ሁለቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በክልሉ ተወካዮች በአጀንዳነት እንደቀረበ የተጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ የታሪክ አዘጋገብን የተመለከተ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ አዘጋገብ “ለሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ቅድሚያ ይሰጣል” የሚል ትችት በውይይቱ ላይ መነሳቱን ምሁራንን የወከሉት ተሳታፊ ተናግረዋል።

ይህ ሀሳብ መነሳቱን ያረጋገጡት የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትን የወከሉት አቶ ሙክታር፤ የሶማሌ ሕዝብ “በጀግንነታቸው” የሚጠቅሳቸው ግለሰቦችን “ታሪካቸው በሕዝቡ ተፅፎ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል መሆን አለበት” የሚለው በአጀንዳነት የተከሳ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከክልሉ ተወካዮች የቀረቡትን አጀንዳዎች የተቀበለው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ሂደት ያከናውናል። ኮሚሽኑ ከሁሉም ክልሎች ከሚያሰባስባቸው አጀንዳዎች መካከል የተመረጡት የሁሉም ክልል ተወካዮች በሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ ጉባኤ ላይ ለምክክር ይቀርባሉ።