ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
100 ሺህ ያህል ቅርሳ ቅርሶችን ይዟል የተባለው ታላቁ የግብፅ ሙዚየም ለዕይታ ክፍት ሆነ
ግብፅ ከጥንታዊው ዓለም ሰባቱ አስደናቂ ነገሮች አንዱ የሆነውን ታላቁ የኩፉ ፒራሚድ በጊዛ የያዘውን እና የዘመናዊው ዓለም ባህላዊ ድምቀት እንዲሆን ታስቦ የተሰራውን ሙዚየም በይፋ ከፈተች።
ግብፃዊያን የዓለማችን ትልቁ የአርኪዮሎጂ ሙዚየም (ጂኢኤም)፣ በማለት የሚጠሩት ይህ ሙዚየም የአገሪቱን ሰባት ሺህ ዓመታት ታሪክ ከቅድመ ሥርወ-መንግሥት እስከ ግሪክ እና ሮማውያን ዘመን ድረስ የሚሸፍኑ 100 ሺህ የሚያህሉ ቅርሶች ይዟል።
ታዋቂ የግብፅ ተመራማሪዎች የሙዚየሙ መከፈት በሌሎች አገሮች የሚገኙ የአገሪቱ ቁልፍ ቅርሶች እንዲመለሱ ያላቸውን ፍላጎት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
የግብፅ ውድ ታሪካዊ ቅርሶች ከሚገኙባቸው አገራት መካከል አንዷ ብሪታኒያ ስትሆን በብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ ለሕዝብ ዕይታ የቀረበው ዝነኛው የሮዜታ ድንጋይ እንዲመለሱላቸው ከሚጠይቋቸው መካከል ይገኝበታል።
በብሪታኒያዊው የግብፅ ተመራማሪ ሃዋርድ ካርተር ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ በይፋ ለዕይታ ያልቀረበው እና ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታየው የንጉስ ቱታንክሃሙን ያልተነካ መቃብር የታላቁ ሙዚየም ዋና መስህብ ይሆናል።
የቱታንክሃሙንን አስደናቂ የወርቅ ጭንብል፣ ዙፋን እና ሰረገሎችን ለዕይታ ከቀረቡት መካከል ናቸው።
የዓለም አቀፉ የግብፅ ተመራማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የታላቀ ሙዚየም ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ታሬክ ታውፊክ "እኔ የማስበው የነበረው እንዴት በተለየ መንገድ እናሳየው የሚለውን ነበር። ምክንያቱም መቃብሩ ከተገኘበት እአአ ከ1922 ጀምሮ፣ በመቃብሩ ውስጥ ከነበሩት ከ5,500 በላይ የሚሆኑ ቅርሶች በአጠቃላይ 1,800 የሚጠጉት ለዕይታ ቀርበዋል።
"ሙሉውን መቃብር የማሳየት ሀሳብ ነበረኝ፤ ይህ ማለት ምንም ነገር በመጋዘን ውስጥ አይቀርም ማለት ነው። በሌሎች ሙዚየሞች ውስጥ ምንም ነገር አይቀርም። እናም ጎብኚዎች ሃዋርድ ካርተር ከመቶ ዓመት በፊት ሲያገኘው በነበረው መንገድ የተሟላውን መቃብር ያገኛሉ።"
1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደፈጀ የተነገረው ይህ ግዙፍ ሙዚየም በዓመት እስከ 8 ሚሊዮን ጎብኝዎችን ይስባል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህም በቀጠናው ባለው ቀውስ ክፉኛ የተጎዳውን የግብፅን ቱሪዝም እንዲያንሰራራ ያደርጋል።
በጊዛ መልክዓ ምድሮች ላይ የሚገኙ ፒራሚዶች የሚያስጎበኙት እና የግብፅ ተመራማሪ የሆኑት አህመድ ሴዲክ "የታላቁ የግብፅ ሙዚየም አዲስ ወርቃማ የግብፅ ጥናት እና የባህል ቱሪዝም ዘመንን እንደሚያመጣ ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
ከቱታንክሃምን አውደ ርዕይ እና ለመጀመርያ ጊዜ ለዕይታ ከበቃው እንዲሁም ጥንታዊ እና ተገቢው ጥበቃ ከተደረገለት 4500 ዕድሜ ካለው አስከሬን ማጓጓዣ ጀልባ በስተቀር አብዛኛዎቹ በቦታው ላይ ያሉት ቅርሶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆነዋል።
"ሙዚየሙ ምንም እንኳን በከፊል ብቻ ክፍት የሆነ ቢሆንም ብዙ ጉብኝዎችን እያመጣሁ ነበር" ሲል አህመድ ይናገራል። "አሁን በክብሩ ማማ ላይ ይገኛል። የቱታንክሃሙን ስብስብ ሲከፈት፣ ከዚያ በኋላ መላው ዓለም ተመልሶ ለማየት እንደሚመጣ መገመት ትችላላችሁ። ምክንያቱም ይህ በጥንት ዘመን ከነበሩት ሁሉ በጣም ታዋቂው የፈርዖን ንጉሥ ቅርስ ነው።"
"የግድ መታየት ያለበት ነው" ይላል ከስፔን የመጣው ቱሪስት ራውል፣ ሰኞ ዕለት ጥቅምት 24 2018 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ለሕዝብ ክፍት እስኪሆን ድረስ እየጠበቀ።
በግብፅ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የለንደኑ ሳም በበኩሉ "ሄደን የግብፅን ቅርሶች በሙሉ ለማየት እየጠበቅን ነው" ብሏል። "በሕይወት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ዕድል ነው።"
ሌላዋ ብሪታኒያዊት ቱሪስት ከዚህ ቀደም በተጨናነቀው ታህሪር አደባባይ በሚገኘው ኒዮክላሲካል የግብፅ ሙዚየም የቱታንክሃሙን አውደ ርዕይ ተመልክታለች።
"የቀድሞው ሙዚየም በጣም የተጨናነቀ ነበር፤ እና ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነበር" ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
"ታላቁ ሙዚየም ለመጎብኘት በጣም ቀላል እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፤ እና ከሙዚየሙ የበለጠ ዕይታ አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ።"
አዲሱ ግዙፍ ሙዚየም 500,000 ካሬ ሜትር (5.4 ሜትር ስኩዌር ጫማ) የሚሸፍን ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ወደ 70 የእግር ኳስ ሜዳዎችን ያህላል።
ውጫዊው የሙዚየሙ ክፍል በሂሮግላፊስ እንዲሁም ወደ በሚያብረቀርቁ እና በሦስት ማዕዘን በተቆረጡ የእብነበረድ ድንጋይ ያጌጠ ሲሆን መግቢየው ደግሞ የፒራሚድ ቅርፍ አለው
በሙዚየሙ ለዕይታ ከበቁት ዓይን የሚይዙ ቅርሶች መካከል የ3,200 ዓመት እድሜ ያለው፣ 16 ሜትር የሚረዝመው የኃያሉ ፈርኦን ራምሴስ ሁለተኛ እና ግዙፉ 11 ሜትር ከፍታ ያለው ሃውልቱ ነው።
ግዙፉ ሀውልት እአአ በ2006 ከካይሮ የባቡር ጣቢያ አቅራቢያ ለአዲሱ ተቋም በሚል ወደዚህ ስፍራ ተንቀሳቅሷል።
በእነዚህ ጥንታዊ ንጉሦች እና ንግሥቶች ሃውልት አቅራቢያ አንድ ግዙፍ ደረጃ ያለ ሲሆን በላይኛው ፎቅ ላይ አንድ ትልቅ መስኮት የጊዛ ፒራሚዶችን በጉልህ እንዲታዩ ያግዛል።
ሙዚየሙ በፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ የሥልጣን ዘመን እአአ በ1992 ለመገንባት ታስቦ የነበረ ቢሆንም እአአ በ2005 ግንባታው ተጀምሯል።
ፕሮጀክቱ እአአ በ2011 ሙባረክን ከሥልጣን ባስወገደው የግብፅ የአረብ አብዮት፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በቀጠናዊ ጦርነቶች ወቅት በገንዘብ ቀውስ ተፈትኗል።
የግብፅ የረጅም ጊዜ የቱሪዝም እና የቅርስ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ዛሂ ሀዋስ "ሕልሜ ነበር። ይህ ሙዚየም በመጨረሻ ሲከፈት በማየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ!" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንጋፋው ግብጻውያን አርኪኦሎጂስት በቁፋሮ፣ በቅርሶች ጥበቃ እና በሙዚየሞች አያያዝ ረገድ በውጪ ከሚገኙ የግብፅ ታሪክ ተመራማሪዎች ጋር እኩል መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል።
አሁን ሁለት ነገሮችን እፈልጋለሁ። ቁጥር አንድ ሙዚየሞች የተሰረቁ ቅርሶችን መግዛት እንዲያቆሙ እና ቁጥር ሁለት፣ ሦስት ቅርሶች እንዲመለሱ እፈልጋለሁ። ከብሪቲሽ ሙዚየም የሮሴታ ድንጋይ፣ ከፈረንሳይ ሉቨር ሙዚየም ዞዲያክ እና ነፈርቲቲ ከበርሊን።"
ዶ/ር ሀዋስ በኦንላየን ሦስቱ ቅርሶቹ አንዲመለሱ የሚጠይቅ ፊርማዎቸን እያሰባሰቡ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳትፏል።