እስራኤል በሆስፒታል ላይ በፈጸመችው ጥቃቶች አምስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ሰዎች ተገደሉ

እስራኤል በኻን ዩኒስ ከተማ ናስር ሆስፒታል በተከታታይ ሁለት ጊዜ በፈጸመችው ጥቃት ለአለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚሰሩ አምስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ፍልስጤማውን መገደላቸውን በሐማስ ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ጋዜጠኞቹ ለሮይተርስ፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ፣ አልጀዚራ እና ዘ ሚድል ኢስት አይ ጋር ይሰሩ እንደነበር ሚዲያዎቹ አረጋግጠዋል።

በዚህ ጥቃት አራት የጤና ባለሙያዎች መገደላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን እያገዙ የነበሩ ሰዎች በድጋሚ በተፈጸመ ጥቃት መመታቸውን ከአካባቢው የወጡ ቪዲዮዎች ያሳያሉ።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በሆሰፒታሉ ላይ የተፈጸመውን ጣምራ ጥቃት "አሳዛኝ ጥፋት" ሲሉ የገለጹት ሲሆን ወታደራዊ ባለስልጣናት "ምርመራ እያከናወኑ ነው" ብለዋል።

እስራኤል በጋዛ ላይ የተቀናጀ ጥቃት ከጀመረች መስከረም 26/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተገደሉ ጋዜጠኞች 200 ገደማ አድርሷቸዋል።

የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ ቢያንስ 178 ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች በእስራኤል መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

እንደ ሲፒጄ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ለጋዜጠኞች የከፋ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመት የተገደሉ ጋዜጠኞች እስካሁን በዓለማችን በጦርነት ከተገደሉት በድምሩ በከፍተኛ የላቀ ነው ብሏል።

የአሁኑ ዙር ጦርነት ከተጀመረ ጀምሮ አለም አቀፍ ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ ሰርጥ ገብተው እንዳይዘግቡ እስራኤል እገዳ ጥላለች።

ሰኞ ዕለት የተፈጸመውን ጥቃት የሚያሳይ አንድ ቪዲዮ አንድ ዶክተር በሆስፒታሉ መግቢያ ላይ ቆሞ በደም የተጨማለቀ ልብስ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ለጋዜጠኞች ያሳያል።

ወዲያውኑ ድንገተኛ ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን በርካቶችም ህይወታቸውን ለመታደግ ሲሮጡ ይታያል። በፍንዳታው የተጎዳ ሰው ሽፋን ለማግኘት መሬት ላይ እየተጎተተ ሲንቀሳቀስ ይታያል።

በአልጋድ ቴሌቪዥን በቀጥታ የተላለፈው ቀረጻ ደግሞ የመጀመሪያውን ጥቃት ተከትሎ በርካታ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ናስር ሆስፒታል ላይኛው ፎቅ አካባቢ እርዳታ ሲያደርጉ ይታያሉ።

በርካታ ጋዜጠኞችም በዚህ ስፍራ ላይ ነበሩ።

ሁለተኛው ጥቃት በቀጥታ የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞችን እና ጋዜጠኞችን ሲመታም ይሄው ቀረጻ ያሳያል። የሮይተርስ የካሜራ ባለሙያ ሁሳም አል ማስሪ ከተገደሉት መከካከል አንዱ መሆኑን የዜና ተቋሙ ተናግሯል።

ጋዜጠኛው በተገደለበት ወቅት ጣሪያ ላይ ሆኖ የቀጥታ ፕሮግራም ሲያስተላልፍ ነበር ።

የተፈጸመበትን ጥቃት ተከትሎ የቀጥታ ቀረጻው ተቋርጧል።

ሌላኛው የሮይተርስ የፎቶ ባለሙጣ ሃተም ካሌድ በሁለተኛው ጥቃት ጉዳት እንደደረሰበት የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በጣም ማዘኑን እና "በአስቸኳይ ተጨማሪ መረጃ እፈልጋለሁ" ብሏል።

ኤፒ በበኩሉ ማሪያም ዳጋ የተባለች ፍሪላንስ ጋዜጠኛው መገደሉን አስታውቋል።

የዜና ወኪሉ የ33 ዓመት ጋዜጠኛው ግድያ "እንዳስደነገጠው እና እንዳሳዘነው" ገልጿል።

ሌሎቹ የተገደሉት የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ሞሀመድ ሳላማ፣ የሚድል ኢስት ፍሪላንሰር አህመድ አቡ አዚዝ እና የፎቶ ባለሙያው ሞአዝ አቡ ታሃ ይገኙበታል።