ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአምስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ እንዲወጡ የሚያደርገውን ውሳኔ ፍርድ ቤት በጊዜያዊነት አገደው
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፤ የጥገኝነት መብት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ እንዳይባረሩ ያደረገውን ሕጋዊ ከካለ ለማቋረጥ ያስተላለፈውን ውሳኔ ፍርድ ቤት በጊዜያዊነት አገደው። ይህ የፍርድ ቤቱ ብይን አሜሪካን ለቅቀው ለመውጣት ሁለት ሳምንት ብቻ የቀራቸውን ከአምስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝም ነው።
በአሜሪካ ቦስተን ከተማ የሚገኙት የፌደራል ዳኛው ብራያን መርፊ ይህንን ብይን የሰጡት ትናንት አርብ ጥር 22/2018 ዓ.ም. እንደሆነ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ዲስትሪክ ዳኛው ይህንን ጉዳይ የተመለከቱት ሦስት ኢትዮጵያውያን 'አፍሪካ ኮሚዩኒቲስ ቱጌዘር' ከተባለ የአፍሪካውያን ስደተኞች መብት ተሟጋች ቡድን ጋር በመሆን ባለፈው ሳምንት ክስ መክፈታቸውን ተከትሎ ነው።
ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅነት መሥሪያ ቤት የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሲሰጥ የነበረውን ጊዜያዊ የሕግ ከለላ ለማቋረጥ ታኅሣሥ መጀመሪያ ያስተላለፈውን ውሳኔ የሚቃወም ነው።
እንዲቋረጥ የተወሰነው ከለላ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን በ2015 ዓ.ም. ተግባራዊ የሆነ ነበር። የባይደን አስተዳደር፤ የጥገኝነት መብት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ እንዳይባረሩ እንዲሁም የመሥራት ፈቃድ እንዲያገኙ የሚያደርገውን ይህንን ከለላ የዘረጋው በዋነኛነት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ነበር።
በመጀመሪያ ይህ ሕጋዊ ከለላ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ እንዲቆይ ተወስኖ የነበረ ሲሆን፤ ጊዜው ሲጠናቀቅ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የደኅንነት ስጋት አለመቀረፉ ተገልጾ ለተጨማሪ 18 ወራት ተራዝሟል።
ሁለተኛው የቆይታ ጊዜ ባለፈው ታኅሣሥ መጀመሪያ መጠናቀቁን ተከትሎ ግን በስደተኞች ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ ያለው የትራምፕ አስተዳደር ከለላውን ላለማራዘም ወስኗል። በዚህ አሠራር አማካኝነት ከለላ ያገኙ አምስት ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያንም በ60 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ሰጥቷል።
ይህንን እርምጃ በመቃወም በፍርድ ቤት ክስ የመሰረቱት ኢትዮጵያውያን እና የመብት ተሟጋች ቡድን፤ የትራምፕ አስተዳደር "በአገሪቱ የትጥቅ ግጭቶች እየቀጠሉ ባለበት ሁኔታ በ60 ቀናት ማስጠንቀቂያ ብቻ" ከለላውን ማቋረጡ ሕገ-ወጥ ነው" ሲሉ ተከራክረዋል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሯ ክሪስቲ ኖም ይህን እርምጃ የወሰዱት "ነጭ ባልሆኑ ስደተኞች ላይ ባላቸው ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ጥላቻ ላይ በመመስረት ነው" ሲሉም ባቀረቡት ክስ መወንጀላቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።
ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ብራያን መርፊ፤ የሕግ ክርክሩ የሚሰማበት ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት ሲሉ ኢትዮጵያውያኑ ለቅቀው እንዲወጡ የተቀመጠው ቀነ ገደብ እንዲታገድ የሚያደርግ ትዕዛዝ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
በዚህ ጊዜ ውስጥ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ እንዴት እዚህ ውሳኔ ላይ እንደደረሰ የሚያስረዱ ዝርዝር መዝገቦችን እንደሚያቀርብም አስረድተዋል።
ዘገባው እንደሚያመለክተው፤ ዳኛው እነዚህ ሰነዶች ላይ ተመስርተው የመሥሪያ ቤቱን እርምጃ ለተጨማሪ ጊዜ ለማገድ ውሳኔ ያሳልፉ እንደሆን ያጤናሉ።
የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት በስደተኞች መብት ተሟጋቹ ቡድን ለቀረበው ክስ ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆ እንደነበር ተገልጿል።
ይህም ቢሆን ግን በኢትዮጵያውያኑ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ለጊዜውም ቢሆን እንዲዘገይ በዳኛው መበየኑን ተቃውሟል።
ዳኛ መርፊ የመሥሪያ ቤቱ መዝገቦች ከቀረቡላቸው በኋላ ከሁለቱ ወገኖች የሚቀርቡ ተጨማሪ ክርክሮችን እንደሚያዳምጡ ተናግረዋል። የአሜሪካ መንግሥትን የወከሉት ዐቃቤ ሕግ በበኩላቸው ሰነዶቹ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ዳኛው፤ "ይህ ጉዳይ እንዲቀጥል ማድረግ የምችለውን ሁሉ ማከናወን እፈልጋለሁ" ብለዋል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ትሪሻ ማክላውሊን በበኩላቸው፤ የሕግ ከለላው "እንደ ምሕረት ፕሮግራም እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ አልነበረም፣ ነገር ግን ያለፉት አስተዳደሮች ለብዙ አሥርት ዓመታት የተጠቀሙበት በዚህ ዓይነት መንገድ ነው" ብለዋል።