ቴሌቪዥንን ለመፍጠር የተደረገው የአንድ ሰው ፈታኝ ጥረት እና በቲቪ የታየው የመጀመሪያ ግለሰብ

የቴሌቪዥን ፈጣሪው ከሠራው ማሽን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Alamy

ተመራማሪዎች እስከ 1850 ድረስ ቴሌቪዥንን ለመፍጠር ሲሠሩ ነበር። ነገር ግን የወዳወቁ መብራቶች፣ የእንጨት ቁርጥራጮች እና ጣሳዎች የሚሠራ አንድ ፈር ቀዳጅ ሰው ምናብን ወደ ዕውን ቀይሯል።

ጆን ሎጊ ቢርድ ይህን ፈር ቀዳጅ ፈጠራን ከመሥራቱ በፊት ከፊል ስኬት የነበረው መዋዕለ ነዋይ አፍሳሽ ነበር። አብዛኛውን ሕይቱን ጤንነት ርቆት ያሳለፈው ጆን፤ የቄስ ልጅ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለወታደራዊ ምልመላ ብቁ ባለመሆኑ አልዘመተም።

ይልቁንም እምቅ የሥራ ፈጠራ ፍላጎትን አዝሎ የኤሌክትሪክ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ።

አርዓያው የሆነው የሳይንስ ልብ ወለድ ፀሐፊ የሆነው ኤችጂ ዌልስ በፃፈው አጭር ታሪክ በመነሳሳት ከፍተኛ የኤክትሪክ ኃይል በመጠቀም ሠው ሰራሽ አልማዝ ለመፍጠር ሞክሯል። በዚህም የግላስኮውን የኃይል አቅርቦት በከፊል በማውደም ብቻ ስኬታማ ነበር።

የዘመናችን የቴሌቪዥን አቅራቢዎች "ቤታችሁ ይህን አትሞክሩ" ብለው ማስጠንቀቂያ የሚሰጡባቸውን ድርጊቶች በመፈፀም ቁጥር አንድ ነው።

የቴሌቪዥን ሙከራ ጅማሮ

ቢርድ በእነዚህ መሰናክሎች ወደ ኋላ ቢጎተትም የንግድ ስኬቶችን ማግኘት ግን ችሏል። የአክሲያን ድርሻውን እና የሳሙና ንግዱ በመሸጥ በ1923 በእንግሊዝ ደቡብ ጠረፍ በሚገኘው ሄስቲንግስ መጠነኛ ግቢ ቤት ተከራየ። የባሕሩ አየር ደካማ ለሆነው አተነፋፈሱ መልካም ቢሆንለትም፤ የሥራ ከባቢው ግን ለጤና እና ደኅንነት ፈታኝ ነበር።

ቴሌቪዥን የመፍጠር ሙከራውን ለመጀመር ቤተ ሙከራውን ማደራጀት ጀመረ፤ ቀድሞ በቁርጥራጭ ቁሳቁሶች ይሠራበት የነበረውን ሁኔታ ወደ ሞተር አሻሻለ።

የቢርድ የፈጠራ ሥርዓት ዋነኛ ማጠንጠኛ በከፍተኛ ፍጥነት የሚሽከረከር ትልቅ ሳህን ከፍተኛ ብርሃን በመጠቀም ምሥሎችን ይቃኛል። እነዚህ ሦስት መስመሮች ከዚያም በማሠራጨት እና ተንቃሳቃሽ ምሥሎችን ለመፍጠር ይገጣጠማሉ። ምሥሎችን ማስተላለፉ ሲሳካለት ቴሌቪዥን የመፍጠር የአስርት ዓመታት ህልሙ መሬት ረገጠ።

ቢርድ በመኖሪያ ቤቱ በገነባው ቤተ ሙከራ ኤሌክትሪክ ጨብጦ ቃጠሎ ከደረሰበት በኋላ ወደ ብርሃኗ ለንደን ለመዘዋወር ወሰነ፤ አዲስ ቤተ ሙከራ ከፈተ። ቁሳቁሶቹ ከባድ ሙቀት የሚለቁ በመሆናቸው ሰው ልጅ ሊቋቋመው ፈታኝ ነበር።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 1925 የ37 ዓመቱ ቢርድ ለሙከራው የሚሳተፍ በጎ ፈቃደኛ ሰው በማግኘት አስገራሚ ግኝት መፍጠር ችሏል።

የ20 ዓመቱ ዊሊያም ታይንተን ከቢርድ ቤተ ሙከራ አንድ ወለል ዝቅ ብሎ ቢሮ ውስጥ እየሠራ ነበር። ከዚያች ታሪካዊ ቀን ከ40 ዓመታት በኋላ ለቢቢሲ ሲናገር "ቢርድ በጉጉት ተሞልቶ እየሮጠ መጣና ከቢሮዬ ጎትቶ ወደ ትንሿ ቤተ ሙከራው ወሰደኝ። ይመስለኛል በወቅቱ በጣም ስለደተሰተ አንድ ቃል ከአፉ ማውጣት አልቻለም። ጎተት አደረገኝ እና በተቻለ ፍጥነት ወደ ላይ እንድወጣ ፈለገ።"

ጆን ሎጊ ቢርድ ከፈጠራዎቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቢርድ መሰናክሎች ወደ ኋላ ቢጎትሩትም የተወሰነ የንግድ ስኬቶችን ማግኘት ችሏል

የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ክፍያ

ታይንተን የቢርድ የተዘበራረቀ ቤተ ሙከራን ሲመለከት ወደ ኋላ ለመመለስ ፍላጎት እንዳደረበት ተናግሯል። ምክንያቱም ጣራው ላይ የተንጠለጠሉ እና ግድግዳው ላይ የተበታተኑ ገመዶችን ማለፍ ነበረበት። "በዚያን ጊዜ ይጠቀምበት የነበረው መሳሪያ የተበታተነ ነበር" ብሏል ታይንተን።

ቢርድ ማሠራጫው ፊት ለፊት ላይ አስቀመጠው። ግዑዝ አካል ማንሳት ያልቻለውን እንቅስቃሴ እንዲያሳይ ፊት ለፊት ተደቀነ። ታይንተን ሙቀቱ እንደተሰማው እና ፍርሃት እንዳደረበት ቢናገርም፤ ቢርድ ግን ምንም የሚያስፈራው ነገር እንደሌለ እንዳረጋገጠለት ተናግሯል።

"ምሥል ማየት ይችል እንደሆነ ለማየት ወደ መቀበያው ጥሎኝ ሄደ" ሲል ታይንተን ያስታውሳል። "ትኩረት አደረግኩ፤ ነገር ግን ከአምፖሎቹ በሚወጣው በጣም በሚያስፈራው ሙቀት ምክንያት ከአንድ ደቂቃ በላይ መቆየት አልቻልኩም፤ ስለዚህ ወጣሁ።"

ለዚህ ድካሙ ቢርድ ሁለት ሽልንግ ከስድስት ሳንቲም ከፍሎታል። ይህም "የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ክፍያ" ነው።

በቴሌቪዥን ከታዩት የመጀመሪያዎቹ ምሥሎች ውስጥ አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቴሌቪዥን የታየው የመጀመሪያው የሰው ምሥል "በጣም የተደፈጠጠ" እና "ጥራት የሌለው" ነበር

በመላው ዓለም ቤቶች ውስጥ

አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ለመመልከት ቢርድ ምላሱን እንዲያወጣ እና በፊቱ የሚያስቁ እንቅስቃሴዎች እንዲያደርግ ጠይቆታል።

ታዲያ ይህ ሙከራ በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ቀላል አልነበረም። ሙቀቱን ተቋቁሞ መቆየት እስኪችል ድረስ መቆየቱን የተናገረው ታይንተን፤ ቢርድ እየሮጠ መጥቶ እጆቹን ወደ ላይ በመዘርጋት ደስታውን እንዳበሰረው ገልጿል።

"አይቼሃለሁ ዊሊያም፤ አይቼሃለሁ። በመጨረሻም ቴሌቪዥን፤ የመጀመሪያው እውነተኛ የቴሌቪዥን ምሥል አግኝቻለሁ" እንዳለው ተናግሯል።

ታይንተን "ቴሌቪዥን" ስለተባለው ነገር ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ስለዚህ ቢርድ ቦታ እንዲቀያየሩ ሀሳብ አቀረበ። በትንሽ ቱቦ መሳይ አጮልቆ 5 ሴንቲ ሜትር በ8 ሴንቲ ሜትር የሚሆነ አነስተኛ ምሥል መመልከቱን ተናግሯል።

ዊሊያም ታይንተን ከቴሌቪዥን ፈጣሪው ቢርድ ባለቤት ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እ.አ.አ ጥቅምት 1925 ስኮትላንዳዊው ጆን ሎጊ ቢርድ የሰው ምሥል ለመጀመሪያ ጊዜ አሠራጭቷል

"በድንገት የቢርድ ፊት በስክሪኑ ላይ ተከሰተ። ዓይኖቹ ሲከደኑ፣ አፉ እና ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎችን ማየት ትችላለህ። ጥሩ ጥራትአልነበረውም። ጥላውን ብቻ እና መስመሮችን ነው የምታየው። ነገር ግን እየተንቀሳቀሰ ነበር። ይህን ነው ቢርድ በዋናነት ያሳከው። እውነተኛ የቴሌቪዥን ምሥልን አሳካ።"

በዚህ የፈንጠዚያ ስሜት ውስጥ ሆኖ ነበር ቢርድ ታይንተንን ስለ ፈጠራው ምን እንደሚያስብ የጠየቀው። "በቀጥታ ያን ያህል አላስብም። ፊትህን ማየት እችላለሁ ግን ምንም ጥራት የለውም" ብሎ እንደመለሰለት ተናግሯል።

"'ይህ ገና ጅማሮው ነው፤ ይህ የመጀመሪያው ቴሌቪዥን ነው፤ እናም በመላው አገሪቱ በሁሉም ቤት ወደፊት ታገኘዋለህ። ኧረ እንዴውም በመላው ዓለም ታገኘዋለህ' አለኝ።"

በዓመቱ ቢርድ ለመላው ዓለም የመጀመሪያውን የቴሌቪዥን ሙከራ ለሕዝብ አቅርቧል። ምንም እንኳ ፈር ቀዳጅ የሆነው ማሽኑ በስተመጨረሻ የተሻለ አቅም ባላቸው የቴክኖሎጂ አልሚዎች ቢወሰድም፤ ቀጥሎ ለመጣው ነገር ሁሉ ቢርድ መንገድ ጠርጓል።

ቢርድ ምስል ለማየት መቀበያወን ሲመለከት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቢርድ የመጀመሪያውን የቴሌቪዥን ሙከራ ለሕዝብ አቅርቧል