አማዞን ጫካ ውስጥ የጠፉትን ሕፃናት ‘ከሁሉ ቀድሞ አግኝቷል’ የተባለው ውሻ እየተፈለገ ነው

“ፍለጋው አላለቀም” የኮሎምቢያ ጦር እሑድ ዕለት የለጠፈው መልዕክት።

ምንም እንኳ ደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ለ40 ቀናት ጥቅጥቁ የአማዞን ጫካ ውስጥ የጠፉትን ሕፃናት ፈልጋ በማግኘቷ ብትደሰትም ደስታዋ ሙሉ አልሆነም።

የአገሪቱ ጦር ኃይል የአደጋ ጊዜ የነፍስ አድን ቡድን ውስጥ የሚገኘው “ዊልሰን” የተባለው ውሻ ሕፃናት ሊያስስ እንደወጣ በመቅረቱ እሱን በማፈላለግ ላይ ነው።

የስድስት ዓመቱ ቤልጂያን ሼፐርድ የተሰኘ ዝርያ ያለው ውሻ ሕፃናቱ እንዲገኙ ብዙ አስተዋፅዖ አድርጓል።

ውሻው አነፍንፎ በደረሰባቸው ማስረጃዎች ነው የአደጋ ጊዜ ነፍስ አድን ሠራተኞች ሕፃናቱ በሕይወቱ እንዳሉ ማወቅ የቻሉት ይላል የኮሎምቢያ ጦር ኃይል።

ጦር ኃይሉ እንደሚጠረጥረው ውሻው ከሁሉም ቀድሞ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሕፃናቱን ሳያገኛቸው አይቀርም።

ጦሩ ይህን ያለው “የሕፃናቱ ኮቴ” የተገኘበት አካባቢ “የውሻ መሰል ኮቴ” ታይቷል።

አሁን ግን ዊልሰን በተራው ላይ ጠፍቷል። ጥቅጥቁ እና አስፈሪው የአማዞን ጫካ ውጦታል። የዱር እንስሳት ሲሳይ እንዳይሆንም ተሰግቷል።

ጦር ኃይሉ እንደሚለው “ማንም ቢሆን በወጣበት መቅረት የለበትም” እናም ወታደሮች ውሻውን ፍለጋ ተሰማርተዋል።

ባለሮዝ ቀለሙ ጡጦ

አውሮፕላናቸው ተከስክሶ እነሱ በሚገርም ተዓምር ተርፈው በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉ ሲባል እንደ ዊልሰን እምር ብሎ ለፍለጋ የተነሳ የለም።

ነገር ግን ዊልሰን አራቱን ሕፃናት፤ ሌዝሊ፣ ሶሌኒ፣ ቲየን እና ክሪስቲንን እየፈለገ ሳለ ደብዛው ጠፋ።

ለኮሎምቢያ ጦር እና ለአካባቢው ነዋሪዎች ምስጋና ይግባና፣ ከ40 ቀናት መጥፋት በኋላ ሕፃናቱ ባለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም. ተገኝተዋል።

አሁን በዋና ከተማዋ ቦጎታ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

ከአራቱ ሕፃናት በቀር እናታቸው፤ የአውሮፕላኑ አብራሪ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ መሪ የሆኑ ሰው በአደጋው ምክንያት ሞተዋል።

ፍለጋው ሲጀመር ውሻው ዊልሰን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እርዳታ በፍለጋው ላይ ተሰማርቶ ነበር። ብዙዎች ሕፃናቱ በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉ ሲሉ የገመቱት የእሱን አፍንጫ ተማምነው ነው።

ውሻው፤ ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ በጫካው መሃል እየተሯሯጠ አንድ ሮዝ ቀለም ያለው ጡጦ ሲያገኝ የአደጋ ጊዜ ሰዎች በተስፋ ተሞሉ።

የኮሎምቢያ ጦር ውሻው መጥፋቱን ይፋ ያደረገው ባለፈው ሐሙስ ነው።

“ጫካው ተራራ እና ሸለቆ የሞላው፤ ከባድ የአየር ፀባይ ያለበት ስለሆነ ምናልባት በድካም ግራ ተጋብቶ ይሆናል” ብሏል ጦሩ።

ነገር ግን በርካታ ማስረጃዎች እንደሚጠቀሙት ዊልሰን ከሁሉ ቀደም ሕፃናቱን ሳያገኛቸው እንዳልቀረ ነው።

“ባለአራት እግሩ ጓደኛ”

የመጀመሪያ ፍንጭ የመጣው ከእራሳቸው ጠፍተው ከተገኙት ሕፃናት ነው።

አስትሪድ ካሴሬስ የኮሎምቢያ ፋሚሊ ዌልፌር ተቋም ዳይሬክተር ናቸው። ተቋሙ የሕፃናትን መብት የሚጠብቅ ነው።

አስትሪድ እንደሚሉት ሕፃናቱ ጥቅጥቁ ጫካ ውስጥ ሳሉ ውሻ እንዳገኙ ቢናገሩም፣ ዊልሰን መሆኑ ግን ግልጽ አይደለም።

ሕፃናቱ ሲናገሩ “አንድ ውሻ ጫካ ውስጥ አግኝተን ነበር። ቦታውን ባናስታውስም ከእኛ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቆይቷል” ማለታቸውን አስትሪድ ይናገራሉ።

ይህንን ፍንጭ ጨምሮ የጦር ኃይሉ “ከሕፃናቱ ኮቴ አጠገብ የውሻ ሊሆን የሚችል ኮቴ” መገኘቱ ዊልሰን ሕፃናቱን ከሁሉም ቀድሞ ሲያፅናና እንደነበር ማሳያ ነው።

የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሄልደር ፈርናንዶ ጂራልዶ ቦኒላ ሕፃናቱን ለመጎብኘት ወደ ሆስፒታል ባቀኑበት ወቅት አራቱ ልጆች ዊልሰንን የሚመስል ውሻ ያለበት ሥዕል ሰጥተዋቸዋል።

የኮሎምቢያ ጦር “ማንም እንደወጣ መቅረት የለበትም” የተሰኘውን መመሪያውን ተንተርሶ ዊልሰንን ፈልጎ ለማግኘት ቃል ገብቷል።