ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአውሮፕላን አደጋ ተርፈው በአማዞን ጫካ ለ40 ቀናት የቆዩት ሕጻናት እንዴት በሕይወት ተገኙ?
ባለፈው ሳምንት ሰኔ 02/2015 ዓ.ም. አርብ ሌሊት በኮሎምቢያ ደን ውስጥ በወታደሮች መገናኛ ራድዮ ድንቅ ዜና ተሰማ።
መላውን የኮሎምቢያ ሕዝብ ያስደሰተ ዜና ነበር።
“ተዓምር ተዓምር ተዓምር ተዓምር” ይላል የራድዮ መልዕክቱ።
ለ40 ቀናት በኮሎምቢያ ደን ጠፍተው የነበሩ አራት ሕጻናት መገኘታቸው ነበር ተዓምሩ።
ሕጻናቱ ሁቶቶ የተባለ ቀደምት ማኅበረሰብ አባላት ናቸው።
ከእናታቸው ጋር በአውሮፕላን እየሄዱ ሳለ አውሮፕላኑ አማዞን ጫካ ውስጥ ተከስክሶ እናታቸው፣ አብራሪው እና ረዳት አብራሪው ሞተዋል።
ይህ ከሆነ 40 ቀናት ተቆጥረዋል። ልጆቹ በተዓምር በሕይወት መገኘታቸው ዓለምን እያነጋገረ ነው።
ልጆቹ አስራ ሦስት ፣ ዘጠኝ፣ አራት እና አንድ ዓመት የሆናቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው።
የሚተናኮሉ እንስሳት ባሉበት ጫካ ውስጥ በሕይወት እንዴት ተረፉ? የሚለው አስደናቂ ሆኗል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሕጻናቱን በሕይወት እንደሚያገኙ እርግጠኛ አልነበሩም። ግን የእግር ዱካቸውን ሲያገኙ ተስፋ አደረጉ።
በከፊል የተበላ ፍሬ እና ሌሎችም ቁሳቁሶች ተጥለው ሲያገኙ የበለጠ ተስፋቸው ለመለመ።
ሕጻናቱ ያልተጋፈጡት አደጋ ያለ አይመስልም።
የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ “በታሪክ የሚዘከር የሕልውና ምልክት” ሲሉ ነው ልጆቹን የገለጹት።
‘የጫካ ልጆች’
እንዲህ ያለ መከራን መጋፈጥ የሚችሉ ሕጻናት ካሉ እነሱ እነዚህ ሕጻናት ብቻ ሳይሆኑ አይቀርም።
ቀደምት ማኅበረሰባቸው ከልጅነት ጀምሮ አደን፣ ዓሣ ማስገር፣ ፍራፍሬ መልቀም እና ሌላም ሌላም ያስተምራቸዋል።
ወንድ አያታቸው ፊደንሲዮ ቫሌንስያ እንደሚሉት ሁለቱ ታላላቅ ልጆች ሌዝሊ እና ሶለኒ ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዴት ደን ውስጥ ራስን ማቆየት እንደሚቻል ተምረዋል።
አክስታቸው ዳማሪስ ሙኩቲ እንዳለችው ቤተሰቡ ብዙ ጊዜ ራስን ከአደጋ ማዳን የሚቻልበትን መንገድ በጨዋታ መልክ ያስተምራቸዋል።
“ትንንሽ ካምፖች አዘጋጅተን ነው የምንማረው። የ13 ዓመቷ ሌዝሊ የትኛው ፍሬ መርዛም እንደሆነ ታውቃለች። ስለዚህ ጫካ ውስጥ የትኛውን ፍሬ መመገብ እንዳለባት አይጠፋትም። ልጅ እንዴት መንከባከብ እንደሚቻልም ተምራለች” ትላለች አክስታቸው።
አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ የ13 ዓመቷ ሌዝሊ ከእንጨት ስብርባሪ ጊዜያዊ መጠለያ ሠራች። በፀጉር ማስያዣዋ ነበር እንጨቶቹን ያያየዘችው።
ይጓዙበት ከነበረው ሴስና 206 አውፕላን ፋሪና የተባለ የምግብ ዱቄት ወስዳም ለቀናት ተመገቡ።
ዱቄቱ ሲያልቅ ፍራፍሬ እየተመገቡ እንደቆዩ የቀደምት ማኅበረሰቡ አባል እና ከፍለጋው መሪዎች አንዱ ኤድዊን ፓኪ ገልጿል።
“ፓሽን ፍሬ የሚመስል አቪኩር የተባለ ፍሬ አለ። አደጋው በተከሰተበት ስፍራ አቅራቢያ የዚህን ፍሬ ዛፍ ሲፈልጉ ነበር” ብሏል።
የኮሎምቢያ የቤተሰብ ደኅንነት ኃላፊት አስትሪድ ካሴርስ እንዳለችው፣ ወቅቱ ፍሬ የሚበቅልበት በመሆኑ ልጆቹ የሚመገቡት አግኝተዋል።
የሚበሉት ቢያገኙም የተከበቡት ግን በአደጋ ነበር።
የቀደምት ማኅበረሰብ ባለሙያው አሌክስ ሩፊኖ እንዳለው ልጆቹ “ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ በጨለማ ተከበው” ቆይተዋል።
ጫካው ውስጥ በአካባቢው ግዙፍ የሆኑ ዛፎች ይገኛሉ።
ልጆቹ ውሃ ለማጥራት የሚሆን ቅጠል ቢያገኙም፣ አንዳንዶቹ ቅጠሎች ግን መርዛማ ናቸው።
“አካባቢው ብዙም አልተጠናም። ከወንዝ አቅራቢያ በትንንሽ ከተሞች የተከበበ ነው” ይላል።
የሚተናኮሉ እንስሳትን ማምለጥ ደግሞ ሌላው የታዳጊዎቹ ፈተና ነው።
ጫካ ውስጥ ከፍተኛ ዝናብ አለ። ታጣቂ ቡድኖች የመሸጉበትም ነው።
ልጆቹ ራሳቸውን ከዱር ውሾች መከላከል እንደነበረባቸው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።
በቀደምት ማኅበረሰብ ውስጥ ያደገች የ13 ዓመት ልጅ ራሷን እና ቤተሰቧን መከላከል የምትችልበት ክህሎትን መማሯ የልጆቹ ሕይወት መዳን ምሥጢር ሳይሆን አልቀረም።
ሕጻናቱ ያደጉበት ጉዋናኖ የተባለው ቡድን መሪ ጆን ሞሬኖ እንዳሉት ሕጻናቱን ያሳደጉት በአካባቢው የሚከበሩት የቀደምት ማኅበረሰብ መሪ የሆኑ የሕጻናቱ ሴት አያት ናቸው።
“ማኅበረሰባቸው ያስተማራቸውን ተግብረዋል። ራሳቸውን ለማዳን የቀደምት አያቶቻቸውን ዕውቀት ተጠቅመዋል” ብለዋል።
የልጆቹ ፍለጋ በፍጥነት እየተካሄደ አይደለም የሚል ትችት ሲሰነዘር ነበር። ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ስለ ልጆቹ መገኘት የተሳሳተ የትዊተር መልዕክት መተላለፉም ለትችት ዳርጎታል።
በፍለጋው ወቅት ልጆቹ እንዴት ራሳቸውን ማዳን እንዳለባቸው የሚጠቁሙ 10,000 በራሪ ወረቀቶች ደኑ ውስጥ ተበትነዋል።
ሴት አያታቸው ያስተላለፉት መልዕክት ተቀርጾም በሄሊኮፕተር ድምጹ ሲተላለፍ ነበር።
ፍለጋውን የመሩት ኮማንደር ጄኔራል ፔድሮ ሳንቼዝ እንዳሉት ልጆቹን ለማግኘት ከ20 እስከ 50 ሜትር ርቀት እየደረሱ ነበር።
150 ወታደሮች እና 200 በጎ ፈቃደኞች በፍለጋው ተሳትፈዋል።
“መርፌ የሳር ክምር ውስጥ እንደመፈለግ ዓይነት ነበረ። ልጆቹ እየተንቀሳቀሱ ስለነበር ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር” ብለዋል ኮማንደሩ።
ከአንድ ወር ፍለጋ በኋላ ሰው በመፈለግ የሠለጠኑ ውሾች ልጆቹን አገኟቸው።
የአንድ ዓመት እህቷን አቅፋ የነበረችው ሌዝሊ በተገኙበት ቅጽበት “ርቦኛል” ነበር ያለችው።
አንደኛው ወንድሟ ደግሞ “እናቴ ሞታለች” ነበር ያለው።
እናታቸው አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ ለአራት ቀናት በሕይወት ብትቆይም ከመሞቷ በፊት “ልጆቼ እናንተ ሂዱ” ብላቸው እንደነበር አባታቸው ማኑዌል ራኖክ ተናግሯል።
የኮሎምቢያ መከላከያ መሥሪያ ቤት የለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምሥል ሕጻናቱ ለሕክምና በሄሊኮፕተር ወደ ዋና ከተማዋ ቦጎታ ሲወሰዱ ያሳያል።
“ተስፋ አልቆረጥኩም ነበር። በፍለጋው ስሳተፍ ነበር። አሁን ደስተኛ ነኝ። ፕሬዝዳንቱን እና በፍለጋው የለፉ የአገሬን ልጆች አመሰግናለሁ” ብለዋል ሴት አያታቸው።
ፕሬዝዳንቱ “የወታደሮች እና የበጎ ፈቃደኞች ትጋት ከወታደራዊ እና ማኅበረሰባዊ ዕውቀት ጋር ተደምሯል። ይህ የሰላም ማሳያ ነው” ብለዋል።
ልጆቹ ከአካባቢያቸው ጋር ያላቸው ልዩ ትስስር በሕይወት ለመቆየታቸው ያበረከተውን አስተዋጽኦም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
“የጫካው ልጆች ናቸው። አሁን ደግሞ የኮሎምቢያ ልጆች ናቸው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የቀደምት ማኅበረሰብ ባለሙያው የልጆቹ መገኘት “ተዓምራዊ” የሆነው “ከተፈጥሮ ጋር ባላቸው መንፈሳዊ ቁርኝት” ነው ሲል አስረድቷል።
“ደኑ አረንጓዴ ብቻ አይደለም። ጥንታዊ ኃይል አለው። ከዚህ ጋርም ማኅበረሰባችን ይተሳሰራል። ለመረዳት ሊከብድ ይችላል። ይህንን ዕድል ተጠቅሞ በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ምልከታ መረዳት መልካም ነው” ሲልም አክሏል።
አያይዞም “ከአደጋው በኋላ መንፈሷ ብቻ የቀረው እናታቸው ጠብቃቸዋለች። አሁን ታርፋለች” ብሏል።