ታዋቂው አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል በቀጥታ የሚተላለፍ ትምህርት እየሰጡ ሳሉ በስለት ተወጉ

በአውስትራሊያ ሲድኒ በቀጥታ በኢንተርኔት እየተላለፈ የነበረ መንፈሳዊ ትምህርት እየሰጡ የነበሩት አቡን እና ሌሎች ምዕመናን በስለት ተወጉ።

ይህ የሆነው ዋኬሌ በሚገኘው ክራይስት ዘ ጉድ ሼፐርድ በተሰኘው ቤተ-ክርስቲያን በአውስትራሊያ ሰዓት በቆጣጠር ዛሬ ሰኞ አመሻሽ ላይ በነበረ ሥነ-ሥርዓት ነው።

በስለት ጥቃት ከተፈጸመባቸው መካከል የሆኑት አቡነ ማር ማሪ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በእንግሊዝኛ በሚያርቧቸው መንፈሳዊት ትምህርቶቻቸው ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በብዙዎች ዘንድ ተደማጭ ናቸው።

ጥቃቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በስለት ተወግተዋል የሚል ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ ወደ ሥፍራው ተሰማርቶ ሁኔታውን ያጣራ ሲሆን፣ የሰዎች ሕይወትን ለአደጋ የሚዳርግ ጉዳት አልደረሰም ብሏል።

ፖሊስ አክሎ እንደገለጠው አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሎ አድራሻው ወዳልተገለጠ ሥፍራ ተወስዷል።

ከጥቃቱ በኋላ በርካታ ሰዎች የተሰባሰቡ ሲሆን ቢቢሲ ያላጣራቸው የማኅበራዊ ሚድያ ቪድዮዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ ሰዎች በሕንፃው እና በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መኪናዎችን ላይ ጥቃት አድርሰዋል።

ሥፍራው በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠበቀ እንደሆነ የገለጠው ፖሊስ ሰዎች ወደዚያ አካባቢ እንዳይሄዱ አሳስቧል።

የአካባቢው ፖሊስ ጥቃት የደረሰባቸው አቡን ስማቸው ማር ማሪ ኢማኑዔል እንደሆነ አሳውቋል። የኢስተርን ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንም ከፖሊስ ዘገባ በኋላ የሃይማኖት አባቱን ማንነት ይፋ አድርጓል።

ቤተ-ክርስቲያኗ በሰጠችው መግለጫ አባ ኢሳክ የተባሉ ቄስም ጉዳት እንደደረሰባቸው አሳውቋል። ሁለቱም የሃይማኖት አባቶች ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ተልከዋል።

“አሁን ፀሎታችሁን እንሻለን” ይላል ቤተ-ክርስቲያኗ ከአደጋው በኋላ ያወጣችው መግለጫ።

መግለጫው አክሎም “ቤተ-ክርስቲያኗ አካባቢ ያሉ ሰዎች በሰላም ከሥፍራው ገለል እንዲሉ በትህትና እንጠይቃለን” ብሏል።

የአካባቢው ከንቲባ ፈራንክ ካርቦን ሕዝብ ወደ መረጋጋ እንደሚለስ ጠይቀዋል።

“የአካባቢያችን ሰዎች በተፈጠረው ነገር እንደተደናገጡ አውቃለሁ፤ ነገር ግን አሁን ዋናው ጉዳይ አቡኑ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው እና ጤናቸው መልካም መሆኑ ነው” ሲሉ ለስካይ ኒውስ አውስትራሊያ ተናግረዋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው አካባቢው አነስተኛ ቁጥር ያለው የሲድኒ ክሪስቲያን አሲሪያን አባላት መኖሪያ ነው። አብዛኞቹ ከኢራቅ እና ከሶሪያ ግድያን ሸሽተው የመጡ ናቸው።

በኢንተርኔት አማካይነት በቀጥታ እየተላለፈ በነበረው ሥርጭት ላይ ጥቁር የለበሰ አንድ ግለሰብ ወደ አትሮነሱ ቀርቦ አቡኑ ላይ ጥቃት ሲያደርስባቸው ይታያል።

በርካታ ሰዎች የግለሰቡን ጥቃት ለማስቆም ሲሞክሩ የታዩ ሲሆን፣ የተቀሩት ምዕመናን ጩኸትም ይሰማል።

“ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ሕይወታቸው ላይ ስጋት የማይደቅን ጉዳት ነው የደረሰባቸው። የአምቡላንስ የሕክምና ባለሙያዎች እንክብካቤ እያደረጉላቸው ይገኛል” ይላል የፖሊስ መግለጫ።

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በ20 እና 70 ዕድሜ መካከል የሚገኙ ወንዶች ናቸው።

ግለሰቡ ጥቃቱን ለምን እንዳደረሰ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ከስድስት ቀናት በፊት በስድኒ አንድ ግለሰብ ወደ ገበያ አዳራሽ ገብቶ በስለት ባደረሰው ጉዳት ስድስት ሰዎች መግደሉ ይታወሳል። ጥቃት አድራሹ በፖሊስ ጥይት ተገድሏል።

ሁለቱ ጥቃቶች የሚገናኙ ስለመሆናቸው የሚጠቁም ምንም ዓይነት መረጃ የለም።