ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሃርቫርድ ሬሳ ክፍል አስተዳዳሪ የሰውነት ክፍሎችን ቆርጦ በመሸጥ ተከሰሰ
የሃርቫርድ የሕክምና ክፍል የሬሳ ክፍል አስተዳዳሪና ሌሎች ሶስት ሰዎች የሰውነት ክፍል በመሸጥና በመግዛት ተከሰዋል።
ሴድሪክ ሎጅ “ጭንቅላት፣ አንጎል፣ ቆዳ እና አጥንት” ከሬሳ ክፍል አውጥቶ በይነ መረብ ላይ ቸብችቧል ተብሎ ተከሷል።
ሬሳዎቹ ለሃርቫርድ የሕክምና ክፍል ለምርምር እንዲረዱ በእርዳታ መልክ የሚሰጡ ናቸው።
የክሱ መዝገቡ እንደሚያሳየው ሰውየውና ሚስቱ ዴኒስ ማሳቹሴትስ እና ፔንሲልቫኒያ ላሉ ደንበኞች የሰውነት ክፍሎችን ሸጠዋል።
ይህ የሆነው በፈረንጆቹ ከ2018 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ነው።
አቃቤ ሕግ እንደሚለው ሎጅ በእርዳታ የሚሰጡ ሬሳዎች ክፍል አስተዳዳሪነቱን ለግል ጥቅሙ በማዋል ለምርምር የተለገሱ ሬሳዎችን ቆራርጦ ሸጧል።
የሃርቫርድ ተማሪዎች የጤና ትምህርትና ምርምር የሚያካሂዱት በልገሳ በተሰጡ ሬሳዎች ላይ ነው።
አብዛኛውን ጊዜ ምርምራቸውን ሲያጠናቅቁ ሬሳዎቹ እንዲቃጠሉ ሆኖ አመዳቸው ለቤተሰብ ይላካል።
አሊያም ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጤና ምርምር መቃብር ስፍራ አፅማቸው እንዲኖር ይደረጋል።
ሎጅ እና ሚስቴ ከእነዚህ ሬሳዎች ላይ የሰውነት ክፍሎችን በመውሰድ፣ በመሸጥና ለገዢዎች በማድረስ ተከሰዋል።
የአሜሪካ አቃቤ ሕግ ቢሮ የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው ተከሳሹ “አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ወደ ሬሳ ክፍሉ በማስገባት የሰውነት ክፍል እንዲመርጡ ያደርጋል።”
የሰውነት ክፍል ገዝተዋል ተብለው የተጠረጠሩት ካትሪና ማክሊን እና ጆሹዋ ቴይለርም ክስ ቀርቦባቸዋል።
የክስ ሰነዱ እንደሚገልጠው በ2020 ካትሪና ማክሊን የሰው ፊት በ600 ዶላር ገዝታለች።
ካትስ ክሪፒ ክሬሽንስ የተሰኘ ሱቅ ያላት ካትሪና የማሕበራዊ ሚድያ ገፆቿ እንደሚያሳዩት የሕፃናት መጫወቻ አሻንጉሊቶችን ቀለም በመቀባት ወደ አስፈሪ ገፅታ መቀየር ያስደስታታል።
የገዛችውን የሰውነት ከፍል ለዚህ ዓለማ አውላው ይሆን ወይም የሚለው እስካሁን ግልጥ አይደለም።
ነገር ግን የክስ መዝገቡ እንደሚለው በሱቋ ውስጥ የሰውነት ክፍል አስቀምጣለች እንዲሁም ሸጣለች።
ጆሹዋ ቴይለር ደግሞ በአራት ዓመታት ውስጥ 39 ጊዜ ለሎጅ ክፍያ የፈፀመ ሲሆን ይህ ክፍያ ለተሰረቁ የሰውነት ክፍሎች ነው።
ይህ ክፍያ ሲሳላ 37 ሺህ ዶላር ሲሆን በአንድ ወቅት አንድ ሺህ ዶላር የከፈለበት ክፍያ ላይ “ጭንቅላት ቁጥር 7” የሚል ማስታወሻ ተያይዟል።
ባልና ሚስት በሃምፕሻየር ፌዴራል ፍርድ ቤት ቀርበው ሲወጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አልሻቱም።
አራቱ ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 15 ዓመት እሥር ይጠብቃቸዋል።