በአውስትራሊያ አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል ላይ የደረሰው ጥቃት “የሽብር ድርጊት” ነው ተባለ

የአውስትራሊያ ፖሊስ ሰኞ ምሽት ሲድኒ በሚገኘው ቤተ-ክርስትያን ላይ የደረሰው ጥቃት ኃይማኖታዊ “የሽብር ድርጊት” ነው ብሏል።

በአሲሪያን ዘ ጉድ ሼፐርድ ቤተ-ክርስትያን የሚገኙ አቡን፣ ቄስ እና ምዕመናን ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የ16 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ቢያንስ 4 ሰዎች “ሕወይታቸውን አደጋ ላይ የማይጥል” ጉዳት ደርሶባቸዋል ያለው ፖሊስ ጥቃት ያደረሰውም ግለሰብ መጎዳቱን አሳውቋል።

በሲድኒ ዋኬሌ በተባለች ሥፍራ የደረሰው ድርጊት በቀጥታ ሥርጭት የተላለፈ ሲሆን ሥፍራው እንዲታመስ ምክንያት ሆኗል።

የአውስትራሊያ ፖሊስ የሽብር ድርጊትን በርዕዮተ-ዓለም የተነሳ የሚፈፀም ድርጊት ሲል ይተነትነዋል። ምንም እንኳ ምርመራው ባይጠናቀቅም ጥቃቱ የተፈፀመው ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነትን ተከትሎ ነው ይላል ፖሊስ።

ባለሥልጣናት ጥቃት አድራሹ ታዳጊ እምነቱ ምን እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።

ታዳጊው አቡኑ ላይ በስለት ጥቃት ሲያደርስ የሚያሳይ ቪድዮ ማሕበራዊ ሚድያውን ያጥለቀለው ሲሆን ይህን የተመለከቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤተ-ክርስትያኗ ተመዋል።

ቤተ-ክርስትያኗ ከከተማው ማዕከል 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ ነው የምትገኘው።

በሥፍራው የተሰበሰቡት ሰዎች ከፖሊስ ጋር የተጋጩ ሲሆን ፖሊስ ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ሕክምና እስኪያገኝ ድረስ ቤተ-ክርስትያኗን ከቦ ሲጠብቅ አምሽቷል።

ከፖሊስ ጋር በነበረ ግጭት ሁለት ፖሊሶች ሲገደሉ 10 የፖሊስ መኪናዎች ደግሞ ወድመዋል። ሕክምና ሰጪዎች ለሶስት ሰዓታት ያክል ውስጥ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ ጥቃቱን “አሰቃቂ” ሲሉ ካወገዙት በኋላ ብሔራዊ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶችን ድንገተኛ ስብሰባ ጠርተዋል።

“እኛ ሰላም ወዳድ ሀገር ነን. . . ለፅንፈኝት ቦታ የለንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰዎች እንዲረጋጉና ምርመራውን ለፖሊስ እንዲተዉ አሳስበዋል።

ፖሊስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አቡኑ እና ቄሱ የቀዶ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጾ የኃይማኖት አባቶቹ “በሕይወት መቆየታቸው አስደናቂ ነው” ብሏል።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አቡኑ ታዋቂው አባ ማር ማሪ ኢማኑዔል ሲሆኑ ቄሱ ደገሞ አባ ኢሳክ ሮዬል ይባላሉ።

በ2011 የተቀቡት አቡነ ኢማኑዔል ታዋቂ የኃይማኖት አባት ሲሆን በማሕበራዊ ሚድያ የሚሰጧቸው ትምህርቶች በሚሊዮኖች ይታያሉ።

ፖሊስ ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ወደ አቡኑ ተጠግቶ ጥቃት ከማድረሱ በፊት “ኃይማኖት ተኮር” አስተያየት መስጠቱንና በቀጥታ በሚተላለፍ ፕሮግራም ጥቃት ማድረስ የፈለገው ሆነ ብሎ መሆኑን ተናግሯል።

ተጠርጣሪው ይህን ድርጊት የፈፀመው ብቻውን መሆኑን አልፎም “ፖሊስ እስከሚያውቀው ድረስ” የሽብርተኞች መዝገብ ላይ አለመኖሩን የፖሊስ መግለጫ ያሳያል።

ግለሰቡ ጣቶቸ ላይ ጉዳት ስለደረሰበት ቀዶ-ጥገና እየተደረገለት ሲሆን ጉዳት የደረሰበት በራሱ ስለት ይሁን አሊያም ምዕመናኑ ሊያስቆሙት ሲሞክሩ የሚለው ግልፅ አይደለም።

ባልተያያዘ ዜና ከቀናት በፊት በሲድኒ የገበያ ማዕከል አንድ ግለሰብ በስለት ስድስት ሰዎች ወግቶ መግደሉ በተሰማ ማግስት ይህ መሆኑ ብዙዎችን አስደንግጧል።

ዋኬሌ የሚባለው ሥፍራ አነስተኛ ቁጥር ያለው የሲድኒ ኦርቶዶክስ ክሪስቲያን አሲሪያን አባላት መኖሪያ ነው። አብዛኛዎቹ ከኢራቅና ሶሪያ ግድያን ሸሽተው የመጡ ናቸው።

አቡነ ኢማኔዔል በማሕበረሰቡ ተደማጭነት ያላቸው የኃይማኖት መሪ ሲሆን ዳይ ሌ የተባለ ግለሰብ “በጣም ሩህሩህ፣ ንፁሕ እና ሀቀኛ ሰው ናቸው” ሲል ይገልጻቸዋል።

ነገር ግን አቡኑ ከዚህ ቀደም ከአሲሪያን ቤተ-ክርስትያን ጋር ተጋጭተው የራሳቸውን ቤተ-ክርስትያን ለማቋቋም በመሞከራቸው ከሥራቸው ለተወሰነ ጊዜ ታግደው ነበር።

በ2021 በኮቪድ-19 ምክንያት የተጣለውን የእንስቅስቃሴ ገደብ በመቃወም እንዲሁም ክትባቱ ውጤታም አይደለም የሚል አቋም በማራመድ ቀዳሚ ነበሩ።