ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሐማስ ቃል አቀባይ አቡ ኦቤይዳ በጋዛ መገደሉን የእስራኤል ጦር አስታወቀ
የሐማስ ቃል አቀባይ አቡ ኦቤይዳ በጋዛ በአየር ጥቃት መገደሉን የእስራኤል ጦር አስታወቀ።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ለዚህ ግድያ የእስራኤል መከላከያ ኃይልን እንዲሁም የእስራኤል የደህንነት ኤጀንሲ፣ ሺን ቤትን አመስግነዋል።
ሚኒስትሩ "እንከን የለሽ አፈጻጸም" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ሐማስ የቃል አቀባዩን ግድያ እስካሁን አላረጋገጠም።
እሰራኤል በጋዛ ሰርጥ በመኖሪያ ህንጻ ላይ ባደረሰችው ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ቀደም ሲል ሐማስ አስታውቆ ነበር።
በጋዛ ከተማ ህዝብ በሚጨናነቅባት አል ሪማል ሰፈር ላይ የእሰራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 20 መቁሰላቸውን የአካባቢው ጋዜጠኞች ዘግበዋል።
በዚህ ጥቃት ከተገደሉትም ህጻናት ይገኙበታል።
የቅዳሜው ጥቃት የተፈጸመው እስራኤል በጋዛ ከተማ ሙሉ ወረራ የመፈጸም እቅዷን ተግባራዊ ከማድረጓ በፊት ነው።
ካትዝ በርካታ ተጨማሪ የኦቤይዳ "ወንጀለኛ አጋሮች" በቀጣዩ "ተጠናክሮ በሚቀጥለው የጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ" ኢላማ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።
ካትዝ የገለጹት "ዘመቻ" እስራኤል የጋዛ ከተማን በሙሉ ለመውረር በቅርቡ በካቢኔዋ የጸደቀውን ዕቅድ ነው ።
የእስራኤል መከላከያ እና ሺን ቤት የሐማስ ቃል አቀባይን ስለገደለው ጥቃት ዘርዘር ያሉ መረጃዎችን ባወጡት መግለጫ ሰጥተዋል።
ግድያው ሊሳካ የቻለው ቃል አቀባዩ የተደበቀበትን ቦታ ለመለየት በሺን ቤት እና በመከላከያ ሰራዊቱ በተሰበሰበ መረጃ እንደሆነ በጋራ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።
ኦቤይዳ በህይወት ከቀሩት የሐማሰ ወታደራዊ ክንፍ ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ነበር።
በአል ሪማል ሰፈር ህንጻ የሚገኘውን ባለ ስድስት ፎቅ አፓርታማ አምስት ሚሳኤሎች ከሁለት አቅጣጫ መምታታቸው ተነግሯል።
የህንጻው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ፎቅ ኢላማ መደረጉ ተገልጿል።
ህንጻው የጥርስ ቀዶ ሃኪም አገልግሎት መስጫነት ያገለግላል ተብሏል።
የተቋማቱ የጋራ መግለጫ ኦቤይዳ "የሐማስ አሸባሪ ድርጅት የህዝብ ፊት ሆኖ አገልግሏል" እንዲሁም "የሐማስን ፕሮፖጋንዳ ያሰራጭ ነበር" ብሏል።
ወደ 40 ዓመት ገደማ የሚጠጋው ኦቤይዳ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ በሆነው አልቃሳም ብርጌድ ስም ረዘም ያሉ ውግዘቶችን ያዘሉ ጽሁፎችን በእስራኤል ላይ አሰምቷል።
ፊቱን በፍልስጤም ካፊያ፣ ሻርፕ የሚሸፍነው ኦቤይዳ ለሐማስ ደጋፊዎች በሙሉ ተምሳሌት ነበር። ኦቤይዳ አርብ ዕለት ባደረገው ንግግር የቀሩት የእስራኤል ታጋቾች እጣ ፈንታ ከሐማስ ተዋጊዎች ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን በመግለጽ እስራኤል በጋዛ ላይ ልትፈጽመው ያሰበችውን ወረራ አስጠንቅቋል።
ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት እና ከጋዛ አስተዳዳሪነቱ ማስወገድን ጨምሮ አምስት መርሆዎችን ይዟል የተባለው ጦርነቱን የመቋጨት እንዲሁም የጋዛ ከተማ ወረራ ዕቅድ የጸደቀው በቅርብ ነው።
አምስቱ ተብለው የተዘረዘሩት ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት፣ ሁሉንም ታጋቾች መመለስ (በሕይወት ያሉ እንዲሁም የሞቱትን አስከሬኖቻቸውን)፣ የጋዛ ሰርጥን ከወታደራዊ ትጥቅ ነጻ ማድረግ፣ ጋዛን የሚያስተዳድረውን ሐማስን በማስወገድ እንዲሁም ዌስት ባንክን ከሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር ውጪ የሆነ አማራጭ የሲቪል መንግሥት ምሥረታን ያካተተ ነው።
እቅዱ መጀመሪያ ላይ የጋዛ ከተማን ሙሉ ወረራ በመፈጸም አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያንን ወደ ደቡባዊ ግዛቶች ማፈናቀል ላይ ያተኮረ መሆኑን የእስራኤል ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው አስፍረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኙ የስደተኛ ካምፖችን እንዲሁም ታጋቾች አሉባቸው የሚባሉ ስፍራዎችን ይወራሉ ተብሏል።
ከሳምንታት በኋላ ሁለተኛ ዙር ጥቃቷን እስራኤል እንደምትጀምር የተገለጸ ሲሆን፤ የሰብዓዊ እርዳታዎች እንደሚገቡ ሚዲያዎቹ ዘግበዋል።
የእስራኤል የጋዛ ወረራ እቅድ ማጽደቋ በአገሪቱ ከሚገኙ አንዳንድ ወታደራዊ ባለስልጣናትን ጨምሮ በጋዛ ቤተሰቦቻቸው ከታገቱ አካላት ተቃውሞ ገጥሞታል።
ሐማስ የጋዛ ከተማን ወረራ እቅድ "አዲስ የጦር ወንጀል" ሲል ያወገዘው ሲሆን "ይህም [እስራኤልን] ዋጋ የሚያስከፍል ነው ብሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የኒውዚላንድ እና የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች "እቅዱን ውድቅ" የሚያደርግ የጋራ መግለጫ አርብ ዕለት አውጥተዋል።
እስራኤል አብዛኛውን የጋዛ ሰርጥን ተቆጣጥራ የምትገኝ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት 87 በመቶ የሚሆነው የጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ ቀጣና ወይም ጋዛውያን በአስገዳጅ የሚፈናቀሉባቸው ቦታዎች እንደሆኑ አስታውቋል።
ለጥቂት ጊዜ የቆየው የተኩስ አቁም መጋቢት ወር ላይ መፍረሱን ተከትሎ እስራኤል ሁሉንም የድንበር አካባቢዎች "አደገኛ የውጊያ ቀጣና" በሚል ፈርጃ በቀጣዮቹ ወራት እነዚህ ቀጣናዎች እየሰፉ መጥተዋል።
በዚህ አውዳሚ ጦርነት ከ2.1 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ሕዝብ መካከል 90 በመቶ ወይም 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል።
አንዳንዶች በተደጋጋሚ የተናፈናቀሉ ሲሆን በርካታዎቹ በተጨናነቀ እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት።
የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ በደቡባዊ ክፍል በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት ዕቅድ እንዲያዘጋጅ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ትዕዛዝ መስጠታቸውን ከዚህ ቀደም ተዘግቦ ነበር።
በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ ይቋቋማል የተባለው ይህ ካምፕ በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ሕዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሆነ ተገልጾ ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል።